1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የበርሊን ግንብ የፈረሰበት 30ኛ ዓመት 

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 18 2012

ጀርመን ለሁለት በተከፈለችበት ዘመን በአንድ የጀርመን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ወይም በምሥራቅ ጀርመን ዜጋ እና በምዕራብ ጀርመናዊ መካከል ክልክል የነበረውን ጓደኝነት ሁለቱ የጀመሩት ቡልጋርያ ውስጥ በጎርጎሮሳዊው 1977 ዓም ማለትም የዛሬ 42 ዓመት ነበር።

https://p.dw.com/p/3S9am
30 Jahre Mauerfall - Zeitzeugen
ምስል privat

የዛሬ 41 ዓመቱ ስደት በዶናው ወንዝ ላይ

ጀርመንን ለሁለት ከፍሎ የቆየው የበርሊን ግንብ ከፈረሰ በሚቀጥለው ሳምንት ቅዳሜ  30 ዓመት ይሞላዋል። ግንቡ ሲፈርስ በርካቶች ከምሥራቅ ጀርመን ወደ ምዕራብ ጀርመን ገብተዋል። ከዚያ በፊትም ብዙ የምሥራቅ ጀርመን ዜጎች ህይወታቸውን ለአደጋ እያጋለጡ ጭምር በተለያዩ መንገዶች ወደ ምዕራብ ጀርመን ሲገቡ ቆይተዋል።ከመካከላቸው አንዱ በዋና እና በመኪና  ድንበር አቋርጦ የገባው የያኔው ምሥራቅ ጀርመናዊ ይገኝበታል።
ጀርመን ለሁለት ተከፍላ በነበረችበት ዘመን ጓደኛሞች የነበሩት አንድ ምዕራብ ጀርመናዊና አንድ ምሥራቅ ጀርመናዊ የዛሬ 30 ዓመት የበርሊን ግንብ ከመፍረሱ በፊት በፈጸሙት ጀብዱ ለየት ያለ ታሪክ ይጋራሉ ።ሁለቱም ግንቡ በጎርጎሮሳዊው ህዳር 9፣1989 የመፍረሱን ዜና የሰሙት በተለያየ ቦታ ሆነው ነበር።  አንደኛው ዜናውን የሰማው ህንድ ውስጥ በአንድ የባህር ዳርቻ እየተዝናና ሳለ ነበር።ሌላኛው ደግሞ ደቡብ ጀርመን ሙኒክ በሚገኝ መኖሪያ ቤቱ ውስጥ ሆኖ በቴሌቪዥን ነበር ግንቡ ሲፈርስ ፈዞ ሲመለከት የነበረው።አንደኛው የሆነውን ማመን አቅቶት  በደስታ ሲፈነጥዝ ሌላኛው ደግሞ ደስታው አስለቅሶታል።ከዛሬ 41ዓመት በፊት የምሥራቅ ጀርመን ነዋሪ የነበረው ኤክሃርድ ቫልተር ጀርመንን ለሁለት ከፍሎ የቆየውን የበርሊንን ግንብ መፍረስ ወደ ኃላ መለስ ብሎ ሲያስታውስ በህይወቱ የገጠመው አስደሳች ነገር መሆኑን ይናገራል። 
«በፖለቲካ ህይወቴ ውስጥ እጅግ ደስ የሚል ተሞክሮ ነበር፤ የጀርመን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ መንኮታኮት በጀርመን ታሪክ በአጠቃላይ ልዩ ስፍራ የሚይዝ ነው።»
ቫልተር እንደሚለው ግንቡ ይፈርሳል ብሎ አስቦም አያውቅም ነበር።ግንቡ ከመፍረሱ በፊት የኖረባት ምሥራቅ ጀርመን ያለ ግንቡ ልትቆይ አትችልም ነበር ይላል።ምሥራቅ ጀርመናዊው ቫልተር ግንቡን ጥሶ ምዕራብ ጀርመን የገባው ከመፍረሱ ከ11 ዓመታት በፊት በዋና እና በመኪና ነበር። ዶናው በተባለው ወንዝ ላይ 25 ኪሎሜትር ዋኝቶ ነው ምኞቱ የተሳካለት። ቀሪውን መንገድ ደግሞ ከጓደኛው ጋር በመኪና ተጉዞ ነው ምዕራብ ጀርመን የደረሰው። በዋና ካቋረጣቸው ከተሞች መካከል የሃንጋሪው ሞሃክስ እና የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ከተማ ባቲና ይገኙበታል። ቫልተር በድፍረት ጀብዱውን የጀመረበትን ስፍራ ለመጎብኘት በዚህ ዓመት በታሪካዊው ቦታ ተገኝቶ ነበር።ዳናው እንደደረሰ እንባ ነበር የቀደመው።ዋና የጀመረበት ቀን የህይወቱ ማለፊያ ቀን ሊሆን ይችል እንደነበረ ይሰማዋል። ሆኖም ህልሜን ላሳከበት ችያለሁና ምን ጊዜም ደጋግሜ ላደርገው እችላለሁ ብሏል፣በዋና የተሻገረውን የዳናውን  ወንዝ ባሻገር እየተመለከተ። በስተጀርባው ያኔ ወደ ምዕራብ ጀርመን እንዲሰደድ የረዳው በምዕራብ ጀርመንዋ በኮሎኝ ከተማ የሚኖረው ጓደኛው ኤልሃርት ዜልባህ ቆሟል።ዛሬ ሁለቱም በ60 ዎቹ እድሜ የሚገኙ አዛውንት ናቸው።ያኔ በ20 ዎቹ እድሜ ውስጥ ሳሉ ነበር እቅዱን አውጥተው የተገበሩት።«ያኔ የምንሞት አይመስለንም ነበር» ይላሉ። ጀርመን ለሁለት በተከፈለችበት ዘመን በአንድ የጀርመን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ወይም በምሥራቅ ጀርመን ዜጋ እና በምዕራብ ጀርመናዊ መካከል ክልክል የነበረውን ጓደኝነት ሁለቱ የጀመሩት ቡልጋርያ ውስጥ በጎርጎሮሳዊው 1977 ዓም ማለትም የዛሬ 42 ዓመት ነበር።ያኔ በሁለቱ ሃገራት መካከል ስላለው የፖለቲካ ልዩነት ደንታም አልነበራቸውም።አንድ ቀን ሁለቱም በተዋወቁበት ቦታ ኤክሀርት ዜልባህ ጓደኛውን ኤክሀርት ቫልተርን ሃገርህን ጥለህ መውጣት አትፈልግም ወይ ሲል ይጠይቀዋል።ቫልተር ወዲያውኑ ፍላጎቱን አላሳወቀም።ያኔ ሃሳቡም አልነበረውም።
«ለመጥፋት አስቤም አላውቅም ነበር።ድንበሩ በአደገኛ ሁኔታ ይጠበቅ ነበር። በኤልበ ወንዝ ላይ ዋኝቼ ቢሆን ኖሮ የራስን ሕይወት በገዛ እጅ ማጥፋት ነበር የሚሆነው።በዚህ የተነሳ ስለዚህ ጉዳይ አስቤም አላውቅም ነበር።»
ከሳምንቱ በኋላ ግን አዎን እፈልጋለሁ አለው ለጓደኛው።ዜልባህ ቡልጋርያ ውስጥ የተዋወቀውን ጓደኛውን ቫልተርን ለመርዳት ፈቃደኛ ነበር። ወደ ኮሎኝ ከተመለሰ በኋላ ወደ ከምሥራቅ ጀርመን ምዕራብ ጀርመን መግባት ስለ ሚያስችሉ መንገዶች መረጃ መሰብሰብ ጀመረ። በሻንጣ አድርጎ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ጀርመን ማስገባትም ብሎ አሰበ ።ይህ ደግሞ በጣም አደገኛ ነው አለ።በተጭበረበረ የምዕራብ ጀርመን ፓስፖርት ከቡልጋሪያ ወደ ቱርክ እንዲሄድም አስቦ ነበር።ያም አልተዋጠለትም።ከተወሰኑ ወራት በኋላ ሁለቱ ምሥራቅ በርሊን ውስጥ በተገናኙበት ወቅት ዜልባህ ለቫልተር እንግዲህ በከባዱ መንገድ ነው ማድረግ  ያለብን።ዶናውን ዋኝተህ መሻገር ግድ ይላል ሲል ነገረው።ዶናው ከጀርመን ተነስቶ በዘጠኝ  የአውሮፓ ሃገራት በኩል የሚያልፍ 2850 ኪሜትር ርዝመት ያለው እና መድረሻውም ጥቁር ባህር የሆነ ወንዝ ነው። 
«ኤክሃርድ ዶናውን መዋኘት አለብህ ሲል ነገረኝ።እኔም መቼ ነው ይህን የምንደርገው ብዬ ጠየቅኩት ከትንሳኤ እስከ ጳራቅሊጦስ በዓል ባለው ጊዜ ውስጥ አለኝ እኔ ደግሞ በተቻለ ፍጥነት ቢሆን ጥሩ ነው ወደ ብሔራዊ ውትድርና ከመግባቴ በፊት አልኩት ምንም ዓይነት ፍላጎት አልነበረኝም እና» 
ከዚያ በኋላ ሁለቱም መዘጋጀት ጀመሩ።ቫልተር ከጀርመን ክዌድሊንቡርግ ከተባለው ስፍራ በየቀኑ ዋና ሲለማመድ ዜልባህ  ደግሞ ኮሎኝ ሆኖ ጉዞውን ያቅድ ነበር።ለጉዞው አስፈላጊ የሆኑ መታወቂያ እና ፓስፖርት የመሳሰሉ ሰነዶችን ያሰራ ነበር።ዜላባህ በጎርጎሮሳዊው 1978 የስቅለት እለት እነዚህን ሰነዶች እና ጓደኛው ለዋናው የሚያስፈልገውን ልብስ ይዞለት ከጠዋቱ በ11 ሰዓት  ከኮሎኝ ተነስቶ ከ22 ሰዓትት በኋላ 1600 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው የሃንጋሪው ፔክስ  የባቡር ጣቢያ ደርሶ ከጓደኛው ቫልተር ጋር ተገናኙ። ቫልተር የዚያኑ እለት ከሌሊቱ 7 ሰዓት ላይ ፍርሃት ፍርሃት እያለው የዋና ጉዞውን ጀመረ። የፈራው እሱም ብቻ አልነበረም ጓደኛውም ጭምር እንጂ ቫልተር በዋና ዶናውን ሰንጥቆ ሲጓዝ ዜልባህ ደግሞ በመኪና ወደ ዩጎዝላቪያ ተመለሰ።ከዚያ በኋላ ቫልተርን የሚጠብቅበት አስጨናቂው ጊዜ ደረሰ።ልቡ ይመታል የሞተር ጀልባ ድምጽ በሰማ እና ውሻ በበጮኽ ቁጥር ሲሳቀቅ ነጋ።ቫልተርም በብዙ ስቃይ ና ድካም በመካከሉም እያረፈ ከጓደኛው ዜልባህ ጋር የተቀጣጠሩበት ዩጎዝላቭያ ባቲና በተባለችው ስፍራ ከሚገኝ ድልድይ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ደረሰ። ከዚያም በመኪና ጉዞአቸውን ቀጠሉ።በውድቅት ለሊት መኪና "እየነዱ ተፈተለኩ። ሲነጋ ኦስትሪያ ድንበር ደረሱ ኢዚያ እንደደረሱም የጠበቁት አልሆነም።መታወቂያ ፓስፖርት እንጠየቃለን ብለው ጠብቀው ነበር።ያ ግን አልተደረገም።እድል ቀንቷቸው ድንበር ጠባቂዎች ሰላምታ ሰጥተው አሳለፏቸው።በውናቸውም በህልማቸውም ያልጠበቁት ነበር።ኤክሃርት ዜልባህ እንደሚያስታውሰው የሄዱበት መንገድ አደገኛ ነበር።
«እርሱ ፓስፖርት አልነበረውም።እኔ አቃጥየዋለሁ።ለኔ ይህ በጣም አደገኛ ነበር።ርስ ራሱ መሆኑን ማሳመን ነበረበት።ያኔ ፓስፖርቱ መኪና ውስጥ ቢገኝ ኖሮ የተደረገው ስደተኛን ማገዝ መሆኑ በቀጥታ ግልጽ ይሆን ነበር።ግን ውስጤ ሊቀበለው አልቻለም ነበር።» 
ዜልባህ ፣ ቫልተርን ከሚመስል ሰው ፓስፖርት ተውሶለት ነበር።የቫልተር የምሥራቅ ጀርመን ፓስፖርት ጥርጣሬ እንዳይፈጥር በሚል ነበር ያቀጠለበት። ከዚህ ጀብዱ ከተሞላበት አስቸጋሪ እና አስጨናቂ ጉዞ በኋላ ሁለቱም ተሳክቶላቸው ምዕራብ ጀርመን ሙኒክ ገቡ።ያሰቡትን ከግብ ቢያደርሱም እውነት መሆኑን ለማመን ጊዜ ወስዶባቸዋል።የበርሊን ግንብ ከፈረሰ ከ30 ዓመታት በኋላ እንዲሁም ከ40 ዓመትት በላይ ካስቆጠረው ከአደገኛው የስደት ጉዞ በኋላ ቫልተር ምሥራቅም ምዕራብም ጀርመናዊ ሳልሆን ጀርመናዊ ነኝ ብሏል። ግንቡ አሁን ባለመኖሩ ደስተኛ መሆኑንም ይናገራል።ሁለቱ ጓደኛሞች የበርሊን ግንብ እስኪፈርስ ድረስ ይህን ታሪካቸውን ለራሳቸው ብቻ ነበር ይዘው የቆዩት።ምክንያታቸው ይህ ያልታወቀ መንገድ እንዳይዘጋ በማሰብ  ነበር።

30 Jahre Mauerfall - Zeitzeugen
ምስል privat
30 Jahre Mauerfall - Zeitzeugen
ምስል privat
Infografik Karte Donau Ungarn Kroatien Serbien

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ