1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጀርመን የተባባሰው ኮቪድ 19

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 13 2013

ጀርመን ለሁለተኛው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ማዕበል ምክንያት የእንቅስቃሴ እገዳዋን አጠናክራለች። በተሐዋሲው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር አለመቀነሱ ምናልባትም እስከ መጪው ጥር 3 ቀን 2013 ዓ,ም ድረስ የተቀመጠው የእንቅስቃሴ ገደብ ሳይራዘም አይቀርም እየተባለ ነው።

https://p.dw.com/p/3n6ls
Deutschland | Krankenschwester neben Coronapatient
ምስል Ina Fassbender/AFP/Getty Images

«በተሐዋሲው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ»

የጀርመን መንግሥት አጠቃላይ የእንቅስቃሴ እገዳ ለሁለተኛ ጊዜ ወስኖ ከምግብና መጠጥ፤ ከመድኃኒት እና መሰል ከአስፈላጊ ነገሮች መሸጫዎች በቀር ማንኛውም የንግድ አገልግሎት እንዲዘጋ ከወሰነ ሳምንት ሆነው። ድንጋጌው በያዝነው ሳምንት መጨረሻ ቀናት በሚከበረውና በጀርመናውያን ዘንድ ዋነኛው ቤተሰብ ከቤተሰብ በሚገናኝበት ዓመት በአልም ከሁለት ቤተሰብ በላይ በአንድነት እንዳይሰበሰብ ጥብቅ ማሳሰቢያ ተላልፏል። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከዚህ በፊት በጀርመን ባልታየ ደረጃ በየዕለቱ በተሐዋሲው የሚያዙ ሰዎች ቁጥራቸው መጨመሩም ስጋቱን ከፍ እያደረገው ነው። እንደሚታወሰው ባለፈው ዓመት ከመጋቢት እስከ ግንቦት ባሉት ወራት መላው ዓለም በታማሚዎችና በሟቾች ብዛት ግራ በተጋባበት ወቅት ጀርመን ውስጥ የታየው ጥንቃቄ በአርአያነት ሲጠቀስ እንዳልነበረ አሁን የሚታየው አነጋጋሪ ሆኗል።  ዶክተር ሰብለወንጌል ይመኔ፤ የውስጥ ደዌ ሀኪም ሲሆኑ ከኮሎኝ ከተማ ወጣ ብላ በምትገኘው ኤንግልስ ኬርሸ በተሰኘች አነስተኛ ከተማ ውስጥ ባለው ቅዱስ ዮሴፍ ሆስፒታል ውስጥ በሙያቸው ያገለግላሉ። ጀርመን ውስጥ በተሐዋሲው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ለመጨመሩ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ ያሏቸውን ገልጸውልናል። በአሁኑ ጊዜ በመላው ጀርመን በሚገኙ በርካታ ሀኪም ቤቶች ለኮቪድ 19 ታማሚዎች የሚሆን የማስታመሚያ ክፍሎችን በመለየት ርዳታ የሚያሰፍልጋቸውን እያስተናገዱ መሆናቸው በየዕለቱ ይነገራል። ዶክተር ሰብለወንጌል በሚሠሩበት ቅዱስ ዮሴፍ ሆስፒታል ውስጥም የእነዚህ ታማሚዎች ቁጥር ጨምሯል።

Berlin | Robert Koch Institut
ምስል Carsten Koall/dpa/picture-alliance

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት በሚል የሚወሰዱት የጥንቃቄ ርምጃዎች በሌላ ወገን አዎንታዊ ውጤት ማስገኘቱ አንድነገር ቢሆን አዲስ የተባለው የተሐዋሲው ባህሪ ሌላ ጭንቀት ሌላ ስጋት ሆኗል። በአዲስ መልክ ብሪታንያ ውስጥ መከሰቱ ይፋ የሆነው የዚህ ተሐዋሲ የመዛመት ፍጥነት ቀድሞ ከተከሰተው በብዙ እጥፍ የፈጠነና የሚያስከትለው ጉዳትም የባሰ ነው መባሉ ብሪታንያ ከሌሎች ሃገራት ጋር ያገናኛት የነበረው መስመር እንዲዘጋ ምክንያት ሆኗል። እስካሁን ስለአዲሱ አይነት ተዛማች ተሐዋሲ ከተመራማሪዎች ብዙም የተባለ ነገር ባይኖርም በቅርቡ የተጀመረው የኮቪድ 19 ክትባት ላይ ተፅዕኖ አይኖረውም እየተባለ ነው። ስለመጪው ጊዜ መናገር ባይቻልም ለአሁኑ የአውሮጳ የመድሐኒት ተቋም ትናንት ባዮንቴክ እና ፋይዘር የተባሉ ኩባንያዎች በጋራ ላዘጋጁት የኮሮና መከላከያ ክትባት ፈቃድ ሰጥቷል። የአውሮጳ ሕብረትም አባል ሃገራትም የሕብረቱ ኮሚሽን በይፋ ሲያጸድቅ ክትባቱን ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎቻቸው መስጠት ይጀምራሉ።

 ሸዋዬ ለገሠ 

ነጋሽ መሐመድ