1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በውጭ የሚኖሩ ለወገን ደራሽ ኢትዮጵያውያን

ማክሰኞ፣ ግንቦት 3 2013

በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በሚደርሱ ግጭቶች ቤተሰቦቹን ያጣውን፣ የተፈናቀለውን፣ንብረቱ እንዳልነበረ የሆነውንና ባዶ እጁን የቀረውን ወገን ለማገዝ በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የእርዳታ እጃቸውን ከመዘርጋት ተቆጥበው አያውቁም።

https://p.dw.com/p/3tGK2
Äthiopien Hilfe von 'Verband der Äthiopier in der Schweiz'
ምስል Verband der Äthiopier in der Schweiz

ድጋፍ በአውሮጳ ከሚኖሩ የኢትዮጵያውን ሁለት ማኅበራት

ባለፈው ወር በአጣዬ ከተማ እና አካባቢው በደረሰው ጥቃት ለተፈናቀሉ፣ ንብረታቸው ለወደመና በተለያዩ ችግሮች ላይ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ካላቸው ያካፈሉ ሁለት በአውሮጳ የሚገኙ የኢትዮጵያውያንና የትውልደ ኢትዮጵያውን ማኅበራትን በዚህ ዝግጅታችን እናስተዋዉቃለን።  

በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በሚደርሱ ግጭቶች ቤተሰቦቹን ያጣውን፣ የተፈናቀለውን፣ንብረቱ እንዳልነበረ የሆነውንና ባዶ እጁን የቀረውን ወገን ለማገዝ በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የእርዳታ እጃቸውን ከመዘርጋት ተቆጥበው አያውቁም።ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ሰራሽም ሆነ የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ የአቅማቸውን ከመርዳት የማይቦዝኑት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በቅርቡ በአጣዬና አካባቢው በደረሰው ጥቃት ሰበብ ችግር ላይ የሚገኙ ወገኖችን ለመርዳት በግልም በማኅበርም የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ ነው። ከመካከላቸው በስዊትዘርላንድ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የመሰረቱት «እኔም ለወገኔ የበጎ አድራጎት ማኅበርና በምዕራብ ጀርመኖቹ በኮሎኝና በቦን ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያቋቋሙት የኢትዮ ጀርመን ሙስሊሞች ማኅበር ያበረከቱት እርዳታዎች ይገኙበታል።

አቶ ቴዎድሮስ ተክለ ጊዮርጊስ «የእኔም ለወገኔ የበጎ አድራጎት ማኅበር» የቦርድ ሰብሳቢ ናቸው።  ይህ የኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ስዊዝ አቀፍ ማኅበር የአሁኑን መጠሪያውን ይዞ በበስዊዘርላንድ መንግሥት ተመዝግቦ መስራት ከጀመረ አንድ ዓመት ሊሆነው እንደሆነ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።በዚህ አንድ ዓመት ውስጥም ድርጅታቸው ኢትዮጲያ ውስጥ ልዩ ልዩ ችግሮች ለደረሱባቸው ወገኖች  እርዳታዎችን አቅርቧል።በቅርቡም አጣዬ በደረሰው ጥቃት ለተጎዱ ወገኖች የሚሰጥ እርዳታም አሰባስቧል።

EU Flagge
ምስል picture-alliance/NurPhoto/N. Economou

ይህ ማኅበር ከመመስረቱ በፊት በተለያዩ የስዊትዘርላንድ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባቋቋሟቸው የተለያዩ ማኅበራት አማካይነት ልዩ ልዩ እርዳታዎችን ወደ ሃገራቸው ሲልኩ መቆየታቸውንም አቶ ቴዎድሮስ አስታውሰዋል።24 ቋሚ አባላት ያሉት የበጎ አድራጎት ድርጅቱ በዋትስ አፕ መልዕክት መለዋወጫ መድረኩ 250 ተሳታፊዎች አሉት። በዚህ መድረክ አማካይነትም የእርዳታ ጥሪዎችን ያስተላልፋል።ሌላው ከተቋቋመ ሰባት ዓመታት ያስቆጠረውና ከ2013 ዓም ጀምሮ በጀርመን መንግሥት የተመዘገበው«የኢትዮ ጀርመን ሙስሊሞች ማኅበር»ም ተመሳሳይ የበጎ አድራጎት ስራ እያከናወነ ነው።በቅርብ ጊዜው የአጣየው ግጭት ብዙ የተፈናቀሉ ወገኖች መኖራቸውን የሰሙት የማኅበሩ አባላት ከኪሳቸውም ከሌሎችም ገንዘብ አሰባስበው በሮመዳን ጾም እርዳታ ለሚያሻቸው ወገኖች አስፈላጊ ያሉትን መላካቸውን አቶ ሰዒድ አህመድ የማኅበሩ የእርዳታ አስተባባሪ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።

ይህ ማኅበሩ ለአምስተኛ ጊዜ ኢትዮጵያ ለሚገኙ ወገኖች እጁን የዘረጋበት እርዳታ ነው። አቶ ሰዒድ አህመድ ወደ 60 ያህል ቤተሰቦችን ያሰባሰበው ማኅበሩ ቀደም ባሉት ዓመታት የድሬዳዋ የጎርፍ አደጋ ሰለባዎችን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎችም ችግር ላይ ለወደቁ ወገኖችም ካለው ማካፈሉንም ተናግረዋል።የአሁኑ እርዳታም እዚያ በሚገኙ ሰዎች አማካይነት እንዲደርስ ነው የተደረገው።

የአማራ ክልል እንዳስታወቀው ባለፈው ወር በከሚሴና አጣዬ በደረሱ ጥቃቶች ከ328 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል። ከቅርብ ዓመታት  ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ እዚህም እዚያም በሚከሰቱ ግጭቶች የሚደርሱ ግድያዎች ፣የንብረት ጥፋትና የሰዎች መፈናቀል ውጭ የሚገኘውን ኢትዮጵያዊ ልብ የሚሰብርና እጅግ የሚያሳዝንም መሆኑን ነው የበጎ አድራጎት ማኅበራቱ ተወካዮች የገለጹት ።

አቶ ቴዎድሮስም የወገንን ሞት ስቃይና መፈናቀል ፣ከሩቅ ሆኖ ማየትና መስማት እጅግ ከባድ መሆኑን ነው የተናገሩት

አቶ ቴዎድሮስም ሆነ አቶ አቶ ሰዒድ በኢትዮጵያ በየአቅጣጫው የሚጣሉ ጥቃቶችን አስቀድሞ በመከላከል መንግሥት የዜጎቹን ደህንነት በማስጠበቅ የበኩሉን ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ ከመንግሥት የሚጠበቅ ሲሆን በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከሩቅ ሆነው ግጭቶችን ከማባባስ እንዲቆጠቡ አቶ ቴዎድሮስ መክሯል። እነርሱን ከመሰሉ ማኅበራት ልምድ በመውሰድ «50 ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡ» እንደሚባለው ለግብረ ሰናይ ተግባራት እንዲተጉም ጥሪ አስተላልፏል። አቶ ቴዎድሮስና አቶ ሰዒድ ችግር ላይ የወደቁትን ወገኖች በዘላቂነት ማቋቋሙ የተሻለው መፍትሄ ነው ሲሉም ሃሳብ አቅርበዋል።

 

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ