1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

በኮሮና ወቅት የተዘነጉት የልብና የኩላሊት ታካሚዎች «ስለ ልብ ከልብ አድምጡን»

ማክሰኞ፣ ሰኔ 23 2012

በኮሮና ወረርሽኝ በዓለም ላይ  ከአስር ሚሊዮን በላይ ሰዎች በተዋህሲው የተያዙ ሲሆን  ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ  ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏልይህ ወረርሽኝ ከጤና ችግርነቱ ባሻገር ዘርፈ ብዙ ችግሮችንም እየፈጠረ ይገኛል።ከነዚህም አንዱ ለሌሎች በሽታዎች የሚሰጠውን ትኩረት መቀነሱ ነው።

https://p.dw.com/p/3ebCt
16.07.2015 Fit und Gesund Niere
ምስል Colourbox

በጎርጎሪያኑ ታህሳስ 2019  ዓ/ም በቻይና የጥቂት ሰዎች የጤና ችግር የነበረው  የኮሮና ወረርሽኝ  በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም የሚሊዮኖችን በር እያንኳኳ ይገኛል።ይህ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ከተከሰተ ካለፈው ሚያዚያ ወዲህም  በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህመም በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎችን ደግሞ ለሞት ዳርጓል። ከዚህ በተጨማሪም ኮቪድ-19  የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን በመፍጠር እንዲሁም ለሌሎች በሽታዎች የሚደረገውን ትኩረትና እገዛ እንዲቀንስ በማድረግ እያሳደረ ያለው ተፅዕኖም ቀላል አይለም።ይህ ተፅዕኖ የዳበረ የጤና ስርዓት ያላቸው ሀገራትን ሳይቀር አቅም የፈተነ ሆኗል። እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ቀድሞውንም የጤና ስርዓታቸው ደካማ በሆኑ ሀገራት ደግሞ ጉዳቱ ዘርፈ ብዙ ነው።በሀገር በቀል በጎ አድራጊዎችና በውጭ ሀገር የዕርዳታ ተቋማት ድጋፍ ሲደረግላቸው የነበሩ የማኅበረሰብ የጤና ተቋማት ተፅዕኖ ካረፈባቸው መካከል ናቸው።በዛሬው የጤናና አካባቢ ዝግጅት በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ድጋፍ ከተቋረጠባቸው ተቋማት ውስጥ  ሁለቱን እንዳስሳለን።


በ1981 ዓ.ም. በዶክተር በላይ አበጋዝ የተመሰረተው የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማኅበር  ላለፉት 30 ዓመታት የልብ ህሙማንን በተለይም ህፃናትን በነፃ የቀዶ ጥገናና ሌሎች ህክምናዎችን ሲያከናዉን ቆይቷል። ይህ የህክምና ማዕከል  80 በመቶ የሚሆኑት ታካሚዎቹ ህፃናት ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት  የልብ ቀዶ ሕክምና የሚፈልጉ ከሰባት ሺህ  በላይ ሕሙማን ተራቸውን  እየተጠባበቁ ይገኛሉ።ማዕከሉ በዋናነት ከሀገር ውስጥና ከውጭ ለጋሾች በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ የተገነባ ሲሆን የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶክተር ሄለን በፈቃዱ እንደሚሉት የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ  ድጋፉ በመቋረጡ ማዕከሉ ፈተና ገጥሞታል።

Symbolbild | Arztpraxis, Ärztin erklärt Patient die Funktionsweise und mögliche Erkrankungen des menschlichen Herzens
ምስል picture-alliance/dpa/imageBROKER


«በማዕከሉ የነበረበትን የገንዘብና የአላቂ ዕቃእጦት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅረፍየተለያዩ የህዝብ ግንኑነት ስራዎችን ላለፉት አንድ አመት ከስድስት ሲሰራ ቆይቷል።ወረርሽኙ ከመምጣቱ በፊት የተሻለ ተስፋ ሰጭ የሚባል እንቅስቃሴ ነበር።በውጭም በሀገር ውስጥም።አሁን ግን ባለፉት ሶስትና አራት ወራት በተለይ ኮቪድ-19 ወደ ሀገራችን ከገባ በኋላ ማዕከሉ ላይ ተፅዕኖ ማምጣቱ በዋናነት በዘላቂነት ሊንሰራ ካሰብነው የቀዶ ጥገና ጋር ወረፋ ከሚጠባበቁ ህፃናት ቁጥር አንፃር ስናየው የወረርሽኙ ተፅዕኖ ቀላል የማይባል ነው።»
የኮሮና ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት ማዕከሉን በገንዘብ ለመደገፍ በኢትዮ ቴሌኮም በኩል አስር ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ  ታቅዶ የተጀረው የገቢ ማሰባሰቢያ አንድ ሚሊዮን ብር የሞላ ገንዘብ ሳይሰበሰብ  በኅብረተሰቡ የሚደረገው ድጋፍ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መቋረጡንም ገልጸዋል።ከዚህ በተጨማሪ ከውጭ የሚመጡ የበጎ ፈቃድ ሀኪሞችና ይዘዋቸው ይመጡ የነበሩ መድሃኒቶች እንዲሁም የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ በመቋረጡ ህክምና ለማግኘት የሚጠባበቁ የልብ ህሙማንና የማዕከሉ የዕለት ተዕለት ስራ ችግር ላይ ይወድቃል የሚል ስጋት አላቸው።  
በሌላ በኩል ማዕከሉ ለታካሚዎቹና ለቤተሰቦቻቸው  የተለዬ የማረፊያ ቦታ ለማዘጋጀት አቅም ባለመኖሩ ከሩቅ አካባቢ የሚመጡ ታካሚዎች በሆቴል ወይም ዘመድ ጋ  ሆነው ለመታከም ለተዋህሲው ከፍተኛ  ተጋላጭ በመሆናቸው በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱን ለማግኘት የሚቸገሩ መኖራቸውን ዶክተር ሄለን  አመልክተዋል።ማዕከሉ በዓመት ከአንድ ሺህ በላይ ለሆኑ የልብ ታማሚ ሕፃናት የቀዶ ሕክምና አገልግሎት የመስጠት አቅም ቢኖረውም  በድጋፍ ማጣት በዓመት ለ450  ሕፃናት ብቻ  ሕክምና ሲሰጥ  ቆይቷል ።በአሁኑ ወቅት ደግሞ የኮቪድ-19 በፈጠረው ተፅዕኖ ድጋፍ በመቋረጡ ከዚህ በፊት በማዕከሉ  ይስተናገዱ የነበሩ  በቀን ከ40 እስከ 50  ተመላላሽ ታካሚዎች ቁጥራቸው ወደ ሃያ ወርዷል።አገልግሎት ይሰጥባቸው የነበሩ የስራ ቀናትም ወደ ሶስት ዝቅ እንዲሉ ተደርጓል።የልብ የቀዶ ጥገና ህክምናም በግማሽ ቀንሷል።


«ከዚህ በፊትባለው በሳምንት አምስት ወይም ስድስት የቀዶ ጥገና ለመስራት በዚያጥረት እያደረግን ነበር።አሁን ላይ ቀዶ ጥገና በሳምንት ሶስት የልብ «ካስተራይዜሽን» የሚባለው በሽቦ ከፍቶ የጠበበ የልብ ቧንቧንና የተከፈተ የልብ አካልን የሚዘጋበት በሳምንት አንድ ወይም ሁለት በዛ ከተባለ ሶስት እንሰራለን።ከዚህ በፊት ግን አልሰራንም ከተባለ በሳምንት ስድስት እንሰራ ነበር።በአጠቃላይ በ50 ፐርሰንት አካባቢ አገልግሎቱ ቀንሷል ብለን ነው የምናምነው።» የልብ ማዕከሉ አገልግሎት ከሰጠባቸው 30 ዓመታት ውስጥ የመጀመርያዎቹን 20 ዓመታት ዘውዲቱ ሆስፒታል ውስጥ በአንድ አነስተኛ ክፍል የቆየ ሲሆን ከአሥር ዓመታት ወዲህ ደግሞ‹‹አንድ ብር ለአንድ ልብ›› በሚል የገቢ ማሰባሰቢያ  ዘመቻ በኅብረተሰቡና በአጋር ድርጅቶች ድጋፍ ጥቁር አንበሳ  ሆስፒታል ውስጥ የልብ ሕሙማን ሕፃናት ሕክምና ማዕከልን  ገንብቷል።በእነዚህ አስር ዓመታት 5600 ለሚሆኑ ህጻናት በነፃ የልብ ቀዶ ጥገና ማካሄዱን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።ለአንድ የልብ ቀዶ ጥገና በትንሹ  ከሶስት እስከ አራት መቶ ሺብር ያስፈልጋል የሚሉት ዶክተር ሄለን ፤ወደ ውጭ ሄደው መታከም የነበረባቸውን ህፃናት በሀገር ውስጥ እንዲታከሙ በማድረግ የታማሚዎቹን ህይወት ከማትረፍ በተጨማሪ  ሀገሪቱን ከውጭ ምንዛሬ ማዳኑንም አስረድተዋል።በመሆኑም ይህ ብቸኛ የሀገርና የህዝብ ተቋም ሙሉ ለሙሉ ስራ ከማቆሙ በፊት  የተገነባውና የሚንቀሳቀሰውም በኅብረተሰቡ ድጋፍ በመሆኑ  «ስለ ልብ  ከልብ አድምጡን» በማለት እገዛ ጠይቀዋል።

Pakistan Muhammad Iqbal, Nierenspender
ምስል DW/R. Aslam


የኮሮና ወረሽኝ ስርጭት በኩላሊት ህመምተኞች ላይም ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ እየተነገረ ነው።«ሞት በኩላሊት ይብቃ» የተባለው ማህበር መስራችና ስራ አስኪያጅ  አቶ እዮብ ተወልደ መድህን እንደሚሉት የኮሮና ወረርሽኝ  የሁሉንም ቀልብ መሳቡ እንደ ኩላሊት ያሉ ተዛማጅ ህመሞችና ህመምተኞች ተዘንግተዋል። ማኅበሩ ላለፉት አራት አመታት ስለ ኩላሊት በሽታ ግንዛቤ በመስጠትና  አቅም ለሌላቸው ታማሚዎች የህክምና  ገንዘብ ከበጎ አድራጊዎች እንዲረዱ በማድረግ እየሰራ ያለ የኩላሊት ታማሚዎች ማኅበር ነው። ከበጎ አድራጊ ድርጅቶችና ግለሰቦች በሚገኝ ድጋፍ በማኅበሩ አማካኝነት ለ140 የኩላሊት ህመምተኞች የዲያሊሲስ ህክምና እድዲያገኙ እየተደረገ ቢሆንም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ችግር እንደገጠመው አቶ እዮብ ጨምረው ገልፀዋል። የኩላሊት ህመም ተጠቂ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ እዮብ እሳቸው ከፍለው በሚታከሙበት የመንግስት የህክምና ተቋም እንኳ የአቅርቦት እጥረት ተፈጥሯል በሚል ህክምና የሚያገኙበት ቀን ከሶስት ወደ ሁለት ቀናት ዝቅ ብሏል። በመሆኑም ለኮሮና ወረርሽኝ የሚደረገው ርብርብ እንዳለ ሆኖ ለኩላሊት ህመምተኞችም ይሁን ለሌሎች ተጓዳኝ በሽታዎች ተገቢው ድጋፍና ትኩረት ከመንግስትም ከህብረተሰቡም አይለየን ሲሉ አሳስበዋል።


ፀሀይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ