1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በየግጭት ጦርነቱ ለችግር የሚጋለጡት ሴቶች በመገናኛ ብዙሃን

ማክሰኞ፣ ሰኔ 21 2014

በማንኛውም ጊዜና መንስኤ በሚነሱ ግጭች ሴቶች እና ሕጻናት ለከፋ ጉዳት ሲዳረጉ ይታያል። ኢትዮጵያ ውስጥ የተደጋገመ ማባሪያ ባጣው ጥቃት እና ግጭት ከቤት ንብረት ከመፈናቀል አንስቶ ለጾታዊ ጥቃት እና ሌሎች እንግልቶች ስለተዳረጉ አዋቂ እና ሕጻናት ሴቶች አልፎ አልፎ መረጃዎች ይወጣሉ። ሆኖም ችግሩ በቂ የመገናኛ ብዙሃንን ሽፋን ሲያገኝ አይታይም።

https://p.dw.com/p/4DNYF
Äthiopien | Binnenvertriebene in Oromia
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ሴቶች እና መገናኛ ብዙሃን

በየጊዜው በሚያከሰቱ የተለያዩ መንስኤዎች ምክንያት ኅብረተሰቡ ለችግር የሚጋለጥባቸው አጋጣሚዎች ይኖራሉ። በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ ችግሮች ሳቢያ በሚፈጠረው ችግር በተለይ ሴቶች እና ሕጻናት ግንባር ቀደም የጥቃት እንግልቱ ሰለባዎች መሆናቸው ይታያል። በግጭት ጦርነት ቤተሰብ ሲበተን፤ በድርቅ በርሃብ ጓዳ ሲራቆት በአብዛኛው ሴቶች እና ሕጻናት የችግሩ ጫና ይጠናባቸዋል። ኢትዮጵያ ውስጥም በቅርብ ጊዜያት እንኳን ማቆሚያ ባጣው ግጭት ጦርነት የብዙዎችን ኑሮ ሲያናጋ ሴቶች እንደማኅበረሰብ አካል ከደረሰባቸው ጉዳት በተጨማሪ ለጾታዊ ጥቃት ተጋልጠዋል። በሌላው ወገን ድርቅ እና ርሃብ ጓዳን ሲያራቁትም እናቶች ለልጆቻቸውም ሆነ ለቤተሰባቸው የሚያቀርቡት አጥተው መቸገራቸው ተደጋግሟል። በጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉት በአማራ ክልል ዋግህምራ ዞን የሚገኙት እመጫት እናት ከራሳቸው በተጨማሪ ለልጆቼ ምን ላብላ፣ ምንስ ላልብስ የሚለው የብዙዎችን ጥያቄ ይወክላል። እሳቸው አንድ ማሳያ ናቸው። ሆኖም በሰሜን ኢትዮጵያ በፌደራል መንግሥት እና በህወሃት መካከል ትግራይ ውስጥ የጀመረው ጦርነት ወደ አጎራባች ክልሎች በመዛመቱ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩት ሴቶች እና ሕጻናት በመጠን ይኽነው ተብሎ መግለጽ በሚያዳግት መልኩ ለከፋ እንግልት መዳረጋቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች ለማንሳት ሞክረናል። በምዕራብ ኢትዮጵያ በወለጋ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጸሙ እና በሚደርሱ ጥቃቶች ዛሬም ድረስ ከነእጻናት ልጆቻቸው መጠጊያ አጥተው የሚቸገሩት ጥቂት አይደሉም። በደቡብ ኢትዮጵያም እንዲሁ ከጥቃት ግጭቶች ጋር በተገናኘም ሆነ በተከሰተው ድርቅ በርካቶች ለችግር ተዳርገዋል። እንዲያም ሆኖ ክስተቱ የሚያገኘውን ያህል የዜና ሽፋን ለመከራ የተዳረጉት ሴቶች ጉዳይ እጅግም የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት ሲሆን አይታይም። በጋዜጠኛነት ያገለገለችው እና አሁን ፕላን ኢንተርናሽናል በተባለው መንግሥታዊ ባልሆነው ድርጅት ውስጥ የተግባቦት ተጽዕኖን በሚመለከተው ዘርፍ ኃላፊ ትዕግሥት ካሣም ይኽንኑ ክፍተት አስተውላለች።

Äthiopien IDPs in der Region Amhara
7ከኦሮሚያ የተፈናቀሉ ዜጎች አማራ ክልል ምስል Alemenw Mekonnen/DW
Äthiopien - IDPs in Debark, Amhara Region
ደባርቅ አማራ ክልል ተፈናቃዮችምስል Debark Woreda Food Security/Disaster prevention Office

ግጭትን በጥንቃቄ መዘገብን አስመልክቶ የሥርዓተ ጾታ ጉዳይ እንዴት ይታያል በሚል ለጋዜጠኞች የተሰጠ ስልጠና እንደነበር ያመለከቱት እና በወቅቱም ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር በመሆን ጉዳዩን በጥልቀት ለማየት መሞከሩን ነው ያመለከተችው። ግጭቱን ተከትሎም በተለይ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን የመደፈር እና እሱን ተያይዞ የሚመጣ የስነልቡና ቀውስ አስመልክቶም እንዲሁ የመገናኛ ብዙሃንን የሙያ ስነምግባር መሠረት ተዘግቧል ወይ የሚለውም እንዲሁ ሌላው ጥያቄ ላይ የሚወድቅ ጉዳይ ነው ባይናት። ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መዘገቡ አንድ ነገር ሆኖ አቀራረቡ እና የሚገለጽበት መንገድ ተጎጂዎቹን ዳግም ለሌላ ችግር እንደሚዳርግም ያካሄዱትን ቅኝት መነሻ በማድረግም አጽንኦት ሰጥታለች። እንዲህ ያለው ማኅበራዊ ችግር ሌላው ወገን እንዲያስተውለው ብሎም እንዲማርበት መገናኛ ብዙሃን አደባባይ ሲያቀርቡ ባለሙያው አስቀድሞ እንዴት ይመልከተው የሚለውም ወሳኝ ነው።

Äthiopien Flüchtlinge in Oromia Region
ጉጂ ዞን የተፈናቀሉ ወገኖች ምስል Seyoum Getu/DW

በሸገር ኤፍኤም ሳምንታዊ የሆነውን ይመችሽ የተሰኘ በሴቶች ላይ ያተኮረ መሰናዶ አዘጋጅ የሆነችው ጋዜጠኛ መልካምሰው ሰሎሞንም ይኽንኑ ጉድለት አስተውላለች። ግን ደግሞ ችግር ወደተከሰተባቸው አካባቢዎች በመሄድ ተጎጂዎችን አነጋግሮ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ጋዜጠኛው የሚገጥመው እንቅፋት ቀላል አይደለም ነው የምትለው። ጋዜጠኞች በሥራ ስምሪት የሚገጥማቸው እንቅፋት እንዳለ ሆኖ እንዴት መቅረብ ይኖርበታል የሚለውም ሌላው ጉዳይ ነው እንደጋዜጠኛ መልካም ሰው።

በማንኛውም አጋጣሚ ማኅበረሰብ ሲታወክ ሴቶች እና ሕጻናት ለከፋ ጉዳት መዳረጋቸው ይታያል። መገናኛ ብዙሃንም እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች ተገቢውን ትኩረት እንዲያደርጉ ነው የሚመከረው። እንዲህ ያለ ማኅበራዊ ቀውስ በሚያጋጥምበት ጊዜ መገናኛ ብዙሃን ጉዳዩን በተሻለ መንገድ ትኩረት ሰጥተው እንዲዘግቡት ለማድረግ ለጋዜጠኞች የሚያነቃ ስልጠና ቢሰጥ የተሻለ ሊሆን ይችላል ነው የምትለው ትዕግሥት።

ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ከሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር መገናኛ ብዙሃኑን የማንቃቱ ሥራ በስፋት እየተሰራ መሆኑን በማመልከትም በተለይ እንዲህ ችግሮች ማኅበረሰቡ ውስጥ ሲከሰቱ ሕጻናት ሴቶች ላይ የሚኖረው ጫና ዘርፈ ብዙ መሆኑንም ነው ያመለከተችው።

Äthiopien Flüchtlinge in Oromia Region
ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተፈናቀሉምስል Seyoum Getu/DW

በነገራችን ላይ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ መላው ዓለም በእንቅስቃሴ ገደብ ላይ በነበረበት ወቅት እስያ በሚገኙ በርካታ ሃገራት እንዲሁም በአረብ ሃገራት አዳጊ ሴት ልጆች ዕድሜያቸው ሳይደርስ ለትዳር በግድ የተሰጡ መሆኑን ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ይፋ አውጥተዋል። መሬት በሴት ማለትም በእናት ትመሰላለች። መሬት ሁሉን እንደምትሸከም የቤተሰብ ኃላፊነት በአብዛኛው በተለይ እንደ እኛ ባለው ኅብረተሰብ የሴቶች ሸክም መሆኑ ይታወቃል። ስለሴቶች ሲነገርም ሴቶችን ብቻ የሚመለከት ጉዳይ እንዳለ ሁሉ ባጠቃላይ የማኅበረሰቡ የዕለት ተዕለት መስተጋብር ላይ ተጽዕኖ ያላቸው ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች መኖራቸውን ልብ ይሏል።

 ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ