1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጀርመን የቢሮ ሰራተኞች ከቤታቸዉ እንዲሰሩ ተጠየቀ

ዓርብ፣ ጥር 7 2013

የጀርመን ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ሠራተኞች ወደ ቢሮ ከመሄድ እንዲታቀቡ ጥሪ አቀረቡ። ፕሬዝደንቱ ዛሬ ይህን ጥሪ በቴሌቪዥን ያስተላለፉት ጀርመን ውስጥ በኮቪድ 19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ በመምጣቱ የተሐዋሲውን ስርጭት ለመቀነስ በሚል ነው።

https://p.dw.com/p/3nzAP
Deutschland Coronavirus Steinmeier Appell Homeoffice
ምስል Bernd von Jutrczenka/dpa/picture alliance

የጀርመን ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ሠራተኞች ወደ ቢሮ ከመሄድ እንዲታቀቡ ጥሪ አቀረቡ። ፕሬዝደንቱ ዛሬ ይህን ጥሪ በቴሌቪዥን ያስተላለፉት ጀርመን ውስጥ በኮቪድ 19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ በመምጣቱ የተሐዋሲውን ስርጭት ለመቀነስ በሚል ነው። የሀገሪቱ የተላላፊ በሽታዎች መቆጣጠሪያ ተቋም ዛሬ ይፋ እንዳደረገው ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 22,368 ሰዎች በተሐዋሲው ተይዘዋል፤ ባጠቃላይም በሀገሪቱ በኮሮና የተያዙትም ከ2 ሚሊየን በልጠዋል። ፕሬዝደንት ሽታይንማየር በተሐዋሲው የተያዙት ቁጥር ከመጨመሩ ሌላ በተለይ ብሪታንያ ውስጥ የታየው የተለወጠው የተሐዋሲ አይነት በማዕከላዊ አውሮጳ መገኘቱም እንዳሰጋቸው ነው ያመለከቱት። 
«አለመታደል ሆኖ በርካታ ሰዎች በሀገራችን በኮሮና ተሐዋሲ እየተያዙ ነው፤ በዚያም ላይ በተሐዋሲው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መብዛቱ አሳዝኝና አሳሳቢ ነው። በብሪታንያ ወይም በደቡብ አፍሪቃ እንደሆነው የተለወጠው ተሐዋሲ አይነት በተወሰኑ ሰዎች ላይ እዚህ ጀርመን ውስጥም  መገኘቱ ስጋቱን ይበልጥ አባብሶታል። ይህ በጣም አሳስቦኛል።»
ፕሬዝደንቱ አክለውም ከጀርመን የሠራተኛ ማኅበራት ጥምረት ኃላፊዎች ጋር በጉዳዩ መነጋገራቸውን በማመልከትም የግድ ካልሆነ በቀር ሰዎች ወደ መሥሪያ ቤታቸው ከመሄድ እንዲታቀቡ አሳስበዋል።  መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በበኩላቸው ቀጣይ ጠንካራ ርምጃ ለመውሰድ ከ16ቱ የፌደራል ግዛቶች ጋር ለመነጋገር ማቀዳቸው ተነግሯል። 


ሸዋዬ ለገሰ 

አዜብ ታደሰ