1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በደቡብ የጠ/ሚ ሰላም የማስፈን ጥረት

ረቡዕ፣ ሰኔ 13 2010

በደቡብ የተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ግጭቶችን ለማረጋጋት ጠ/ሚ ዐብይ አህመድ የወሰዱት ርምጃ በብዙዎች ዘንድ አዎንታዊ መንፈስ አሳድሯል። ትናንት ከሀወሳ ከተማ ጀምረው ወላይታ ሶዶ ዛሬ ደግሞ በወልቂጤ ከኅብረተሰቡ ጋር ያደረጉት ውይይት የችግሩን መንስኤዎች ለመዳሰስ የሞከረና የሕዝቡንም ስሜት ያደመጠ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

https://p.dw.com/p/2zxNm
Addis Abeba, Äthiopien, Äthiopischer Premierminister Abiy Ahmed im Parlament
ምስል DW/Y.Geberegziabher

የጠ/ሚ ዐብይ የሰላም ጥረት በአዎንታዊ አስተያየቶች ታጅቧል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በደቡብ ኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን ግጭት ያረጋጉበት ንግግር እና ወደቦታው በመሄድም ግጭቱ ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት የኅብረተሰቡን ትኩረት መሳቡ ይታያል። የችግሩን መንስኤ ለመመርመር የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዳለ ሆኖ በአሁኑ ወቀት ግጭት በተካሄደባቸው አካባቢዎች የፀጥታው ሁኔታው መረጋጋት እንደሚታይበት በዋትስአፕ እና በፌስ ቡክ ገጻችን የደረሱን መልዕክቶች ያመለክታሉ። ከደረሱን አስተያየቶች 99,9 በመቶ የሚሆነው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሰብዓዊነት የተላበሰ አቀራረብ የሚያደንቅ፤ የጀመሩት ሰላም የማስፈን ጥረት እንዳይደናቀፍ የየበኩሉን ምክር የሚለግስ፤ እንከን ብለው የሚያነሱትም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቅንነቅ የተላበሰ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ የተቀናበረ ችግር መኖሩን የሚጠቁም አይነት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝቡን ጥያቄ ለመስማት ዝቅ ማለታቸው እና ኅብረተሰቡን በየአካባቢው ሄደው ማነጋገራቸውን ካደነቁት አብዛኞቹ አስተያየቶች በዋትስአፕ በጽሑፍ ከደረሱን ጥቂቱ እንዲህ ይላሉ፤ «አሁን ገና መሪዋን አገኘች እናት ኢትይዮጵያ ሠላም ለማስፈን የደደቢትን እንትኖች ከዙሪያው ማፅዳት» አሉ በዋትስአፕ አንዱ፤ « ዶክተር ዐብይ በመሪ ደርጃ የሚሰሩት ስራ ቢያስደስተንም ለመጀመሪያ ግዜ ህዝብ ተበደለ ብሎ ታቺ ወርዶ በደላቺሁ ምድነ ው የሚል መሪ ማገኘታቺን ቢያስደስተንም እሳቸው እዳሉት የቀንጅቦቺ ግን አላኖሩንም። እኔ መፍትሄ የሚመስለኝ ይሄን ሁኩትና ግጭት ፈጣሪወቺ እዳሉ እርሳቸውም አውቃለሁ ብለዎል ስለዚህ ይሄን ካወቁ  እያጣራነው ማለቱን ትተው እርምጃውን መውሰድ ነው የሰውልጅ በጠራራፀሀይ እየተገደለ ወጀለኛ ለመያዝ እያጣራነው የማይመስል ጫወታ ይሆናል ባይነኝ መልካሙን ሁሉ ለህዝባችን።» አሉ ሌላው አስተያየት ሰጪ። «በጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተገኘ ያለዉ እዉነተኛ ዲሞክራሲ ወደ ፊት እንዳይሄድ ሆን ብለዉ የሚሰራው ስራና በስልጣን ሱሰኛ ህወሃት ቅንብር ሰለ ሆነ በጎሳና በሃይማኖት ህዝቡን እያጋጩት ነዉ አማራ ክልል ዉስጥ በተለያዩ ቦታዎች ግጭቶች አሉ።» ሲሉ አከሉ ሌላው። አሁንም በዋትስአፕ የደረሰን «ጠቅላይ ሚንስተራችን እንኳን የኢትዮጵያን ሰላም የምስራቅ አፍሪካን ሰላምም ማረጋገጥ የሚያስችል ብቃት አለው።» ይላል። 
«ህዝቡ ሄዶ ማወያየቱ ጥሩ ነው ግን በቂ አይደለም። እንደኔ መሆን ያለበት የምለው ግጭቱ እንዲቀሰቀስ ያደረጉ አመራሮችና መዋቅራቸው ብትንትኑ ወጥቶ አጥፊዎች እንዲቀጡ ማድረግ ነው። በተጨማሪም ከታች በሀገር ሽማግሌዎች ችግሩ እንዲፈታ ማድረግና መንግሥትም የሀገር ሽማግሌዎች የሚያደርጉት ጥረት ያለምንም ጣልቃ ገብነት ሂደቱ በውጪ ሆኖ መከታተል አለበት ባይ ነኝ።» ያሉም አሉ። «ሀዋሳ ነው የምኖረው ዛሬ ከተማዋ ተረጋግታለች። ሆኖም የመንግሥትን ርምጃ እየጠበቅን ነው።» ያሉን ደግሞ ከሀዋሳ ነዋሪ አንዱ ናቸው። 
በፌስ ቡክ ጌታነህ ዉቤ አምዴ «ለ27 አመታት እንዲባላና እንዲጠፋፋ ሲሰበክ የኖረን ህዝብ ወደ አንድነት ማምጣቱ ጊዜ የሚጠይቅ ስራ ቢሆንም ይህ ብልህ መሪ ብዙም ጊዜ ይፈጅበታል ብዬ አላስብም ፤ ዶክተሩ ለኢትዮዮጵያ ከአምላክ የተሰጠ ONE MORE CHANCE ነው።» ይላሉ፤ ታደሰ ኃይለ ማርያም ደግሞ «ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ቆሞ ማውረድ ይቸግራል" ደምህን አፍሰህ ኣጥንትህን ከስክሰህ በሚሳይል ተዋግተህ ልታገኘው የማትችለው እድል እጅህ ላይ ወድቆልሀል (ዶ/ር አብይን ሰጥቶሀል) ዘረኞች ባጠመዱልህ አዘቅት ገብቶ መዳከር ምን ኣይነት እርግማን ሊሆንነው? አሁንም ለመታረም ጊዜ አለን አንዳችን ለአንዳችን ጌጥ መሆን አለብን እንጅ አንዱ ሌላውን ከምድረ ገፅ አጥፍችቸ እኖራለሁ ብሎ የሚያስብ እራሱን ይፈትሽ "እኛ እየተጠላላን ለምን እንወልዳለን ለእልቂት?..." ብለው ይጠይቃሉ። 
ጀርሚያ ኤርሚያስም ከእሳቸው የሚቀራረብ አስተያየት ነው ያላቸው፤ « ቁጥጥር ሥር ገብቷል ማለት ይከብዳል። እንደገና ሊነሳ ይችላል። የህዝቦች አኗኗር የተጠላለፈ የተጠጋጋ መሆኑ፥ ለረጅም ግዜ የተሰበከ ጥላቻ አስተሳሰብ ታምቆ መኖሩ፥ህግ አስከባሪውም አቋም አለማስትማመኑ ስጋት ነው። መፍትሄው ቀጣይ ውይይትና ድርድር ነው። ብዙ ግዜ ያ የህዝብ ተመራጮች ስራ ነው።በርግጥ ያን ቀድሞ አለማድረጋቸው ለአሁኑ ችግር መንስኤ ነው። ብዙ ስብሰባ ያደርጋሉ ወሳኝ ነገሮችን ለነገ ያስተላልፋሉ። ብዙዎቹ በወሰኑት ነገር ስለማይተማመኑ መራጩን ለማሳመን አይጋፈጡም። ያም ሆኖ በስርአቱ ያለው መፍትሄ ይህን ይመስላል።» አድነው መስቀል ደግሞ መፍትሄ ያሉትን እንዲህ ጽፈዋል፤ « መፍትሔው አሁን በስልጣን ላይ ያሉ የደቡብ ባለስልጣን ላይ አስተማሪ በሆነ መልኩ እርምጃ መውሰድ አለበት ይህም ማለት ከስልጣን ማውረድ በአፋጣኝ ለኢሀዲግም ለወደፊቱ መልካም ጉዞ ይሆንለታል እናም ለቀጣይ ለሚመጡ ባለስልጣን ትምህርት እንዲሆናቸው ።» ገብረስላሴ ጌታሁን በበኩላቸው፤ « በአዋሳ የተቀሰቀሰዉ ግጭት ሰይጣዊ ነበር ለዘመናት አብረዉ የኖሩትን ህዝቦች እርስ በእርስ እሚያጋድል እሚያጋጭ ማን እንደሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ ይገለፅ።» ይላሉ። ለቦጃ ታቦር ደግሞ ጉዳዩ እንዲህ ነው ፤ « በየቦታው ችግር የሚፈጥሩት የወረዳና የቀበሌ ካድሬዎች ናቸው እነዚህን አካላት ለጥፋት የሚያሰማራ ቡድን አለ ስለዚህ በነዚህ የህዝብና የሀገር ጠላቶች ላይ ህዝባችን ከመንግስት ጋር በመተባበር ለፍትህ ሊያቀርባቸው ይገባል።» 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግጭቱ በተከሰተባቸው የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ተዘዋውረው ከኅብረተሰቡ ጋር ባደረጉት ውይይት ከሕዝቡ የቀረቡላቸውን ጥያቄዎች በማድመጥ እንደየሁኔታው ምላሾችን መስጠታቸውን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው። በዛሬው ዕለትም ወልቂጤ ላይ ተገኝተው ኅብረተሰቡን ባነጋገሩበት ወቅት የሲዳማ፣ ወላይታ፣ ጉራጌ፣ ቀቤና ዞን እና ወረዳ ከፍተኛ ባለስልጣናት ስልጣን እንዲለቁ መጠየቃቸውን አቶ ፍፁም አረጋ በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል። በአካባቢዉ ለተፈጠረው አሳዛኝ አጋጣሚም ባለስልጣናቱ ኃላፊነት መውሰድ እንዳለባቸው ጠ/ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል። 

Äthiopien Industriepark Hawassa
ምስል Imago/Xinhua/M. Tewelde

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ