1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርት

በዩቲውብ የቋንቋ አስረማሪው : ታቲ ጋሹ

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 23 2013

ታቲ ጋሹ ዩ ቲውብ ላይ ቋንቋ የሚያስተምርበት « Tatti Tube » የተሰኘ ቻናል አለው። ወጣቱ እንደሚለው በ ዩ ቲውብ ከሚያገኘው ገንዘብ የበለጠ በሚሰጠው ትምህርት የሚያገኘው የመንፈስ ርካታ ይበልጥበታል።

https://p.dw.com/p/3mxNp
Äthiopien | Tatti Tube | Tatti Gashu
ምስል Tatti Tube

ታቲ ጋሹ

ታቲ ጋሹ ዩቲውብ ላይ ከ 60 000 በላይ ተከታዮች አሉት። እንግሊዘኛ፣ ስፓኒሽኛ እና ጀርመንኛ ለአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች በትርፍ ሰዓቱ ያስተምራል። እነዚህን የቋንቋ ትምህርቶች መስጠት ከጀመረ አንድ አመት አለፈው። « ከልጅነቴ አንስቶ ከቋንቋው ጋር የተያያዘ አኪያሄድ ስለነበረኝ አሁን የማውቀውን፣ የምችለውን እና የምወደውን ነገር ለማህበረሰቤ ለማስተማር ፈለኩኝ» ይላል።  ታቲ አራት ቋንቋዎች ይናገራል። ከዚህም ሌላ የፈረንሳይኛ ቋንቋን ለ አንድ ዓመት ተኩል ያህል ተምሯል። ታቲ አሁን ወደሚኖርባት የጀርመን ሀገር ፍራንክፈርት ከተማ ከመምጣቱ በፊት ስፔን ሀገር ለ 10 ዓመት ገደማ ያህል ኖሯል። « ከእድሜዬም አኳያ ፣ እዛም ብዙ ጊዜ ስለቆየሁ በደንብ መናገር እችላለሁ» ይላል። ታቲ ስፓኒሽኛ የማስተማር ፍላጎት ቢኖረውም ቋንቋውን የመማር ፍላጎት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ግን ጥቂት ብቻ ሆነውበታል። « ብዙውን ጊዜ የኛ ማህበረሰብ የሆነ ነገር ሲያስፈልገን ብቻ ነው ለመማር ወይም ለማወቅ የምንፈልገው፤ ይህንን ነገር ብናሻሻል ጥሩ ነው። » በዚህም ምክንያት ወጣቱ በአሁኑ ሰዓት በስፓኒሽኛ የሚሰጠውን ትምህርት አቋርጦ ትኩረቱን ወደ ሌሎቹ ቋንቋዎች አድርጓል።  ቋንቋ ማስተማር የጀመረው ግን በስፓኒሽኛ ነበር። « ወደ አምስት ስድስት ቪዲዮዎች ሰርቻለሁ። ከሚያየው ሰው አንፃር ግን ልፋቴ ይበልጣል።» መማር የሚፈልጉ ሰዎች ካሉ ግን ለማስተማር ፍቃደኛ ነኝ»።
ኤርትራዊው ኤርሚያስ የሺጥላ ከታቲ ተማሪዎች አንዱ ነው። ምንም እንኳን ጀርመን ሀገር ሲኖር 7 ዓመት ቢሆነውም ቋንቋውን በደንብ የመማር እድል ባለማግኘቱ ይህንን አጋጣሚ ለበጎ እየተጠቀመበት እንደሆነ ገልጾልናል። « አብዛኛው ጊዜዬን በስራ ነው ያሳለፍኩት። ጀርመንኛ የተማርኩት ለ 6 ወር ያህል ነው። እና ይህ በቂ አልነበረም።» ኤርሚያስ አማርኛ በመናገሩም ታቲ በዩቲውብ የሚያሰራጫቸውን ቪዲዮዎች እያየ ለመማር ችሏል።
በየሳምንት ከአንድ እስከ ሁለት ማስተማሪያ ቪዲዮዎች እሰራ ነበር የሚለው ታቲ «አሁን ላይ ሰዎች በኮሮና ስጋት እና በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ትኩረታቸው በሌላ ነገር ስለተሳበ ቪዲዮ የምሰራው በአስራ አምስት ቀን አንዴ ሆኗል እና ብዙ እየሰራሁ አይደለም» ይላል። በብዛት የሚያስተምረውም የሰዋሰው ትምህርት ነው። « መዝገበ ቃላትን በትንሽ ልፋት ማወቅ ይቻላል። የሰዋ ሰው ትምህርት ግን ትንሽ የተወሳሰበ ነው፣ መማር ያስፈልጋል። »

Äthiopien | Tatti Tube | Tatti Gashu
ታቲ ጀርመንኛ ለጀማሪዎች ያስተምራልምስል Tatti Tube

ዳግማዊት አፈወርቅ የ 23 ዓመት ወጣት ናት። ከታቲ ጋር የተዋወቀችው በዩቲውብ በሚሰጠው የእንግሊዘኛ ቋንቋ ትምህርት ነው። ዛሬ ታቲ የዩቲውብ መምህሯ ብቻ ሳትሆን ፤ የግል አስጠኝዋም ጭምር ሆኗል።« ስልክ ቁጥሬን የዩቲውብ ቻናሉ ላይ አስቀመጥኩለት። ደወለልኝ እና የምንገናኝበትን መንገድ አመቻችተን ያስጠናኛል» ትላለች የ10ኛ  ክፍል ተማሪዋ።« ዩቲውብ ላይ በሚገባኝ ፣ በቋንቋዬ ስለሚያስረዳኝ በጣም ጥሩ ነው» ። የፍራንክፈርት ከተማ ነዋሪ የሆነችው ዳግማዊት « መማር የሚፈልጉ ነገር ግን የመማር እድል የማያገኙ አሉ።» ስለሆነም በዩቲውብ የሚሰጡ ጠቃሚ ትምህርቶች በአስተማሪዎችም ይሁን በተማሪዎች ዘንድ ሊበረታቱ ይገባል ትላለች።  
የቋንቋ አስተማሪው ታቲ ጋሹ ወደፊት እውን ማድረግ የሚፈልጋቸው ሁለት ህልሞች አሉት። ሁለቱም ከቋንቋ ጋር ይገናኛሉ። « ከሆነ ጊዜ በኋላ የኛንም ቋንቋ ፣ የእኛንም ባህል በተለያየ አጋጣሚ ለውጭ ዜጎች ማቅረብ ፣ማሳየት፣ ማሳወቅ እፈልጋለሁ። ሌላው ደግሞ የቋንቋ ትምህርት ቤቶች ተከፍቶ የተለያየ ቋንቋ መማር የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንን መድረስ የሚቻልበት መንገድ ቢኖር ይህም ሀሳቤ ነው።» ይላል በ ዩቲውብ አማካኝነት የምወደውን እና የምችለውን ነገር ለሌሎች ኢትዮጵያን ለማካፈል ስለፈለኩ ነው ቋንቋዎች የማስተምረው የሚለው ታቲ ጋሹ ።

ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ