1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርት

 በከፍተኛ ውጤት የተመረቁት ሴት የገጠር ተማሪዎች

ዓርብ፣ ነሐሴ 10 2011

የዛሬው የወጣቶች ዓለም እንግዶቻችን ዘንድሮ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ዮንቨርስቲዎች የተመረቁ ልጃ ገረዶች ናቸው። ወጣቶቹን ለየት የሚያደርጋቸው  ሴቶች እምብዛም ትምህርት በማይማሩበት ገጠራማ አካባቢ አድገው ከዮንቨርስቲ መመረቃቸው ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸውም ነው። 

https://p.dw.com/p/3NxKX
Äthiopien | Uniabschluss mit Hilfe von Integrated Family Service Organization
ምስል IFSO

በከፍተኛ ውጤት የተመረቁት ሴት የገጠር ተማሪዎች

ሁሉም በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ገጠራማ ቀበሌዎች ተወልደው  እስከ 8ኛ ክፍል እዚያዉ ገጠር የተማሩ ናቸዉ። « ከቤተሰቦቼ አንድ ሰዓት ተኩል ተጉዜ ነበር እስከ 8ኛ ክፍል የተማርኩት»ትላለች ትዕግስት ይመር። ሌሎቹም ሙሉ እና መሠረት በተመሳሳይ ሁኔታ በቀን በአማካይ እስከ 20 ኪሎ ሜትር እየተጓዙ ነው የተማሩት። ስምንተኛ ክፍልን ከአጠናቀቁ በኋላ ግን ትምህርታቸውን እንዴት እንደሚቀጥሉ አያውቁም ነበር። በዛን ወቅት የሚያስተምራቸው አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አገኙ። መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የተቀናጀ የቤተሰብ አገልግሎት ድርጅትን። የዚህ መሥሪያ ቤት መስራችና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ መቅደስ ዘለለው « 30 የተቸገሩ እና ከሩቅ መንገድ የሚመጡ ተማሪዎችን ከወረዳው ጋር በመመልመል ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ሁሉንም ነገር ችለን እንዲማሩ አድርገናል። 30ዎቹም ተማሪዎች ዩንፀርስቲ ገብተው ከነዚህ ውስጥ 16ቱ ዘንድሮ ተመርቀዋል።» ይላሉ ድርጅታቸው እንዴት እነዚህን ልጃገረዶች ለማስተማር እንደወሰነ ለ DW ሲያብራሩ። 

16ቱ ተማሪዎች  ከተለያዩ ዩንቨርስቲዎች የተመረቁ ሲሆን የ22 ዓመቷ ሙሉ እሸቱ ከነዚህ ልጃ ገረዶች አንዷ ናት። የተቀናጀ የቤተሰብ አገልግሎት ለሷም ድጋፍ መስጠት የጀመረው ከ9ኛ ክፍል  አንስቶ ነው። « እኔ በሰዓቱ ከፍተኛ ውጤት ነበረኝ። ቤተሰቦቼ የሰባተኛ ክፍል እያለሁ ነበር ያረፉት። ያኩትም አክስቴ ጋር ነው።» ድርጅቱ ከ 9ኛ ክፍል አንስቶ ድጋፍ ያደረገላቸው ተማሪዎች በኢኮኖሚ ደካማ ከሆኑ ቤተሰቦች የመጡ ብቻ ሳይሆን አብዛኞቹ ከወላጆቻቸው አንዱን ወይም ሁለቱንም ያጡ ናቸው። መሠረት መራዊ አባቷን ያጣችው የ አምስት ዓመት ልጅ ሳለች ነው። « ከእናቴ እና ከወንድሞቼ ጋር ነው ያደኩት። እናቴ ናት ያሳደገችኝ»

Äthiopien | Uniabschluss mit Hilfe von Integrated Family Service Organization
ተመራቂዎቹና የድርጅቱ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ መቅደስ ዘለለውምስል IFSO

አፍሪቃ ውስጥ ትምህርት የሚማሩ ልጆች ቁጥር በቅርቡ ቢጨምርም አሁን ድረስ ሴቶች ከወንዶች ጋር ሲነፃጸር ትምህርት የማግኘት እድላቸው ከወንዶች አናሳ ነው።የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት UNICEF እንደዘገበዉ ከሆነ በተለይ ከሰሀራ በስተ ደቡብ የሚገኙ ሀገራት ይህ ሁኔታ ይስተዋላል። በደቡብ ሱዳን ለምሳሌ 100 ወንዶች በሚማሩበት ትምህርት ቤት ትምህርት የሚያገኙት ልጃ ገረዶች ቁጥር 75 ያህል ነው። ድርጅቱ ባለፈው ዓመት ባወጣው ዘገባ መሠረት በዓለም  34 ሚሊዮን የሚሆኑ ልጃ ገረዶች የአንደኛ ደረጃ ትምህርት እንኳን ያላገኙ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥም ሙሉ ያደገችበት ገጠራማ አካባቢም ሴቶች ለመማር ብዙ እድል አያገኙም። « ብዙ ጊዜ ሴቶች አይማሩም።ያላቻ ጋብቻ ነበር። ብዙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሰአቱ ነበሩ። » ሙሉ ከአዲስ አበባ ዮንቨርስቲ በፊዚክስ ነው የተመረቀችው።  ባመጣችው 3,4 ነጥብም እዛው ዩንቨርስቲ ቀርታ ስራ የማግኘት እድል ገጥሟታል። የሙሉ የወደፊት ህልም የህዋ ተመራማሪ መሆን ነው።

Äthiopien | Uniabschluss mit Hilfe von Integrated Family Service Organization
ምስል IFSO

የአካውንቲንግ ምሩቋ የትዕግስት ይመር የስኬት ሚስጥር ደግሞ  ትምህርት ላይ ብቻ ማተኮር ነው። « መዝናናት አያምረኝም። ከአላማ ውጪ የሚገፋፉኝን የጓደኞች ፈተናን መቋቋም ነበረብኝ» ትላለች። 3,86 ነጥብ አምጥታ የተመረቀችው ወጣት ግን ገና ስራ አላገኘችም። ከወሎ ዮንቨርስቲ 3,96 በማምጣት በማኔጅመንት በማዕረግ የተመረቀችው መሠረት በተቀናጀ የቤተሰብ አገልግሎት ድርጅት ድጋፍ ተምረው ዘንድሮ ከተመረቁት ልጃ ገረዶችም ቀዳሚውን ውጤት ያስመዘገበችው ናት። ለ 23 ዓመቷ ወጣት ይህ አዲስ ነገር አይደለም። « ከአንድ እስከ ስምንት ስማር ከክላስ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ከትምህርታችንም አንደኛ ነበር የምወጣው።»
የተቀናጀ የቤተሰብ አገልግሎት ድርጅት ከተመሰረተ 25 ዓመት ሆኖቷል።በ17 ፕሮጀክቶች ይሰራል።  ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ መቅደስ እንደገለፁልን በተለይ ልጆቹን ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ወጪያቸው ተሸፍኖ እንዲማሩ የተባበራቸው የጣሊያን ድርጅት ነው። ልጃገረዶቹ  ጥሩ ቦታ ደርሰው ማየት ለድርጅቱ መስራች ትልቅ እርካታ እንደሆነ ይናገራሉ።
 

ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ