1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በወለጋ አሁንም ሰዎች እየሞቱ ነው - የምክር ቤት አባል

ሐሙስ፣ ኅዳር 13 2011

በኦሮሚያ ክልል ዉስጥ ባለፈዉ መስከረም አጋማሽ የተጀመረዉ ግጭት እና ግድያ አሁንም አለመብረዱን ከአባቢዉ የተወከሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አስታወቁ። የምክር ቤት አባሉ አቶ ወርዶፋ በቀለ ዛሬ ለ«DW» እንደተናገሩት በምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች ውስጥ አሁንም ሰዎች እየተገደሉ፤ እየቆሰሉ እና እየተፈናቀሉ ነዉ።

https://p.dw.com/p/38k2l
12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

አሳሳቢዉ የምስራቅ ወለጋ ግጭት  

የአሮሚያ ክልልን ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች በተቀሰቀሰ ግጭት ሰዎች እየሞቱ መሆናቸውን አንድ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ለDW ገለጹ። በሺህዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው በችግር ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል። 

በምስራቅ ወለጋ የምትገኘውንን የጊዳ ሲረም ወረዳን ወክለው የተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ዎርዶፋ በቀለ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ከአንድ ወር በፊት የተቀሰቀሰው ግጭት አሁንም አልበረደም ብለዋል። የሁኔታውን አሳሳቢነት በዛሬው የምክር ቤት ስብሰባ ላይ ያነሱት አቶ ዎርዶፋ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢን ሹመት ለማጸደቅ በቦታው የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል። እርሳቸው በተመረጡበት አካባቢ በትላንትው ዕለት በደረሰ ጥቃትም ሰዎች መሞታቸውን ለDW ተናግረዋል። 

በኦሮሚያ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ከዚህ ቀደምም በመሬት እና የግጦሽ ቦታ ይገባኛል ግጭቶች ይስተዋሉ እንደበር አቶ ወርዶፋ ያስታውሳሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋሉ ግጭቶች ግን በታጠቁ ኃይሎች የሚፈጸሙ እንደሆኑ ከአካባቢው መረጃ ደርሶኛል ይላሉ።  

ግጭቱ በተለይ የጠናው በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ባሉ አካባቢዎች ቢሆንም ምዕራብ ወለጋም የችግሩ ተጠቂ መሆኑን አቶ ወርዶፋ ይናገራሉ። በግጭቱ ምክንያትም ከጊዜ ወደ ጊዜ የህዝብ መፈናቀል እየጨመረ መጥቷል ብለዋል። በምስራቅ ወለጋ ዞን ጎሶ ጊዳ ወረዳ በተለይ ሻሺጋ በሚባል ቦታ፣ በዚያው ዞን ሊሙ ወረዳ እና በምዕራብ ወለጋ መና ሶጉ ወረዳ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው መፈናቀሉን ገልጸዋል።  

በምስራቅ ወለጋ ዞን የጎሶ ጊዳ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ዲጲሳ በሚመሩት ወረዳ ብቻ ከአራት ሺህ በላይ ህዝብ ተፈናቅሎ በድንኳን ተጠልሎ እንደሚገኝ አስረድተዋል። በአካባቢያቸው አሁን ግጭቱ ጋብ ቢልም በጸጥታ ስጋት ምክንያት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ እንዳልቻሉም ገልጸዋል። እንደ አቶ ደሳለኝ ገለጻ በወረዳቸው በየድንኳኑ ለተጠለለዉ ተፈናቃይ የአካባቢዉ ሕዝብ ከሚሰጠዉ በስተቀር ከመንግሥት የደረሰ እርዳታ የለም።  

(ሙሉ ዘገባውን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።)

ተስፋለም ወልደየስ 

አዜብ ታደሰ