1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያዊነት ላይ ያተኮረው የጠቅላይ ምኒስትሩ ንግግር

ማክሰኞ፣ መጋቢት 25 2010

ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ በበዓለ ሲመታቸው ባደረጉት ንግግር ዘረኝነትና መከፋፈልን ለማስወገድ ጥሪ አቅርበዋል። በተራራቀ የፖለቲካ ጠርዝ ከቆሙ ኃይሎች የኮነኑትም ሆነ የወቀሱት አልነበረም። ንግግራቸው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት ያስቀመጡት የፖሊሲ አቅጣጫ ለመኖሩም ጥቆማ አልሰጠም።

https://p.dw.com/p/2vNhz
Äthiopien Vereidigung Premierminister Abiy Ahmed
ምስል picture-alliance/AA/M. W. Hailu

"ለውጥ ለማምጣት ዝግጁነት እንዳለ ማረጋገጫ" መስጠት ላይ አተኩረዋል

ጠቅላይ ምኒስትርነታቸው በተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጭብጨባ የጸደቀላቸው  ዶክተር አብይ አሕመድ ለኢትዮጵያውያን ስሜት የኮረኮረ ንግግር አድርገዋል። ከስድስት ወራት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩት እናታቸው ወይዘሮ ትዝታ ወልዴ እስከ ተቃዋሚዎቻቸው፤ ከተሰናባቹ ሐይለማርያም ደሳለኝ እስከ ኤርትራ መንግሥት እየጠሩ። 35 ደቂቃ ከ25 ሰከንድ የረዘመ ንግግራቸው ደጋግመው ስለ ኢትዮጵያ አንድነት የሰበኩበት ነበር። "አንድ ኢትዮጵያዊ አባት እንዳሉት እኛ ስንኖር ሰዎች ስናልፍ አፈር ስናልፍ ሀገር እንሆናለን። የየትኛውም ኢትዮጵያዊ ክቡር ሥጋ እና ደም በየትኛውም ኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ አፈር ሆኖ ታገኙታላችሁ። ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን።" እያሉ ሰበኩ።

የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሐሌሉያ ሉሌ "ባለፉት ሁለት እና ሶስት አመታት ሀገሪቱ አይታ በማታውቀው የሕዝባዊ አመፅ፣ ተቃውሞ አንዳንዶች አብዮት ብለው እስኪጠሩት ድረስ የታየ ከፍተኛ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ እና እምቢተኝነት ነበረ። ይኸ እምቢተኝነት በአንዳንድ ቦታዎች የብሔርተኝነት ስሜት ነበረው። በአንዳንድ ታዛቢዎች ይኸ ነገር የኢትዮጵያን መንግሥትነት፣ የኢትዮጵያን ሀገርነት ፈተና ውስጥ ከቷል የሚል አመለካከት አላቸው" ሲሉ ይናገራሉ። "በአንዳንድ ሰዎችም ደግሞ አሁን ያለው የፖለቲካው አደረጃጀት ብሔር ላይ በጣም በማተኮሩ ኢትዮጵያዊነት የሚባለው ነገር ጥያቄ ተፈጥሮበታል ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ።  እንግዲህ ዶክተር አብይ ለዛ ፍርሐት ለመመለስ ይመስለኛል በአፅንዖት ያነሱት ብዬ አስባለሁ።" ሲሉ የጠቅላይ ምኒስትሩን ምክንያት ያስረዳሉ።

ንግግራቸው አብዝተው ስለ ኢትዮጵያዊነት የሰበኩበት፤ አንድነትንም የወተወቱበት ይሁን እንጂ በጠቅላይ ምኒስትርነታቸው ስለሚወስዷቸው እርምጃዎች ጥቂት ያሉበት ነው። ቢያንስ ግን ላለፉት ሶስት ገደማ አመታት ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰዎች መገደላቸውን አስታውሰው ይቅርታ ጠይቀዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ"በተለያየ ጊዜ መስዋዕትነት ለከፈሉ የመብት ተከራካሪዎች ፖለቲከኞች በቅጡ ሳይቦርቁ ሕይወታቸው ለተቀጠፈ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች ለስነ-ልቦናዊ እና አካላዊ ቀውስ ለተዳረጉ ቤተሰቦች እና ግለሰቦች ከልብ የመነጨ ይቅርታ እጠይቃለሁ" ሲሉ ተደምጠዋል።

ጠቅላይ ምኒስትሩ ስለ ዴሞክራሲ፣ ፍትኅ፣ ነፃነት እና የሐሳብ ልዩነት የተናገሩት ሁሉ በአስፈላጊነታቸው ላይ ያተኮረ ነበር። ዶክተር አብይ "ነፃነትን ተረድቶ እውቅና የሰጠውን ሕገ-መንግሥታችንን በአግባቡ በመተግበር፤ የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተለይም ሐሳብን የመግለጽ፣ የመሰባሰብ እና የመደራጀት መብቶች በሕገ-መንግሥታችን መሠረት ሊከበሩ ይገባል። የዜጎች በአገራቸው የአስተዳደር መዋቅር በዴሞክራሲያዊ አግባብ በየደረጃው የመሳተፍ መብትም ሙሉ በሙሉ እውን መሆን አለበት" ሲሉ ተደምጠዋል።

እርሳቸው ሐሳብን የመግለጽ እና የመደራጀት መብቶች ሊከበሩ ይገባል ብለው ሲናገሩ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፍትኅ ቢሮ ቃል አቀባይ አቶ ታዬ ደንደዓ እስር ቤት ናቸው። አቶ ታዬ የታሰሩት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት በሞያሌ በስህተት ፈጽመውታል የተባለውን ግድያ በመቃወማቸው ነበር። ጠቅላይ ምኒስትሩ ያሉት ሳይሆን ቀርቶ ከአዲስ አበባ እስከ ባሕር ዳር ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ዘብጥያ ወርደዋል።

ጠቅላይ ምኒስትሩ የተረከቡት መንግሥት የሚመራበትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንድም ቦታ አልጠቀሱም። ከሞያሌ እስከ ወልድያ በተፈጸሙ ግድያዎችያ እጃቸው አለበት ተብለው የሚወቀሱ ተጠያቂዎችን ለፍርድ ለማቅረብ ስለመዘጋጀታቸው ያሉት ነገር የለም።

Äthiopien Vereidigung Premierminister Abiy Ahmed
ምስል picture alliance/AP Photo/M. Ayene

እንደ አቶ ሐሌሉያ አባባል "የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን ካለው መዋቅር እና የኃይል ግንኙነት አኳያ አንድ የኦሮሞ ጠቅላይ ምኒስትር የደኅንነት እና የመከላከያ ኃይሎችን አዞ ወይም በእነሱ ላይ ጫና አሳድሮ የሕገ-መንግሥት ሥልጣኑን ተጠቅሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ጫና የማሳደር አቅም ይኖራቸው አይኖራቸው" ወደ ፊት የሚታይ ነው።

ጠቅላይ ምኒስትሩ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ለመገንባት፣ የሰብዓዊ መብት፣ የእኩልነት እና የፍትኅ ጉዳዮች ላይ የገቧቸውን ቃል ኪዳኖች ለማሳካት ፈተና ይገጥማቸዋል።

ተንታኙ  "እነዚህን ነገሮች በአግባቡ ለመተርጎም እና መሬት ላይ ለማውረድ የመጀመሪያው ትልቁ የሚያጋጥማቸው እክል የደኅንነት ተቋማት ለዴሞክራሲ ተጠያቂነት እንዲሁም ደግሞ ለሲቪል የበላይነት ተገዢ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው። ሕገ-መንግሥቱ እንደሚያዘው አንደኛ የመከላከያ እና የደኅንነት ተቋማቱ የኢትዮጵያን ሕዝብ ብዝኃነት በሚያንጸባርቅ መልኩ መደራጀት አለባቸው ይላል። ስለዚህ እነዚህ ተቋማት የኢትዮጵያን ሕዝብ ብዝኃነት በሚያንጸባርቅ መልኩ [አመራሩ በተለይ] መዋቀር አለበት። በሁለተኝነት እና በዋንኛነት ደግሞ የእነዚህ ተቋማት ባህል መለወጥ አለበት። ሕገ-መንግሥቱ እንደሚያዘው እነዚህ ተቋማት ሕዝብ ለመረጣቸው እንደራሴዎች ተጠያቂነታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው።  ይኸንን ባህል እንዲሰፍን ማድረግ ዶክተር አብይን እንደ ጠቅላይ ምኒስትር ከሚገጥሟቸው ትልልቅና አስቸኳይ ፈተናዎች መካከል አንዱ ይመስለኛል።" ሲሉ ይናገራሉ።

Äthiopien Vereidigung Premierminister Abiy Ahmed
ምስል picture-alliance/AA/M. W. Hailu

ጠቅላይ ምኒስትር አብይ "ያሳካናቸው በርካታ ድሎች እንዳሉ ሁሉ በፍጥነት መቀረፍ የሚገባቸው በርካታ ጉድለቶች እንዳሉም እናምናለን" ሲሉ ተደምጠዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ የሐብት ብክነት እና የተደራጀ ሙስናን ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ለመቅረፍ ቃል ገብተዋል።የውጭ ንግድ መዳከም፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እና ፍላጎት አለመጣጣም፣ የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነት፣ የውጭ እዳ ጫና፣ ለአገሪቱ ምጣኔ ሐብት ፈተና መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በውጭ አገራት ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከልብ ይቅርታ በመባባል በብሔራዊ መግባባት "ብሩኅ" ወዳሉት አገራዊ ምዕራፍ ለመሸጋገር ጠቅላይ ምኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል። እርሳቸው ተፎካካሪ ያሏቸው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ መንግሥታቸው በጽኑ እንደሚያምንም አስረድተዋል።

አቶ ሐሌሉያ እንደሚሉት የዛሬው ንግግር "ለውጥ ለማምጣት ዝግጁነት እንዳለ ማረጋገጫ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነ እርቅ፣ ሰላም ፍቅር እና አገራዊ አንድነትን ለማስጠበቅ ፍላጎት እንዳለ የሚያሳይ መግለጫ" ተደርጎ ሊታይ ይገባል። ተንታኙ "እንደ ፖሊሲ የተነሱ የሕዝብ ጥያቄዎች እንዴት ለመፍታት፤ መቼ ለመፍታት እንደፈለጉ ግልፅ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫ እና የጊዜ ገደብ አላስቀመጡም" ሲሉ ያክላሉ።

የአፍሪቃ ቀንድ ፖለቲካ በተለያዩ ኃይሎች የጥቅም እና የዓላማ ሽኩቻ "ቀውስ ውስጥ" የገባ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ምኒስትሩ "ከአፍሪቃውያን ወንድሞቻችን ጋር በአጠቃላይ ከጎረቤቶቻችን ጋር በተለይ በችግርም በተድላም አብረን እንቆማለን" ብለዋል። ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለአመታት ሰፍኖ የቆየውን አለመግባባት ለመፍታት ለውይይት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው የኤርትራ መንግሥት "ተመሳሳይ አቋም" እንዲይዝ ጥሪ አቅርበዋል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሠ