1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲና የለውጥ ሂደቱ የተጋረጠበት አደጋ

ሰኞ፣ መስከረም 4 2013

በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለውጡን የሚፈታተኑና የሚገዳደሩ አያሌ ስጋቶች መኖራቸውን ዋንኞቹ የሀገሪቱ የተፎካካሪ ፓርቲዎች እና ዓለማቀፍ የጥናትና ምርምር ተቋማት ባለሙያዎች ጭምር በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በስፋት እየገለፁ ይገኛሉ::

https://p.dw.com/p/3iStl
12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

የፌደራል መንግሥት በተለመደ ሁኔታ የተፎካካሪ አመራሮችንና የተለየ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች የማፈንና ጫማ የማድረግ ሁኔታ አለ

በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለውጡን የሚፈታተኑና የሚገዳደሩ አያሌ ስጋቶች መኖራቸውን ዋንኞቹ የሀገሪቱ የተፎካካሪ ፓርቲዎች እና ዓለማቀፍ የጥናትና ምርምር ተቋማት ባለሙያዎች ጭምር በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በስፋት እየገለፁ ይገኛሉ። ይህ ተግዳሮት ደግሞ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በሚደረገው ጉዞና ጠንካራ ሀገረ መንግሥትን ለመመስረት በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ከባድ ማነቆ ፈጥሯል። አምና በለውጡ ማግስት ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ መሻሻሎችን እያሳየች መሆኗን ገልፆ የነበረው በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው ‹‹ፍሪደም ሐውስ›› የተሰኘው ዓለም አቀፍ የጥናት ተቋም ባለፈው ወር አጋማሽ ላይ ባወጣው ሪፖርት ሀገሪቱ ወደ ተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የምታደርገው ጉዞ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉንና አደጋ እንደተደቀነበት ይፋ አድርጓል። የሀገሪቱ መፃኢ ዕድል ያሰጋው ተቋሙ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ተስፋ እንዳያሽቆለቁል መንግሥት ሕዝቡና ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡትም አሳስቧል። በአንፃሩ ከቀደመው የኢሕአዲግ አገዛዝ ባዶ ካዝና፣ የሃገራትና የዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማቶችን ዕዳ እና የወደቀ ኢኮኖሚን ተረክቦ ወደ ሥልጣን መምጣቱን የሚገልፀው መንግሥት ገዢው የብልፅግና ፓርቲ ከለውጡ በኋላ የሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት እንዲያንሰራራ፣ የሕሊና እስረኞች እንዲፈቱና የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ አያሌ ጥረት ማድረጉን ይስረዳል። በልማቱም ዘርፍ ቢሆን ለዜጎች የሥራ ዕድልን የሚፈጥሩ በርካታ የግንባታ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በመጀመርና በሃብት ብክነትና በግንባታ ጥራት ችግር ተቋርጦ የቆየው የህዳሴው ግድብ ግንባታ ተፋጥኖ የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት እንዲከናወን ሌሎችም በጅምር የቆዩ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች፣ የልማት ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቁ ማድረጉንም እንደ ስኬትና ጥንካሬው ይገልፃል። የለውጡን የሽግግር ጊዜ በተለይም ያለፈውን አሮጌ ዓመት የፖለቲካ ጉዞ የሚገመግሙ የተፎካካሪ ፓርቲዎ እና አንዳንድ የፖለቲካ ልሂቃን ግን፤ የለውጡ ሂደት መስቀለኛ መንገድ ላይ ከመገኘቱም ሌላ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታውም ቢሆን ከባድ አደጋ ተደቅኖበታል ነው የሚሉት። እስከመጪው ምርጫ የለውጡን ሂደት ሊያሳኩ የሚችሉ ጠንካራና ገለልተኛ የዴሞክራሲያዊ ተቋማት አለመገንባታቸው፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ ስር እየሰደደና እየተንሰራፋ የመጣው ፈር የለቀቀ የብሄር ፅንፈኝነት፣ በኢ-መደበኛ አደረጃጀት በተለያየ ስያሜ ራሳቸውን ያደራጁ ወጣቶች የመንግሥትን ሚና ተክተው በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈፅሙት ጥቃትና የንብረት ውድመት፣ የሥራ አጥነት መስፋፋትና የኑሮ ዋስትና ማጣት፣ ሃላፊነት የጎደላቸው መገናኛ ብዙሃን የሚፈጥሩት ጫናና ተፅዕኖ ፣ ከብሄርና ከሃይማኖት ግጭቶች ለማትረፍ የሚንቀሳቀሱ እኩያን ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ አደብ እንዲገዙ ለማድረግ መንግስት የሚያሳየው ዳተኝነት ወይም ቸልተኝነት እነዚህን የመሳሰሉ ምስቅልቅል ፖለቲካዊ ፣ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች በለውጡ ሂደት ላይ ከባድ ማነቆ መፍጠራቸው በዜጎች ሕልውናና በሕግ እና ስርዓት መከበርም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማስከተላቸው በተለያዩ ሕዝባዊ መድረኮች ሲገለፅ ቆይቷል:: የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከዓለማቀፍ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ጋር ከሰሞኑ ባደረጉት የቪድዮ ውይይት፤ ሀገሪቱ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ እንዳትሻገር ማነቆ ከሆኑት ዋንኛ ችግሮች እንዲሁም ከለውጡ ስጋት መካከል በቀላሉ በስሜት የሚነሳሱ በርካታ ስራ አጥ ወጣቶች በሀገሪቱ መኖራቸው መሆኑን አስምረውበታል:: እነዚህን ወጣቶች በቀላሉ ለረብሻ ማሰለፍ እንደሚቻልና በጥቂት ገንዘብ ገዝቶ ለጥፋት ማሰማራት የሚቻል መሆኑን በቅርቡ የተፈጠሩ ችግሮችን ዋቢ መሆናቸውን በመጥቀስም አስረድተዋል፡፡ በማህበረሰባችን ውስጥ የተፈጠረው የሞራል ዝቅጠትም ቢሆን ከሃይማኖት እስከ ትምህርት ተቋማትና በሁሉም ማህበረሰብ ውስጥ ስር ሰዷል የሚሉት ፕ/ር ብርሃኑ ዋናው የሞራል ዝቅጠቱ መነሻም ገንዘብ በማንኛውም መንገድ የማግኘት ያልተገደበ ፍላጐት ነው ይላሉ፡፡ አሁን ያለንበት ጊዜ በእጅጉ የማህበረሰቡ ሞራል የተሸረሸረበት መሆኑንም በመጥቀስ ለማህበረሰቡ ሞራል ዝቅጠት ያለፈውን 27 ዓመት ስርዓት በዋነኛነት ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ የፖለቲካ ልሂቃን በበኩላቸው በሀገሪቱ ስር እየሰደዱ የመጡ ችግሮችን ለመቅረፍ ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም የሚያራምዱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከውህደት እስከ ጥምረት ኃይል እና ግምባር ፈጥረው መንግስትን ከመገዳደር ይልቅ በግል ዝናና በስልጣን ሹክቻ አንዱ ሌላውን ጠልፎ ለመጣል የሚያደርገው የሴራ ፖለቲካ ዛሬም ያልተፈታ የሕዝቡ ሰቆቃ እንዲራዘምና አምባገነን ስርዓት እንዲቀጥል ምክንያት ሆኖል ሲሉ ይተቻሉ:: የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ግን ይህ አስተያየት የተለያዩ ፓርቲዎች ለሀገር እና ለሕዝብ ጥቅም ራሳቸውን አክስመው የጋራ የፖለቲካ ራዕይና ውህደት ፈጠው የመሰረቱትን የእኛ ፓርቲ አይመለከትም ባይ ናቸው::

«ተመሳሳይ ራዕይ ያላቸው ፓርቲዎች ግንባር ወይም ውህደት ፈጥረው ከመንግሥት ጋር ተፎካካሪ ሆነው ለመቅረብ ከመቀሳቀስ ይልቅ የግል ዝናን ማስቀደምና በፖለቲካ ሴራ መጠላለፍ ባህላቸው የሆነ ይመስላል የሚለው ጥያቄ የእኛን ፓርቲ የሚመለከት አይደለም:: ኢዜማ ከ 7 ያላነሱ ፓርቲዎች የሀገር እና የሕዝብን ጥቅም በማስቀደም ራሳቸውን አክስመው ውህደት የፈጠሩት ፓርቲ ስብስብ ነው:: በዚህ አጭር ጊዜም ዓላማና መርሃግብራችንን በመላው ሀገሪቱ ለማስተዋወቅ ከመቀሌ እስከ ሞያሌ ከጅጅጋ እስከ ወለጋ ያልሄድንበት አካባቢ የለም:: ቀደም ባለው አገዛዝ ገዢው መንግሥት ሥልጣን ካጣ ሀገር ትፈርሳለች የሚል እሳቤ ነበር:: አሁን ላይ ግን ሕዝባችን ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ ኢዜማም አለ የሚል የስነ ልቦና ለውጥ እንዲያመጣ ለማድረግ አስችለናል» ብለዋል::

የኢዜማ መሪ ፕ/ር ብርሃኑ በሰሞኑ የውይይት ላይ እንደገለፁት፤ «ሀገሪቱ የምትመራበት ብሄር ተኮር ፌደራሊዝም ለነውረኞችና ለወንጀለኞች በዘር ውስጥ ለመደበቅ ምቹ እድል የሚሰጥ መሆኑ ሀገሪቱ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር በምታደርገው የለውጥ ሂደት ላይ ስጋት ፈጥሯል» ፡፡ አሁን በብዛት የሚነሱ የክልልነት ጥያቄዎችንና ጥፋተኞች ብሔር ውስጥ ለመደበቅ የሚያደርጉትን ጥረትም በአስረጅነት ለመጥቀስ ሞክረዋል፡፡ ይህን ሁሉ ሥርዓቱ ያመጣውን ውስብስብ ችግር መልክ ለማሲያዝ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ አለመሆንና በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት በደንብ ሊገዳደር የሚችል ቁመና አለመያዛቸውም ሌላው እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን በተለይም ደግሞ ምክንያታዊ ሆነው ሰፊ ድጋፍ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ገና በሚፈለገው መጠን አለመፈጠራቸውን ነው የሚናገሩት:: በኢትዮጵያ በተለይም ለአምስት ዓመታት በመላ ሀገሪቱ ተጠናክሮ የቀጠለው ሕዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ገዥውን ፓርቲ ኢሕአዲግ የፖለቲካ ውድድር ሜዳውን ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ክፍት እንዲያደርግ ካስገደደው በኋላ በሚያዝያ ወር 2010 ዓ.ም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ ወደ ስልጣን መምጣት ለብዙ ኢትዮጵያውያን ተስፋን የሰነቀ ነበር:: የፖለቲካ እስረኞች መፈታት, ከሀገር ተሰደው የነበሩ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትና ድጋፊዎች በሃገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ ከጎረቤት ሀገር ኤርትራም ጋር ለሃያ ዓመታት ያህል ሻክሮ የቆየውን ግንኙነት እንዲቀጥል ማድረግ በለውጡ አመራር የተወሰዱ በጎ ጅምሮች ነበሩ:: ይሁን እንጂ ሕወሃት አዲሱን የብልፅግና ፓርቲ ለመቀላቀል አለመፈለጉ, መቆሚያ ያጣው የብሄር ግጭትና የሕዝቦች መፈናቀል እንዲሁም ፅንፈኞች በንፁሃን ዜጎች, በዕምነት ተቋማትና በንብረት ላይ የሚፈፅሙት ጥቃትን ማስቆም አለመቻል ሀገሪቱ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር በምታደርገው የለውጥ ሂደት ላይ ከባድ ስጋትና አደጋ መደቀናቸው እየታየ ነው:: አንዳንድ በኢ-መደበኛ አደረጃጀት ራሳቸውን የየአካባቢው ሹም አድርገው ያደራጁ ግለሰቦችም በእንቅስቃሴያቸው ላይ ቀላል የማይባል እንቅፋት ፈጥረው መቆየታቸውን የኢዜማ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ተናግረዋል::

«በኢ-መደበኛ አደረጃጀት እራሳቸውን ያደራጁ ግለሰቦችና አንዳንድ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ አካላት እንደ ኦሮምያ አማራና ደቡብ ክልሎች እንቅስቃሴያችንን በምናከናውንበትና ቢሮ በምንከፍትበት ወቅት ለአጭር ጊዜ ጫናና ተፅዕኖ ለማሳደር ሞክረው ነበር:: ችግሩንም ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ለየክልሉ መንግሥታት በማሳወቃችን ሊቀረፍ ችሎዋል:: በመሰረቱ ይህ ዓይነቱ ድርጊት ፈፅሞ መፈፀም አልነበረበትም:: የሚቀጥል ቢሆን ኖሮ ሁከት እና ብጥብጥ ሊያስከትል ይችል ነበር:: አሁንም ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲደረግ ፍላጎቱ ካለ ሁሉም ፓርቲዎች የህግ ድጋፍና ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል።»

በዓለማችን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰትም ሀገሪቱ ለአምስት ዓመታት የፖለቲካ ነውጥ እና አለመረጋጋት ውስጥ ከቆየች በኋላ ባሳለፍነው ዓመት ነሃሴ ወር ላይ ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ በነበረችበት ወቅት መከሰቱ ለፖለቲካዊ ውጥረቱ መባባስ የራሱን አስተዋፅዖ አድርጓል:: መንግሥት ለፖለቲካዊ ጭቆና መሳሪያ አድርጎ እስካልተጠቀመበት ድረስ የምርጫውን መራዘም እንደግፋለን ያሉ አንዳንድ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጭምር ዘግይተው የምርጫው መካሄድ ወሳኝ መሆኑን ሲገልፁ ተደምጠዋል:: ከፌደራል መንግስቱ ጋር ውዝግብ ውስጥ የሚገኘው ሕወሃትም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ, የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክርቤቶች ምርጫው መራዘሙን አስመልክቶ የደረሱበትን ውሳኔ ወደ ጎን በመተው ከቀናት በፊት በተናጥል በክልሉ ምርጫ ማካሄዱ በአዲሱን ዓመት ላይ ያጠላ ሌላ ስጋት ሆኖ ይጠቀሳል:: መንግሥት እስካሁን በተደጋጋሚ ሕወሃትን እና በለውጡ ሂደት ጥቅም ያጡ ሃይሎችን ለሚፈፅሙ ቀውሶች ተጠያቂ ቢያደርግም በተለይም በቅርቡ ለተከሰቱ የሕዝብ ዕልቂቶችና የንብረት ውድመቶች  በመንግሥት አመራር ውስጥ ያሉ ሃላፊዎችም ቸልተኝነት እንዲሁም የመከላከያና የፀጥታ ኃይል በፍጥነት በማሰማራት ጉዳቱን ለመቀነስ ያደረጉት ጥረት አናሳ መሆኑ የሕዝቡን ሰቆቃ እንዳባባሰው ነው የሚገለፀው:: "ለውጡ በብዙ ስኬትና ፈተና የታጀበ ነው" የሚሉት የብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ዋና ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም በፖለቲካ ስርዓት ማሻሻያ ለውጡ በፓርቲው አደረጃጀት በዋናነት "ወዳጅና ጠላት" ብሎ ሰዎችን በሁለት ጎራ በመፈረጅ ይመራበት የነበረውን መርህ ለመቀየር መቻሉን ግንባር እና አጋር ድርጅቶች በሚል ሁለት ጎራ አግላይ የነበረውን ሥርዓት በማሻሻልም አጋር ድርጅቶች በሙሉ እኩል በውሳኔ ሰጪነት እንዲሳተፉ መደረጉ የብልፅግና  ዓበይት ስኬቶች መሆናቸውን ይናገራሉ:: አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝቦች የመኖር ዋስትናና  የሀገሪቱም መፃኢ ዕድል ለአደጋ መጋለጡ በተለያዩ ወገኖች በተደጋጋሚ ቢወሳም መንግስት ህግና ሥርዓትን የማስከበር ፈጣን ውሳኔ መስጠት ተስኖት ቆይቷል ለሚለው ነቀፌታ ጉዳዩ ውስብስብ መሆኑን ለዶይቼ ቨለ የተናገሩት ሃላፊው ገንዘብ መድቦ፣ ሰዎችን አሰልጥኖ የብሄር እና የሃይማኖት ግጭት በመፍጠር የሀገሪቱን ሰላም በማናጋት ለውጡን ለመቀልበስ የሚንቀሳቀስ ኃይል አለ ይላሉ:: ጫፍ የወጣ ፅንፈኝነትና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል አመራሮችም  የወንጀኞች ተባባሪ በመሆንና ሃላፊነታቸውን ለመወጣት  ቸልተኝነት በማሳየት ለለውጡ እንቅፋት ሆነዋል ሲሉ ይገልጻሉ።

«ገንዘብ መድቦ ሰዎችን ለሁከት መልምሎና አደራጅቶ የሚንቀሳቀስ የጥፋት ኃይል የብሄር እና የሃይማኖት ግጭቶችን ለመፍጠር በመላ ሀገሪቱ በስፋት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል:: መንግሥት ሁኔታዎችን በትዕግስትና በሆደ ሰፊነት ሲከታተል ነው የቆየው:: ያም ቢሆን ይህ የሽብር ሃይልና ጫፍ የረገጠ ፅንፈኝነት ለበርካታ ዜጎች ሞት ለሃይማኖት ተቋማትና ለንብረት ውድመት መንስኤ መሆኑን በግምገማችን ተመልክተናል:: በመንግሥት አመራር ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦችም ከዚሁ የጥፋት ኃይል ጎን በመሰለፍና አደጋውን ለመቀነስ ቸልተኝነት በማሳየታቸው በሕግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርገናል:: የጥፋታቸው መጠን አነስተኛ የነበረውንም ቢሆን በየመዋቅሩ ከስልጣን እንዲነሱ እርምጃ ወስደናል:: በአሁኑ ጊዜ የመንግስት ሃላፊዎችም ሆኑ ሕብረተሰቡ ከአዲስ አበባ ውጭ በሰላም ወጥተው የሚገቡበት አስተማማኝ ሰላም ሰፍኗል ወይ ለተባለው ጥያቄም ከሞላ ጎደል ሰላም በማስፈናችን ሁሉም ያለችግር በሰላም መዘዋወር የሚችልበት ሁኔታ ነው ያለው:: ያም ቢሆን አልፎ አልፎ በስውር የማስፈራራትና እና የትንኮሳ ድርጊቶች መኖራቸው ቢታወቅም እሱም ከቁጥጥራችን ውጭ የሚሆን አይደለም።»

ከአዲስ አበባ ውጪ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ሕብረተሰቡ በነጻነት መንቀሳቀስ እንዳልቻለና በስጋት ውስጥ እንደሚኖው እየገለፀ ነው:: በኢ-መደበኛ አደረጃጀት እራሳቸውን ያደራጁ ግለሰቦችና ጽንፈኞች የወንጀል ጥቃትና እንቅስቃሴም ዛሬም ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ የሆነ ይመስላል:: ሀገር ማለት ሕዝብ ማለት ነው:: በመሰረቱ የአንድ መንግሥት ተቀዳሚ ዓላማው የዜጎችን የመኖር ዋስትናና የሀገርን ሕልውና ማረጋገጥ እንዲሁም ሕግና ሥርዓትን ማስከበር እንደሆነ ይታመናል:: በዚህ ረገድ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብልፅግና ፓርቲ ይህን መሰረታዊ መብት ከማረጋገጥና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባት ወሳኝ የሆኑ ጠንካራ ተቋማትን ከመገንባት ይልቅ የሕዝብና የሀገር ሰላምና ደህንነት ከተረጋገጠ በኋላ መከናወን ለሚኖርባቸው እንደ ከተማን ማስዋብ ያሉ ዕቅዶች ላይ ከፍተኛ በጀት መድቦና ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀሱ የዕቅድ አፈፃፀም ቅደም ተከተል መፋለስን አያሳይም ወይ ስንል አቶ ብናልፍን ጠይቀናቸው ነበር::

«በመንግሥት ወጪ እና በዕርዳታ የሚከናወኑት እነዚህ የልማት ከተማን የማስዋብ ፕሮጀክቶች ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድልን የፈጠሩ ናቸው:: በእንጦጦ አካባቢ በ እንጨት ሸከማ የድህነት ኑሮ ጀርባቸው የጎበጠ እናቶችንም ሕይወት የለወጠ የገቢ ምንጭን የፈጠረና አዳዲስ የስራ አማራጭንም ያስገኘ መሆኑ ሊታወቅ ይገባዋል።»

ሕወሃት የብልጽግናን ፓርቲ ለመቀላቀል ፈቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግስት የሕወሐት ተወካዮችን በሙሉ በሚያስችል ሁኔታ ከካቢኔው አሰናብቷቸዋል፤ ሕወሃት የተናጥል ምርጫ ማካሄዱና ከፌደራል መንግስቱ ዕውቅና ውጪ ከውጭ መንግስታት ጋር ግንኙነት ለመፍጠር የሚያደርገው እንቅስቃሴም ቢሆን በፌደራል መንግስቱና በትግራይ ክልል መካከል ያለውን ውዝግብና የቃላት ጦርነት ከጊዜ ወደ ጊዜ አካሮታል:: አንዳንድ የትግራይ ወጣት አክቲቪስቶች ከፌደሬሽኑ የመገንጠል ሃሳብን በማህበራዊ ሚድያዎች እያሰራጩ ባሉበትና ክልሉም ልዩ ወታደራዊ ኃይሉን እያጠናከረ በሚገኝበት በአሁኑ ሰዓት ውዝግቡን በሰላማዊ መንገድና በውይይት ለዘለቄታው ለመፍታት በመንግሥት በኩል በአዲስ ዓመት ምን ዕቅድ አለ ስንል ለሃላፊው ያነሳንላቸው ሌላው ጥያቄ ነበር።

Äthiopien Addis Abeba
ምስል DW/S. Muchie

«መንግሥት ከትግራይ ሕዝብ ጋር ምንም ችግር የለበትም:: ሆኖም ለውጡን ለማደናቀፍ በዛው በትግራይ የመሸገ ኃይል አለ:: ይህ ቡድን በቅርቡ አካሄድኩት ያለው ምርጫ ኢ-ህገመግስታዊ እና ተቀባይነት የሌለው ነው:: ቡድኑ መንግሥት የኃይል እርምጃ እንዲወስድ ተደጋጋሚ ትንኮሳዎችን ቢፈፅምም መንግስት ግን ለትግራይ ሕዝብ ሰላምና ክብር ሲል ወደ ኃይል እርምጃ የሚገባ አይሆንም አማራጭም ነው ብሎ አያስብም:: ሆኖም ችግሩን በሰከነ ሁኔታና በብልሃት ለመፍታት ጥረቱ ይቀጥላል።»

ባሳለፍነው ዓመት አብዛኛዎቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሕዝብን ከሰቆቃ ሀገርንም ከቀውስ ለመታደግ መንግሥት በአግባቡ ኃላፊነቱን እንዲወጣና እስከ ቀጣዩ ምርጫ ሀገሪቱን በተሳካ ሁኔታ እንዲያሻግር ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆነው አስፈላጊውን ጫና በማሳደር ይህ ነው የሚባል የጎላ እንቅስቃሴ አላከናወኑም የሚል አስተያየትም ትችትም በተደጋጋሚ ይሰማል:: በመላ ሃገሪቱም ቢሆን በነፃነት ተዘዋውረው አባላትን ለመልመል ጽ/ቤት ለመክፈትና ዓላማና መርሃ-ግብራቸውን በይፋ ለማስተዋወቅ አልቻሉም ነው የሚባለው::አባላቶቻቸውም በተለያየ ሰበብ እየታሰሩባቸው እንደሚገኙ ያስረዳሉ::ይህ ጉዞ ደግሞ በሚጠብቃቸው ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ አያስችላቸውም" እየተባለ በተለያዩ ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ለሚነሱት አስተያየቶችም የኢዜማ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ የሰጡት መልስ አለ::

«የፌደራል መንግሥት በተለመደ ሁኔታ ተገዳዳሪ የተፎካካሪ አመራሮችን እና የተለየ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች የማፈን እና ጫማ የማድረግ ሁኔታ አለ:: ያ ደግሞ የተፎካካሪዎችን እንቅስቃሴ የሚገታና የሚያዳክም ሳይሆን ለበለጠ ትግል የሚያተጋቸው መሆን አለበት ብለን ነው የምናስበው:: እዚህ ላይ አንድ ግልፅ ግምገማ ማድረግ ያስፈልጋል:: ቀደም ባለው አስተዳደር ተደራጅቶ ፖለቲካ ፓርቲ መስርቶ መንቀሳቀስም አይደለም ፖለቲካም ማውራት አስፈሪ የሆነበት ሥርዓት ነበር:: በተወሰነ ሁኔታ ተሸጋግረነዋል ብለን እናስባለን።»

በአሁኑ ወቅት አንዳንድ የተፎካካሪ ፓርቲዎች በለውጡ ጅማሮ ወቅት ታይቶ የነበረው የዴሞክራሲ ጭላንጭል እየከሰመ መሆኑን ይናገራሉ:: መንግሥት የሚቀናቀኑትን እና በጠላትነት የፈረጃቸውን የተቃውሞ ፖለቲካ አመራሮችና ነጻ ጋዜጠኞች እንደ ቀደመው አገዛዝ የፈጠራ ክስ እየመሰረተ የማሰርና የማንገላታት የፍትህ ሥርዓትና ተቋሙም ነፃና ገለልተኛ ባለመሆኑ በፍርድ ቤት የዋስትና መብት የሰጣቸውን ተጠርጣሪዎች በልዩ ትዕዛዝ ፖሊስ በተደጋጋሚ አልፈታም ብሎ እያንገላታ ይገኛል የሚል ተደጋጋሚ ወቀሳም እየሰነዘሩ ይገኛሉ:: እንደሚባለው ዜጎችን በፖለቲካ አመለካከታቸውና በማንነታቸው እየፈረጁ ማሰር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው ምን ያህል ይጠቅማል ለሚለው ጥያቄም የብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ዋና ሃላፊ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም መልስ ሰጥተውናል::

«አባሎቻችን አለአግባብ ታሰሩብን የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ እናውቃለን:: ይሁንና በተለይም ከድምፃዊ ሀጫሉን ሕልፈት ተከትሎ በተቀሰቀሰው የበርካታ ዜጎችን ሕይወት ባጠፋ እና ንብረት ባወደመ ወንጀል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠርጥረው የታሰሩት እነዚህ ግለሰቦች በሚያራምዱት የፖለቲካ አመለካከትም ሆነ በማንነታቸው አለመታሰራቸው ሊሰመርበት ይገባል:: አንድ ግልፅ መሆን ያለበት ከታሳሪዎቹ አብዛኛዎቹ የብልፅግና አመራሮች ሲሆኑ የሕግና የፍትህ ስርዓቱንም ነፃና ገለልተኛ ለማድረግ የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆኑ ግለሰቦች በሃላፊነት ቦታ እስከመስቀመጥ ድረስ የሄደ የለውጥ አመራር መሆኑ ቁርጠኝነቱን ያመላክታል:: ሕግ እና ሥርዓት ይከበር ከተባለ ማንም ሰው በወንጀል የተጠርጠረ ለፍርድ መቅረብ ይኖርበታል:: ምናልባትት ፖሊስ የፍርድ ቤት ዋስትና መብት የሰጣቸውን ተጠርጣሪዎች ሕጉን ተከትሎ አስሮ ሊሆን ይችላል።»

 

እንዳልካቸው ፈቃደ

 

አዜብ ታደሰ