1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ ከተሞች የቀጠለዉ ተቃዉሞ  

ዓርብ፣ ጥቅምት 14 2012

የኢትዮጵያ መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የኦሮሞ መብት ተሟጋች እና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዋና ዳይሬክተር ጃዋር መሀመድ መኖሪያ ቤት አቅራቢያ ተሰማርተዋል መባሉን ተከትሎ በአብዛኛው የኦሮሚያ ከተሞች ትናንት የተጀመረው ተቃውሞ ዛሬ ሐሙስ ቀጥሎ በትንሹ ዘጠኝ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ነዋሪዎች ተናገሩ ነዉ።  

https://p.dw.com/p/3Rt3Y
Karte Äthiopien Ethnien EN

«በተለያዩ ከተሞች ዛሬም አልበረደም»

የተቃውሞ እንቅስቃሴ በርትቶ ከተስተዋለባቸው አካባቢዎች በአምቦ ከተማ ትናንት ረቡዕ ከሞቱት ሶስት ሰዎች በተጨማሪ ዛሬ ሐሙስ አራት ሰዎች በጥቅሉ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ (DW) ተናግረዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች የሆኑት አቶ በርኤ ገምታ እንደሚሉት በከተማዋ በከተማዋ ከትናንት ጀምሮ ሰባት ሰዎች ሞተዋል።

«ሰዎች ሞተዋል። ማታ እስከ ሁለት ሰአት ሶስት ሰው ሞቷል። ዛሬም እኛ አካባቢ ወደ አራት  ሰዎች ሞተዋል። በየቦታው ተኩስ አለ። ትናንት ሰልፉ ሰላማዊ ነበር። ከትንሽ ጊዜ በኋላ በተኩስ ነው ነገሮች የተበላሹት። ከዚያ በኋላ እስከማታ ድረስ ተኩስ ነበር። ዛሬም ከሁለት ሰአት ተኩል አካባቢ ጀምሮ ተኩስ ነበር። አሁን ከቤት መውጣት አይቻልም። አሁን ከሰአት በኋላ እንግዲህ ትንሽ ቀዝቀዝ ብሏል። በተረፈ ወደ ሆስፒታል እየተሄደ ነው» ሲሉ አቶ በርኤ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ሌላው የአምቦ ከተማ ነዋሪ አቶ ወሰና ፈይሳ እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ በክልሉ ፖሊስ እና ለተቃውሞ በወጡ ሰዎች መሃል በተፈጠረ ግጭት የሰዎች ህይወት አልፏል፤ ሰዎችም ቆስለዋል። «የአምቦ ከተማ ህዝብ ተቃውሞውን ለማሰማት እንደወጣ ነው። ሆኖም ግን ከጸጥታ አካላት ጋር አለመስማማት ነበር። በእርግጥ ፖሊስ ጸጥታን የማስከበር ሃላፊነት አለበት። ህብረተሰቡም ደግሞ የፖሊስን ትእዛዝ መቀበል ነበረበት። ያም ሆነ ይህ ግን ሳይግባቡ ቀርተው በመሃል ላይ ሰዎች እንደቆሰሉ እና በቁጥር የማናውቃቸው ሰዎች መሞታቸውን ያለን መረጃ አለ» ብለዋል።

Äthiopien Proteste | Ambo Town
ምስል DW/M. Yonas Bula

ተቃውሞውን ተከትሎ ወደ አምቦ ከተማ የሚያስገቡትም ሆነ ከከተማዋ የሚያስወጡ መንገዶች ተዘግተው መዋላቸውን ነዋሪዎቹ ጨምረው ተናግረዋል። በከተማዋ ውጥረት መንገሱን ተከትሎ በቤት መቆየትን መምረጣቸውንም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። «በከተማዋም ሆነ በክልሉ እየታየ ያለውን አሳሳቢ ሁኔታ መንግስት በአስቸኳይ እልባት ሊያበጅለት ይገባል ሲሉም» እነዚሁ ነዋሪዎች ጠይቀዋል። በአምቦ ከተማ የተፈጠረውን ችግር ከከተማዋ ከንቲባ ለማጣራት ያደረግነው ጥረት ከንቲባው ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ሳይሳካ ቀርቷል።

በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ውጥረት ከነገሰባቸው ከተሞች አንዷ በሆነችው በባሌ ሮቤ ከተማ ከዚሁ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ቁጥራቸው ያልተጠቀሰ ሰዎች መገደላቸውን ስለመስማታቸው የአይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ለጊዜው ቁጥራቸው ያልተጠቀሰ ሆቴሎችና ካፌዎች መቃጠላቸውን እነዚሁ የአይን እማኞች ገልፀዋል። «ዘርፌ ግርማይ ሆቴል የሚባል አለ ከሮቤ ትልቅ ሆቴል ነው። ባላገሩ የሚባል ሆቴል አለ፤ እሱንም አወደሙት። እንደገና ደግሞ መስቀል ሆቴል የሚባል አለ፤ እሱንም አወደሙት። ሀረር ሆቴል የሚባል አለ እቃዎቹን እየደፉ ነበር» ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የከተማይቱ ነዋሪ የተመለከቱትን ገልጸዋል።

እኚሁ የዓይን እማኝ በከተማዋ የህዝብ ማጓጓዣዎች ስራቸውን አቁመው መዋላቸውን አስረድተዋል። «ምንም አይነት ትራንስፖርት የለም። ሌላው ቀርቶ የራሳቸው የፓትሮል መኪና እንኳ እንዳትንቀሳቀስ በድንጋይ ይዘጋሉ። በእንደዚህ አይነት መንገድ ነው ያለው» ሲሉ የከተማዋን የሐሙስ ውሎ ገልጸዋል። የባሌ ሮቤው ነዋሪ በዶዶላ ከተማም ተመሳሳይ ችግር እንደነበር መስማታቸውን ይናገራሉ። «ዶዶላ ዙሪያ ላይ አሁን በቤተክርስቲያን ካሉት ጋር እየተደዋወልን ነበር። ብዙ ሰው ሞቷል» ብለዋል። ዶይቼ ቬለ በባሌ ሮቤ ስለተከሰተው ሁከት እና ግጭት ከመንግስት ባለስልጣናትም ሆነ ከሌሎች ገለልተኛ አካላት ለማጣራት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

Äthiopien Diskussion Medien und Demokratie in Addis Abeba | Jawar Mohammed
ምስል DW/Y. Gebregziabher

በተያያዘ ዛሬ ሐሙስ ከማለዳው ጀምሮ በቢሾፍቱ ከተማም በግጭት የተሞላ የተቃውሞ ሰልፍ እንደነበር እና አንድ ቤት መቃጠሉን አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የከተማዋ ነዋሪ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። «ዛሬ ከነጋ ጀምሮ ተኩስ በተኩስ ነው። መንገድ ይዘጋሉ፤ አንዳንድ ቦታም ቤት ያፈራረሱት አለ፤ ያቃጠሉትም አለ። በቃ ዛሬ ፌዴራል ገብተው የዘጉትን መንገድ አስከፍተው ነበር። ሹልክ ሹልክ እያሉ ሌላ ይዘጋሉ። ደብረዘይት ላይ ብዙ ተኩስ ነበር። አንድ ቤት ሰባብረው እቃውን ሁሉ አቃጥለዋል፤ ሰባብረዋል» ብለዋል። ግጭት በታከለበት የቢሾፍቱ ከተማ ተቃውሞ መንገድ በሚዘጉ እና መንገድ እንዳይዘጋ በሚቃወሙ ወገኖች መካከል ግጭት ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን የመከላከያ ሰራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ ወደ ከተማዋ በመግባት ለማረጋጋት ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር መመልከታቸውን እኚሁ የአይን እማኝ አስረድተዋል።

በጅማ ከተማ በነበረው የተቃውሞ ሰልፍ በከተማዋ ውጥረት ከመንገሱ ባሻገር በሰውም ሆነ በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን አንድ የከተማዋ ነዋሪለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። «በመላ ከተማው ምንም አይነት እንቅስቃሴ የለም። ታክሲዎች፣ መኪና ሁሉ ነገር ቆሞ፤ መናኸሪያ ሁሉ ተዘግቶ፤ ምግብ ቤቶች፣ የህዝብ አገልግሎት መስጫ ማእከላትም ሁሉ ተዘግተው ነበር። ዛሬም ደግሞ ቀጥሎ ያው ጠዋት ላይ ትንሽ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር። ግን አሁን ሁሉ ከተማው ጸጥ ረጭ ብሎ ነው ያለው። ወታደሮችም፣ የፌዴራል ፖሊሶችም፣ የኦሮሚያ ፖሊሶችም፣ አድማ በታኞችም አሉ። የየራሳቸውን መኪና ይዘው መሳሪያ ጠምደው ነው ወደዚያ ወደዚህ እያሉ ያሉት» ሲሉ የጅማ ከተማ የሐሙስ ውሎን አስረድተዋል። በጅማ የፌዴራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሰራዊት ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑንም ነዋሪው ገልጸዋል።

ታምራት ዲንሳ   

ተስፋለም ወልደየስ