1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

'በዚምባብዌ ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት የለም'  ደራሲዋ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 18 2014

ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በሁለት መንገድ አየዋለሁ። በርግጥም ሀሳብን በነፃነት መግለጽ ላይ ጭቆና እና ጫና አለብን። በዚምባብዌ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት አለ። ነገር ግን ሃሳብን ከገለፅን በኋላ ነፃነት የለም የምንለዉ ቀልድ አለን።

https://p.dw.com/p/42HeV
Tsitsi Dangarembga Autorin Simbabwe
ምስል Getty Images/AFP/D. Roland

«ጥሩ ስኬትና እውቅ ሲገኝ ሌሎችን የሚያበረታታ ይመስለኛል»

የዚምባብዌዋ ደራሲ እና ፊልም ሥራ ባለሞያ ፂሲ ዳንጋሬምብጋ፤ ባለፈዉ ሳምንት የዘንድሮዉን የጀርመን መጽሐፍ የሰላም ሽልማትን ተቀብላለች።  ዚምባብዌትዋ ደራሲእና ፊልም ሰሪ ፂሲ ዳንጋሬምብጋ በትውልድ አገሯ ዚምባቤ በሥነ-ጽሁፍ ዘርፍ ያሉትን ተግዳሮቶች ከዶቼ ቬለ ጋር ባደረገችዉ ቃለ ምልልስ ተናግራለች። 
በቀድሞ ስምዋ ሮዴዥያ በመባል በምትታወቀዉ በዚምባቤ በጎርጎረሳዉያኑ 1959 ዓ.ም የተወለደችዉ ደራሲ እና ፊልም ሥራ ባለሞያዋ ፂሲ ዳንጋሬምብጋ ፤ በዚምባቤ በሳይኮሎጂ ማለትም በሥነ ልቦና ሞያ የከፍተኛ ትምህርትዋን አጠናቃለች። ቆየት ብሎ በጀርመን በርሊን የፊልም እና የቴሌቭዝን አካዳሚም በፊልም ሥራ ሞያ ተመርቃለችም። ፂሲ ዛሬ በትዉልድ ሃገርዋ በዚምባቤ ታዋቂ የፊልም ሥራ ባለሞያ በመሆንዋ ታዋቂነትን አትርፋለች። ፂሲ ለእይታ ካከቀረበቻቸዉ ፊልሞች መካከል በተለይም ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱት የኤድስ በሽታ አስከፊነት እና ጥንቃቄዉ፤ ስለሴቶች መብት እና በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በመሳሰሉ ርዕሶች ላይ ለእይታ ባቀረበቻቸዉ ፊልሞችዋ እዉቅናን አግኝታለች።    
ዚምባቤዊትዋ የፊልም ሥራ እና የሥነ-ጽሑፍ ባለሞያ ፂሲ በአገሯ ያሉ ወጣት ሴት ፊልም ሰሪዎችን በንቃት ትደግፋለች። ለሴቶች መብትም ትታገላለች። በዚምባቤ በጎርጎረሳዉያኑ 1990 ዓ.ም «ኔራይ ፊልም» የተሰኘ የፊልም ሥራ ኩባንያንም የመሰረተች ናት። 
ዚምባቤዊትዋ ደራሲ ፂሲ ለአንባብያን ባቀረበቻቸዉ ድርሰቶች ማለትም በጎርጎረሳዉያኑ 1988 ዓ.ም Nervous Conditions በጎርጎረሳዉያኑ 2006 ዓ.ም The Book of Not በ 2018 ዓ.ም ደግሞ This  Mournable Body በተሰኙ ሥነ-ጽሑፎችዋ እዉቅናን አትርፋለች።  
ደራሲ ፂሲ ዳንጋሬምብጋ በምዕራቡ ዓለም ቤተ-መዘክሮች ውስጥ በሚገኙት እና ከአፍሪቃ በቅኝ ግዛት ዘመን ስለተዘረፉ የአፍሪቃ ቅርስ እና የጥበብ ሥራዎች ዙሪያ በርሊን ላይ በተካሄደው ውይይት ላይ ተሳትፏም ነበር። ደራሲ ፂሲ ዳንጋሬምብጋ በትውልድ አገሯ በዚምባቤ የሚታየዉን ሙስና በመቃወም ንቁ ዘመቻ በማካሄድዋ በጎርጎረሳዉያኑ 2020 ዓ.ም ሐምሌ ወር ላይ የዚምባብዌ መንግስትን በመቃወምዋ አጠር ላለ ጊዜ በቁጥጥር ስር ዉላ ነበር። ከዚህ እስር በኋላ እየተካሄደባት ያለዉን ክስ እስከዛሬ ድረስ እየተከታተለች ነዉ። 
ባለፈዉ ሳምንት ጥቅምት 14 ቀን 2014 ዓ.ም የዚምባብዌትዋ ደራሲ እና ፊልም ሥራ ባለሞያ ፂሲ ዳንጋሬምብጋ  የዘንድሮዉን የጀርመን መጽሐፍ የሰላም ሽልማትን በታዋቂዉ የፍራንክፈርት የመጽሐፍ አዉደ ርዕይ ላይ ተቀብላለች። ደራሲዋ ለዚህ ሽልማት በመብቃትዋ ምን ተሰማት ይሆን? ዶቼ ቬለ ዜምባዊትዋን ደራሲ እና የፊልም ሥራ ባለሞያን በአዉደ ርዕዩ ላይ አግኝቶ አነጋሮአት ነበር።  
ፂሲ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪቃ ሃገራት የጀርመንን የመጽሐፍ ንግድ የሰላም ሽልማት የተሸለሙ የመጀመሪያዋ አፍሪቃዊት ሴት ኖት። ይህ ለእርስዎ እና ለሌሎች የአፍሪቃ አህጉር ሴት ፀሐፊዎች ምን ትርጉም ይሰጣል ?  ምን ይሰማዎታል? 
«በሽልማቱ ተደንቄያለሁ ተደስቼማለሁ። ለእኔ፣ እዚህ እውቅና እና አድናቆት ደረጃ እስክደርስ ድረስ በጣም ረጅም መንገድን ተጉዣለሁ። በዚህም መክንያት ምስጋናዬ እጥፍድርብ ነው። እንደኔ አንድ ሰው ስራውን በጥሩ ሁኔታ ሲሰራ እና ሲሳካለት ብሎም የጥሩ ስኬት እና እውቅናን ሲያገኝ ሌሎች ሰዎችን የሚያበረታታ ይመስለኛል»  
የዚምባቤ የረዥም ጊዜ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ከስልጣን ከተወገዱ እና በምትካቸዉ ኤመርሰን ምናንጋግዋ በጎርጎረሳዉያኔ 2017 ስልጣን ከጨበጡ በኋላም ትውልድ ሀገርዎ ዚምባብዌ ዛሬም በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች። ህዝቡ በማህበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እንዲሁም በሰብአዊ መብት ጥሰቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰቃየ ይገኛል። በተለይ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በተመለከተ በዚምባቤ ሁኔታው ምን ያህል አስቸጋሪ ነው ይላሉ? 
«ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በሁለት መንገድ አየዋለሁ። እንደኔ ሃሳብ በተለምዶ በሚታሰብበት መንገድ ማለትም አንድ ሰው አንድ ነገር ሲናገር ይህ አገላለጽ ምን መዘዝ ያስከትልበታል፤ የሚለዉ ነዉ።  ስለዚህ በርግጥም ሀሳብን በነፃነት መግለጽ ላይ ጭቆና እና ጫና አለብን። በዚምባብዌ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት አለ። ነገር ግን ሃሳብን ከገለፅን በኋላ ነፃነት የለም የምንለዉ ቀልድ አለን። ስለዚህ ሰዎች
አንዳንድ ነገሮችን ከተናገሩ፤ ከመንግሥት የሚመጡ መዘዞች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያውቃሉ። ወይም ደግሞ መንግሥት ስለ ጉዳዩ ያዉቃል። ብዙዉን ጊዜም ይህን ጉዳይ ይከታተላል። ምክንያቱም ሰዎች ስለሚያደርጉት እና ስለሚናገሩት ነገር መንግሥት እንዲያዉቅ የሚፈልጉ ሰዎችም ስላሉ ነዉ። ለኔ ሌላ ዓይነት ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት አለ ብዬ አምናለሁ። ይህ ማለት አንድ ሰው እራሱን መግለጽ የሚችለው አቅም ሲኖረው ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱ እየታየ ነዉ። በዚምባቤ ብዙ ሰዎች ሃሳባቸውን ለመግለጽ በማህበራዊ ሚዲያ መሄድ አይችሉም። ምክንያቱም በሃገሪቱ የኢንተርኔት መጠቀምያ እጅግ ዉድ በመሆኑ ነዉ። ሥነ-ጽሑፍ እና ህትመት ብዙ ጊዜ እና ገንዘብን ይፈልጋል። በዚምባብዌ ያለዉን ቀውስ እና ሰዎች በየእለቱ የህልውና መሰረታዊ ጉዳዮቻቸዉን ለማግኘት መቻኮል ላይ በመሆናቸዉ የሚፈልጉትን ለመፃፍ እና በሰላም እና በጥሞና ለማሰላሰል፤እንዲሁም ለመዝናናት ጊዜ የላቸውም። ፊልም መስራት በዚምባቤ የበለጠ ከባድ ነው። ምክንያቱም ዘርፉ አሁን አሁን ብዙ የገንዘብ ምንጭን በመጠየቁ ነዉ። ዚምባብዌ ውስጥ ያሉ የገንዘብ ምንጮች ሁሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር ናቸው። 
በአንድ ወይም በሌላ መንገድ፤ ሁሉም የንግድ ድርጅቶች በመንግሥት መዝገብ ላይ መፃፍ አለባቸው። ስለዚህ፣ ምናልባት የፈጠራ ትረካዎችን ለመደገፍ የሚፈልጉ ትልልቅ ኩባንያዎች የትኞቹን ትረካዎች ወይም ጽሑፎች እንደሚደግፉ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። እነዚህ ኩባንያዎች መንግስትን የማይደግፉ ትረካዎች ወይም ጽሑፎች ከሆኑ ችግር ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ስለዚህ ሰዎች፣ ሀብትን ለመጠቀም የተነፈጉ በመሆናቸው በዚምባቤ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት የለም በሚባልበት ደረጃ ላይ እንገኛለን። »  
ይህአይነቱ ሁኔታ በስራዎ ላይተጽዕኖ አሳድሮአል ይላሉ? 
«አዎ፣ ሁኔታው በሥራዬ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። በእውነቱ፣ ለዚህም ነው፣ ለብዙ ዓመታት የራሴን ፊልም ሳላዘጋጅ ወይም ሳልሰራ የቆየሁት። በጽሑፍም ቢሆን ተመሳሳይ ሁኔታ ነዉ። ብዙ አልፃፍኩም። ፂሲ ዳንጋሬምብጋ በሦስት አስርተ ዓመታት ዉስጥ የፃፈችዉ ሦስት መጽሐፍትን ነዉ። 
እራስን ለማዳን እና ለመቻል፣ በጠረጴዛው ላይ የሚበላ ምግብ መኖሩን ለማረጋገጥ ብዙ ነገር መስራት ያስፈልጋል።  በሚፈልገው ሰላምና ጸጥታ ለመቀመጥ እና ለመፃፍ የሚያስችል ቦታ የለኝም።  
ሰዎች አሁንም ትረካዎችን ለመፃፍ ፍላጎት አላቸው። ነገር ግን የሃገሪቱ የህትመት ኢንዱስትሪ ከሌሎች የአገሪቱ ኢንዱስትሪዎች እና በእርግጠኝነት የፈጠራ ኢንዱስትሪዎች ጋር ወድቋል።  
በዚምባብዌ አሁንም ድረስ እየሰሩ ያሉ ኢንዱስትሪዎች በጣም ጥቂት ናቸው። ስለዚህ በዚምባብዌ ውስጥ ለሚኖር ማንኛውም ወጣት በጽሁፍ ሥራ ላይ ለመሰማራት ማሰብ በጣም ከባድ ነው። የዚምባቤ ጸሐፍቶች በመፅሃፍ እና በሥነ ጽሑፍ ውስጥ ሊሚሳተፉ በሚችሉባቸዉ ኢንዱስትሪዎች ባሉበት ሃገራት የመሰደድ  አዝማሚያ እየታየባቸዉ ነዉ። በእውነትም በዚምባቤ የሥነ ጽሑፍ እና የመጽሐፍ መድረክ ከመንግስትም ሆነ ከየትኛውም ዘርፍ ድጋፍ እያገኘ አይደለም።  
መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አንዳንድ ጊዜ  መጽሐፍ ያሳትማሉ። መጽሐፉ ልብ ወለድ ሊሆን ይችላል፣ ግን በአብዛኛዉ በልማት ትረካ አውድ ውስጥ ያለመጽሐፍን ነዉ የሚያሳትሙት።  መፍታት ያለብን ይህን ችግር ነዉ።  ስለዚህ ዚምባቤ ዉስጥ በአሁኑ ወቅት ሰዎች በሥነ-ጽሑፋዊ ፈጠራ ውስጥ መሳተፍ ወይም የሚነበብ መጻሕፍትን ማግኘት በጣም ከባድ ሆኖባቸዋል። 
በዚምባቤ በበለጠ ነፃነት፣ በበለጠ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን በመስራቶ እና በመታገሎ ለእስር ተዳርገዋል። መስከረም ላይ  ፍርድ ቤት ቀርበዉ ነበር። ለተከታይ ችሎት በሚቀጥለዉ ታህሳስ ወር ፍርድ ቤት መቅረብ ያስፈልግዎታል። ሁኔታው ለእርስዎ ምንያህል አደገኛ ነው ይላሉ? 
በዚምባብዌ የኔ ጉዳይ አሳሳቢ የሚባል አይደለም። አዎ ባለፈው ዓመት ሁለት ፖስተሮች ላይ መፈክሮችን ጽፊ እና ከጓደኛዬ ጋር ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ አደባባይ በመዉጣቴ ታስሬ ነበር።   
ለተደጋጋሚ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርቤም ነበር። ከአሁኑ ጋር ጨምሮ አስር ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርቤያለሁ።  መንግሥት ግን ክስ ለመመስረት እስካሁን ዝግጁ አይደለም።  የፊታችን ታህሳስ 15 ሌላ የፍርድ ቤት ቀጠሮ አለኝ በቀጣይ የምናየዉ ይሆናል።»

Frankfurt am Main | Frankfurter Buchmesse - Tsitsi Dangarembga, Trägerin des Friedenspreises des Deutschen Buchhandels 2021
ምስል Sebastian Gollnow/dpa/picture alliance
Buchcover Nervous Conditions   Tsitsi Dangarembga
Buchcover This Mournable Body  Tsitsi Dangarembga
ምስል Graywolf Press
Simbabwe | Coronavirus | Protest
ምስል Zinyange Auntony/AFP

ታንዛንያዊዉ ደራሲ አብዱልራዛቅ ጉርናህ የዘንድሮዉን የስነፅሑፍ የኖቤል ሽልማት ማሸነፋቸዉን ተከትሎ ዜምባቤዊትዋ ደራሲ ዓለም ለአፍሪቃ ሥነ-ፅሑፍ መድረክዋን እየከፈተች መሆንዋን ደራሲዋ ተናግራለች።  
እንደ ጎርጎረሳዉያን አቆጣጠር በ 1980 ከዚምባቤ ነፃነት በኋላ ፣ በሃገሪቱ ብዙ ጥሩ እና ገለልተኛ አሳታሚዎች እና የመጻሕፍት መደብሮች ነበሩ። ምርጥ ከሚባሉት መፅሐፍት አዉደ ርዕዮች አንዱ ምናልባትም በአፍሪቃ ምርጡ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ የተካሄደው በሐራሬ ነበር። ያ ዛሬ የለም።  ዚምባቤ ዉስጥ በአሁኑ ጊዜ መጽሐፍትን በቀላሉ ማግኘት ምን ያህል ከባድ ነው ይላሉ?  
«በዚምባብዌ የሚነበብ መጽሐፍን  ማግኘት በጣም ከባድ ነው። የሚነበቡ መጻሕፍት ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ ይቀረጣሉ!። በጣም ውድ ገንዘብ ይከፈልባቸዋል። በጣም ጥቂት ሰዎች መጽሐፍትን ለመግዛት አስፈላጊ የሚባሉ የክሪዲት ወይም የብድር መክፈያ ካርዶች አላቸው።  እና በእውነቱ በሃገሪቱ የሚያነቡ ሰዎች ከጊዜ ወደጊዜ እያነሱ እና እያነሱ መሄዳቸዉ እየታየ ነው።    
የዚምባቤ የረዥም ጊዜ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ከስልጣን ከተወገዱ እና በምትካቸዉ ኤመርሰን ምናንጋግዋ በጎርጎረሳዉያኔ 2017 ዓመት ስልጣን ከጨበጡ በኋላም ትውልድ ሀገርዎ ዚምባብዌ ዛሬም በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች። ህዝቡ በማህበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እንዲሁም በሰብአዊ መብት ጥሰቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰቃየ ነዉ።  በተለይ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በተመለከተ በዚምባቤ ሁኔታው ምን ያህል አስቸጋሪ ሆንዋል። 
የዘንድሮ የጀርመን መጽሐፍ  የሰላም ሽልማት አሸናፊ ዚምባቢዊትዋ ደራሲና እና የፊልም ስራ ባለሞያ ፂሲ ዳንጋሬምብጋ ያገኘችዉ ሽልማት እዉቅናን ጨምሮ 25 ሺህ ይሮ አስገኝቶላታል። በጀርመን ሃገር  በሚካሄዱ በአብዛኛዉ የመጽሐፍ አዉደርዕዮች ላይም የክብር ተጋባዥ ናች።  የዚምባቤ ታዋቂ ደራሲ እና የፊልም ሥራ ባለሞያን በተመለከተ  የተጠናቀረዉን ዝግጅት ለማድመጭ የድምፅ ማድመጫዉን በመጫን ይከታተሉ!
አዜብ ታደሰ 
እሸቴ በቀለ 
 

Simbabwe | Coronavirus | Protest
ምስል Zinyange Auntony/AFP