1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጀርመን የዓለምአቀፍ ጤና ተማሪዉ ኢትዮጵያዊ ተሞክሮ

ዓርብ፣ ኅዳር 14 2011

ሃይድልበርግ የዩንቨርስቲ ከተማ ነዉ። ነዋሪዉ በጣም ትንሽ ነዉ። ወደ 160 ሺህ ነዋሪዎች እንደሚኖሩ ይነገራል። ከነዚህ መካከል ደግሞ 30ሺዉ ገደማ ነዋሪ ተማሪ ነዉ። በዚህም ከአምስቱ ነዋሪ መካከል አንዱ ተማሪ ብሎም በጣም ዓለምአቀፋዊ ከተማ ነዉ። ሲል የሕክምና ተማሪዉ የሚኖርበትን የጀርመን ከተማ ይገልፃል።

https://p.dw.com/p/38oLs
Getahun Woldu Lema, Student aus Äthiopien in Heidelberg, Deutschland
ምስል privat

በጀርመን የዓለምአቀፍ ጤና ተማሪዉ ኢትዮጵያዊ ተሞክሮ

ነገ ፈተና ስላለብኝ በጠዋት ከቤቴ ወጥቼ በዩንቨርስቲያችን በሚገኘዉ ትልቅ ቤተ-መጻሕፍት ዉስጥ ቁጭ ብዬ እያጠናሁ ነበር፤ አለ ከ«DW» ለተደረገለት የስልክ ጥሪ መልስ ሲሰጥ።  ዶ/ር ጌታሁን ወልዱ ለማ ይባላል። የሕክምና ትምህርቱን በቀጣይ በጀርመን ሃገር ለመከታተል በቅርቡ የመጣ የ29 ዓመት ወጣት ነዉ። የካቶሊክ የአካዳሚ ልውውጥ አገልግሎት «KAAD» በኩል የትምህርት እድል አግኝቶ የሕክምና ሞያን በጀርመን ሃይደልበርግ ከተማ በሚገኘዉ በአዉሮጳ ግዙፍ በተባለዉ ዩንቨርስቲ በመከታተል ላይ ይገኛል።  ወጣቱን የሕክምና ባለሞያ ዶ/ር ጌታሁንን ፈተናህ ምንድነዉ አልነዉ። 

«Epidemiology እና Biostatistics ይባላል። «Epidemiology» ማለት የበሽታ ጥናት ማለት ነዉ። «Biostatistics» ማለት ደግሞ ዝርዝር መረጃ፤ የጤና ዝርዝር ጥናት ማለት ነዉ። በዚህ ትምህርት ከባድ ፈተና የሚባለዉ የዚህ የሁለቱ ዘርፍ በመሆኑ ሰዉ ሁሉ ተደፍቶ እያጠና ነዉ።» 

ቤተ-መጻሕፍት ገብታችሁ ነዉ የምታጠኑት?

« አዎ ግማሹ ቤቱ ያጠናል ገሚሱ ቤተ-መጻሕፍት መጥቶ ያጠናል። ለኔ ላይብረሪዉ ማለት ቤተ-መጻሕፍቱ ቅርቤ ስለሆነ እዚህ መጥቼ ነዉ የማጠናዉ። እኔ ባለሁበት በሃይድልበርግ ከተማ ዩንቨርስቲ እስካሁን አንድ ኢትዮጵያዉ ብቻ ነዉ ያገኘሁት። ከተገናኘን ወደ አንድ ወር ሊሆነን ነዉ። ለጥቂት ጊዜ ለጥናት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶአል። እስካሁን ያገኘሁት እሱን ብቻ ነዉ። ትምህርት በጣም ስለሚበዛ አብዛኞቻችን አንገናኝም፤።»

ጀርመን ከመጣህ ስንት ጊዜ ሆነህ?

« ጀርመን ከመጣሁ ስምንተኛ ወሬ ነዉ። ቋንቋ ቦን ከተማ ዉስጥ ወደ አራት ወር ተምሬ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርትን አልፌ አሁን የሕክምና ትምህርቴን ሃይድልበርግ ዩንቨርስቲ ጀምሬያለሁ። እንደሚታወቀዉ ሃይድልበርግ ዩንቨርስቲ ጀርመኖች በጣም የሚኮሩበት ዩንቨርስቲያቸዉ ነዉ። በአዉሮጳ ደረጃም ከታየ ሃይድልበርግ ዩንቨርስቲ በአዉሮጳ ከሚገኙ አስር ምርጥ ዩንቨርስቲዎች መካከል ሦስተኛ ደረጃ አካባቢ ላይ ነዉ የሚገኘዉ። ከዓለም ዙርያ የመጡ ብዙ ተማሪዎች የሚገኙበት ዩንቨርስቲ ነዉ። እኔ «International Health» ማለትም ዓለምአቀፍ ጤናን ነዉ በማጥናት ላይ የምገኘዉ። «International Health» ማለት ዓለምአቀፍ ጤና ማለት ጤና ለሁሉም እንዲዳረስ የሚጥር መርህ ነዉ። ጤና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለሰዉ ልጆች የሰብዓዊ መብት እንዲሆን የሚጥር ነዉ። በዚህም ይህ ጥናት ጤና በአንድ ሃገር ወይም በአንድ ቦታ ተስተካክሎ ብቻ እንዲቀጥል ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ታሳቢ ሆኖና ርብርብ ተደርጎበት እንዲዘልቅ በሚሰሩ ሥራዎች ላይ የሚያተኩር ትምህርት ነዉ። ይህ ማለት ጤናን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዴት አድርገን ተንከባክበን በሽታን እንዴት አድርገን መከላከል እንደምንችል እንዴት አድርገን የተቀናጁ ሥራዎችን መሥራት አለብን በሚለዉ ነገር ላይ የሚያተኩር ትምህርት ነዉ። ትምህርቱም ለሁለት ዓመት የሚዘልቅ ነዉ። »   

Getahun Woldu Lema, Student aus Äthiopien in Heidelberg, Deutschland
ምስል privat

በደቡብ ምዕራብ ጀርመን በባደንቩርተምበርግ ግዛት የምትገኘዉ ሃይድልበርግ ከተማ ለየት ያለ ደን ያላት በጥንታዊ ሥነ-ጥበብ የታወቀች እንዲሁም በከተማዋ የሚገኘዉ ዩንቨርስቲ በ14ኛዉ ክፍለ ዘመን የታነፀ በመሆኑ ከተማይቱ በጥንታዊነትዋ ትታወቃለች። ከሃይድልበርግ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አብዛኛዉ የዩንቨርስቲ ተማሪ በመሆኑ፤ ከተማዋ በተማሪዎች መኖርያነትዋ ትታወቃለች ። 

« አዎ ሃይድልበርግ ከተማ የዩንቨርስቲ ከተማ ነዉ የሚባለዉ። ነዋሪዉ በጣም ትንሽ ነዉ። ወደ 160 ሺህ ነዋሪዎች እንደሚኖሩባት ይነገራል። ከነዚህ መካከል ደግሞ 30ሺዉ ገደማ ነዋሪ ተማሪ ነዉ። በዚህም ከአምስቱ ነዋሪ መካከል አንዱ ተማሪ መሆኑ ይነገራል። ከተማዋ በጣም ዓለምአቀፋዊ ናት። እኔም ሃይድልበርግ ትምህርት ከጀመርኩ ወደ አራት ወር ሊሆነኝ ነዉ።»    

በሰሜን ኢትዮጵያ አዲግራት ከተማ የተወለደዉ ዶ/ር ጌታሁን ወልዱ ለማ፤ ትምህርቱን በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ አጠናቆ በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ለሦስት ዓመታት አገልግሏል።   

« የተወለድኩት ሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ አዲግራት በሚባል ከተማ ነዉ። ከዝያ ትምህርቴን የጀመርኩት ኤርትራ ዉስጥ ነዉ። የሕክምና ትምህርቴን የተከታተልኩት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ዉስጥ ነዉ።  ትምህርቴን ከጨረስኩ ሦስት ዓመት ሆኖኛል። ከዝያም አዲስ አበባ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል በሕክምና አገለግል ነበር። በመቀጠል በሕዝብ ጤና ማለትም «Public Health» ዘርፍም ተመርቄያለሁ። በዚሁ ሞያ ዘርፍ ወደ ሦስት ዓመት ሰርቻለሁ። በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ሳለሁ ፤ በተለያየ አደጋ ተጎድቶ በብዛት የሚመጡ ጉዳተኞች ቁስለኞች ጋር ነዉ ያገለገልኩት። ጉዳተኞቹ በመኪና አደጋም ሊሆን ይችላል አልያም በወታደራዊ ጉዳዮች የሚመጡ ቁስለኞች ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህን ታካሚዎች በሰዓቱ በተቀናበረ ሁኔታ ርዳታ ማስጠትና ማከም ነበር። በዚህ ሆስፒታል የሕክምና ሞያን የጀመርኩበት ስለሆነም ብዙ ትዝታዎች ብዙ ልምድ የቀሰምኩበትም ነዉ። ቤቱ ሕክምናን ብዙ እንዳቅ በዘርፉም ብዙ እንድገፋበት ያደረገኝ ቤት ነዉ።»     

ወጣቱ የሕክምና ባለሞያ ወደ አዉሮጳ ለሕክምና ትምህርት ወደ ጀርመን ከመምጣቱ በፊት የቻይና ባህላዊ ሕክምናን ለመከታተል በቻይና ሻንጋይ ነበር። 

« ወደ እዚህ ወደ ጀርመን ከመምጣቴ በፊት ለሁለት ወር የቻይና ባህላዊ ሕክምና  «acupuncture» ትምህርትን ለመከታተል ቻይና ነበርኩ። ወደ አዉሮጳ ወደ ጀርመን የመጣሁት በዚህ የጎርጎረሳዉያን ዓመት 2018 በጋ ላይ ነዉ። የአዉሮጳ በጋ በጣም ደስ የሚልና የሚመች ነዉ። አሁን ግን ክረምቱ በጣም ይበርዳል። ከባድ ነዉ። ከክረምቱ ዉጭ አዉሮጳ ብዙ ደስ የሚል ነገር አለዉ። እኔ በአብዛኛዉ ትምህርት ላይ በመሆኔ ከቤት ወደ ትምህርት ማለትም ወደ ዩንቨርስቲ ከመሄዴ በስተቀር ብዙ ተዘዋዉሬ አላየሆም፤ ሆኖም ግን በጋዉ ላይ የተለያዩ ቦታዎችን ተዘዋዉሬ ለማየት እድሉ ነበረኝ። ብዙ ጥሩ ነገሮችን አይቻለሁ። ጀርመኖች በጣም ጥሩና ቀናዎች ናቸዉ። ተዘዋዉሬ በነበርኩባቸዉ ቦታዎች ሁሉ መንገድ ጠፍቶኝ መንገድ እንዲያሳኙኝ ስጠይቃጠዉ በሥነ-ስርዓት በእንጊሊዘኛ ቆመዉ ነዉ የሚያስረዱኝ። በጣም ተባባሪዎች እና ትሁቶች ናቸዉ።»     

እስቲ የቻይናዉን ትዝታ ንገረን? የህክምና ትምህርትህን ስትከታተል ከቻይናዉያኑ ጋር በምን ነበር የምትግባባዉ? እስቲ ስለቻይናዉ ተሞክሮህ አጫዉተን?

« በርግጥ በጀርመንም ሆነ በቻይና ትምህርቱ የነበረዉ በእንጊሊዘኛ ቋንቋ ነበር። ነገር ግን የቻይናዉ ትንሽ የሚከብድ ነገር ነበረዉ። በቻይና ወጣ ሲባል እንጊሊዘኛ የሚናገር ብዙም ስለማይገኝ አንድ ሰዉ የቻይና ቋንቋን ካልቻለ ኑሮዉ በጣም ከባድ ነዉ። እና ሁሉንም ነገር የምንሰራዉ በግምት ነበር የምንሄድበት ቦታ ሁሉ በግምት ነበር። እኔ ቻይና የነበርኩት ከአንድ ሌላ ጓደኛዬ ጋር ነበር እና በጣም አስቂኝ ትዝታ ነበር ያለኝ። በተለይ ለኛ ኢትዮጵያዉያን ምግቡ ተስማሚ አይደለም። ምግብ ቤት አዘን ስንቀመጥ ስለቻይና የምግብ ነገር ከሃገራችን ይዘን የመጣነዉ ሃሳብም ነዉ መሰል ምግቡን እያየን ስንስቅ ምግቡን ሳንበላ ቤቱ የመዘግያዉ ሰዓት ደርሶ የሚዘጋበት ጊዜ ነበር።» 

በጀርመንስ ምግቡ ተስማምቶሃል?

Getahun Woldu Lema, Student aus Äthiopien in Heidelberg, Deutschland
ምስል privat

« በጀርመን ሁሉ ነገር ተስማሚ ነዉ። በመጀመርያ ደረጃ ዉጭ አንበላም። ሁሉን ነገር አብስለን ነዉ የምንበላዉ ። በተማሪዎች መኖርያ ዉስጥ የምግብ ማብሰያ ማዕድ ቤት «ኪችን» አለን። የፈለግነዉን ነገር ገዝተን እራሳችን አብስለን ነዉ የምንበላዉ። እንጀራም ከፈለግን በሃይድልበርግ ከተማ አንድ የኤርትራ አንድ የኢትዮጵያ ምግብ ቤት አለ። እዝያ ሄደን እንጀራ ገዝተን ወጡን ቤታችን ሰርተን እንበላለን። »  በቻይና ምንም የማረከህ ነገር የለም?

« በቻይና ቆይታዬ ቋንቋ አልተማርኩም ትምህርቱ በኢንጊሊዘኛ ለሁለት ወራት የዘለቀ ነበር። ለሰላምታ ለምስጋና የምትሆን ቃላትን ብቻ ነዉ የማዉቀዉ። በሻንጋይ ቆይታዬ የቻይናዉያኑን መንገድ ሕንፃ በጣም አስደንቆኛል። ሻንጋይ በጣም ትልቅ ከተማ ነዉ። ብዙ በጣም ብዙ ያስደመሙኝ የቻይና ሥራዎችም አሉ። በአጠቃላይ የቻይናዉያኑ የመሰረተ ልማት ሥራዎች የሚደነቅ ነዉ። ከሁሉም በላይ የቻይናዉያኑ የሥራ ባህል የሚገርም ነዉ። በእሁድና በሰኞ መካከል ምንም ልዩነት የለም ሕዝቡ በጣም ሰራተኛ ነዉ ። እሁድም ሰኞም የሥራ ቀን ነዉ።»

የሕክምና ባለሞያዉን ወጣት ጌታሁን ወልዱ ለማ፤ በጀርመን ሃይደልበርግ ከተማ የጀመረዉን ዓለምአቀፍ ጤና ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ ወደ ሃገሩ ተመልሶ እንደ ሕክምና ባለሞያ ብዙ እቅዶች እንዳሉት ይናገራል። ሕክምናን በተመለከተ ኢትዮጵያ ዉስጥ ብዙ መቀረፍ ያሉባቸዉ ችግሮች እንዳሉ እሙን ነዉ ያለዉ ዶ/ር ጌታሁን ወልዱ ለማ ከሕክምና ሞያዉ በበለጠ በተለይ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ ማለትም እንደ ደም ግፊት፤ ስኳር በሽታዎች ላይ ጥናት ማድረግን እንደሚሻ ገልፆአል። ይህ ዓላማዉ አድርጎ የተነሳዉ ደግሞ ኢትዮጵያ ዉስጥ የጤና ፖሊስና የምርምር እጥረት በመኖሩ መሆኑ ሳይገልጽ አላለፈም።  የጤና ባለሞያዉ ጌታሁን ወልዱ ለማ በዚህ ረገድ የራሴን አስተዋጽኦ ለማድረግ እቅድ አለኝ ሲል ገልጿል።  

ከሕክምና ባለሞያዉን ወጣት ሙሉ ቃለ-ምልልስ የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ