1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«በክልሉ ወንጀል እየጨመረ ነዉ» ያለዉ የአማራ ክልል ም/ቤት ስብሰባ

ሐሙስ፣ የካቲት 30 2015

በአማራ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት በማህበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፎች የተሸለ አፈፃፀም የታየ ቢሆንም የወንጀል ድርጊት ግን እየጨመረ መምጣቱ ተገለጠ፣ የርዕሰ መስተዳድሩ ሪፖርት ክልሉ መደበኛ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች እንዲቀጥሉ የሚያመለክት መሆኑን አንድ ምሁር አመልክተዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4ORjS
Amhara regional parliament holds meeting in Bahr Dar
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

«በክልሉ ወንጀሎች እየተወሳሰቡና መልካቸውን እየቀየሩ መጥተዋል» የም/ቤቱ የህግና ፍትህ አስተዳደር

በአማራ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት በማህበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፎች የተሸለ አፈፃፀም የታየ ቢሆንም የወንጀል ድርጊት ግን እየጨመረ መምጣቱ ተገለጠ፣ የርዕሰ መስተዳድሩ ሪፖርት ክልሉ መደበኛ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች እንዲቀጥሉ የሚያመለክት መሆኑን አንድ ምሁር አመልክተዋል፡፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን፣ 5ኛ መደበኛ ጉባኤ ከትናንት ጀምሮ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው፡፡ ለምክር ቤቱ የ6 ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ በኢኮኖሚ፣ በመሰረተ ልማት፣ በማህበራዊ፣ በፍትህና መልካም አስተዳደር በበጀትና በልማት ስራዎች መልካም አፈፃፀሞችን መመዝገባቸውን አብራርተዋል፡፡

ሆኖም በወንጀል መከላከል ረገድ አሁንም የሚቀሩ ስራዎች መኖራቸውን ያመለከቱት ዶ/ር ይልቃል በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ “በክልሉ አጠቃላይ ወንጀል በግማሽ ዓመት ውስጥ 13ሺህ 608 የተፈፀመ ሲሆን የተፈፀመው ወንጀል በወረራ የተያዙ አካባቢዎችን ሳይጨምር ካለፈው ዓመት ተመሳሳ ወቅት ከተፈፀመው 9ሺህ 580 ጋር ሲነፃፀር 4000 ብልጫ ያለው ነው፣ በዋና ወንጀል ተይዘው ክትትል ከሚደረግባቸው ወንጀሎች መካከል ሰው መግደል 1ሺህ 115፣ ሰው ማገት 83፣ መኪና አስቁሞ ዘረፋ 8፣ 5ሺህ 597 ህገወጥ የሰዎች ዝውውወር ከፍተኛ የወንጀል ድርጊቶች የነበሩ ሲሆን ከባለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር እየጨመረ የመጣ በመሆኑ በቀጣይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል፡፡” ብለዋል፡፡

የምክር ቤቱ የህግ ፍትህና አስተዳደር ቃሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ወርቅነህ እንደግም በክልሉ የወንጀል ድርጊቶች እየተወሳሰቡና መልካቸውን እየቀየሩ መምጣታቸውን ለምክር ቤቱ ተናግረዋል፡፡

“የሰው ማገት ወንጀል እንዲሁም በህፃናትና በአዋቂ ሴቶች የሚፈፀም ወንጀል ያልተለመደና የወንጀል ድርጊት እየሆነ መጥቷል፣ በበጀት ዓመቱም ችግሩን ለማስቆም የተለያዩ ግቦች ተጥለው ርብርብ እየተደረገ ቢሆንም አፈፃፀሙ የበጀት ኣመቱን እቅድ አለማሳካት ብቻም ሳይሆን፣ ከባለፉት ወቅት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የወንጀል ሁኔታ እየጨመረ የመጣ ነው፡፡ የሚፈፀሙ ወንጀሎችም ከጊዜ ጊዜ አሳሳቢ የሆኑና የሚፈፀመው ወንጀልም ልተለመደ እሆነ መጥቷል፡፡”

Amhara regional parliament holds meeting in Bahr Dar
የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን፣ 5ኛ መደበኛ ጉባኤምስል Alemnew Mekonnen/DW

ከደቡብ አፍሪካውም ሆነ ከኬንያው ስምምነት በኋላ በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌና ፃግብጂ ወረዳ ነዋሪዎች ከህወሓት ነፃ መሆን ባለመቻላቸው ህዝቡ በችግር ላይ እንደሆኑ የጠቆሙት አቶ ወርቅነህ መፍትሔ በአፋጣኝ ሊበጅለት ይገባል ብለዋል፡፡

“አገራዊ ድርድሩ ከሆነም በኋላ የክልላችን ህዝቦች በተለይም የዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የአበርገሌና ፃግብጂ ወረዳዎች አሁንም በህወሓት የተያዙ በመሆናቸው፣ አሁንም አሰቃቂ ኑሮ ውስጥ ኖራሉ፣ የህዝባችን የቀን ተቀን ጩኸትም አሳዛኝ ሆኗል፣ የተደረገው አገራዊ ስምምነትና ድርድር በተሟላ መንገድ ሊተገበር ይገባል፣ ውጤቱም ለክልላችን ህዝቦች በተለይ ለነዚሁ ዞኖችና ወረዳዎች ሊደርሳቸው ይገባል፣ ስለዚህ በዚህ በኩል ትኩረቱ አሁን ባግባቡ ተሰጥቶ የተጀመረው መፍትሔና ስምምነት ያለመሸራረፍ እንዲተገበር ተገቢ ግፊት ሊደረግ ገባል፡፡” ዶክተር ይልቃል መላው የክልሉ ህዝብ መንግስት ያስቀመጣቸውን የልማትና የሰላም ስራዎች ውጤታማ ሆነው እንዲከናወኑ ከመንግስት ጎን በመሆን ተገቢውን ትብብርና ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የርዕሰ መስተዳድሩን ሪፖርት በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡን የፖለቲካ ተንታኝ ዶ/ር ደሴ ጥላሁን፣ ክልሉ በርካታ የፀጥታ ችግሮች የነበሩበት ቢሆንም አሁን በተሻለ የልማታ ጎዳና ላይ መሆኑን አመላካች መሆኑን ገልጠዋል፡፡ “ርዕሰ መስተዳድሩ ቀረቡት ሪፖርት የሚያመላክተው ክልሉ በተለያዩ የፀጥታ ስጋት ውስጥ ሆኖም በአጭር ጊዜ ሰላምና መረጋጋቱ እያጠናከረ መደበኛ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች እንዲሰሩ የሚደረገውን ርብርብ የሚያሳይ ነው፡፡ የቀረበው ሪፖርት በግብርና፣ በመሰረተ ልማት፣ በማህበራዊ ዘርፍ፣ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የሚያመላክት ነው፣ ሆኖም ግን የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዱ በተያዘለት ጊዜ እንዳፈፀም እዚህም ከዚያም የሚያጋጥሙ የፀጥታ ስጋቶች ያሉ መሆኑን፣ አገራዊ ሁኔታው በቀጥታ ክልሉ ውስጥም ተፅዕኖ የሚያሳድርበት ሁኔታ በሚታይበት ጊዜ ምናልባት ከዚህ በላይ ሰፋፊ ስራዎችን ልንሰራ የምንችልበት እድሎች የነበሩ መሆኑን ማየት ይቻላል፣ የቋሚ ኮሚቴዎችም ግምገማ የሚያሳየው ይህንኑ ነው፣ በአጭር ጊዜ ወደ ሰላምና መረጋጋት የመጣ ሰፋፊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች እየተሰሩ ያሉ መሆናቸውን የሚያሳይ ሪፖርት ነው የቀረበው፡፡”

ምክር ቤት አባላት በርዕሰ መስተዳድሩ ሪፖርት ላይ ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ እየተወያዩበት ሲሆን ዶ/ር ይልቃል ከምክር ቤት አባላት በሚቀርቡ ጥያቄዎችና አስተያቶች ላይ ማጠቃለያ ይሰጡበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ