1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ የዜጎች መብት እና የሕግ የበላይነት እንዲከበር ተጠየቀ

ቅዳሜ፣ መስከረም 12 2011

በፍራንክፈርት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የቡራዩ እና አካባቢዋ ጥቃት ሰለባዎችን ለመዘከር ዛሬ ከተማ አስተዳደር ሕንጻ አካባቢ ተሰባስበው የጸሎት እና የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት አካሄዱ። ንጹሃን ዜጎች ሕይወታቸውን ያጡበትን እና በሺዎች የሚቆጠሩ የተፈናቀሉበት ጥቃት ከባህላችን ያፈነገጠ እና ሰብአዊነት የጎደለው ነው ሲሉ አውግዘዋል።

https://p.dw.com/p/35LQq
Deutschland Frankfurt am Main | Gedenkveranstaltung fü Opfer von Burayu in Äthiopien
ምስል DW/E. Fekade

Beri. (Frankfurt)- Ethiopians commemoration service for Burayu victims - MP3-Stereo

በኢትዮጵያ ብሄር ተኮር ጥላቻ እና ዘረኝነት እንዲሁም በሥርዓት አልበኝነት የሚፈጸም ህገ ወጥ የደቦ ጥቃት አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱን በፍራንክፈርት ከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል:: በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይት እና የትብብር መድረክ እዛው ጀርመን ከሚገኘው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚቴ ጋር ዛሬ በከተማው ዋና ማከል ሮመርበርግ በሚባለው አካባቢ በሚገኘው የከተማው አስተዳደር ህንጻ በቡራዩ እና አካባቢዋ የዘር ጥቃት ሰለባዎችን ለመዘከር በጋራ ባጋጁት የጸሎት የሻማ ማብራት እና የዕርዳታ ማሰባሰብ ሥነ ሥርዓት የተፈጸመውን ኢሰባዊ ድርጊት አውግዘው መንግስት የዜጎቹን ሰብአዊ መብት በአግባቡ እንዲያስከብር ጠይቀዋል።

በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይት እና የትብብር መድረክ ሊቀመንበር እና የሥነ ስርዓቱ ዋና አስተባባሪ አቶ አፈወርቅ ተፈራ የንጹሃን ዜጎች ህይወት እንዲቀጠፍ ንብረት እንዲወድም እና አያሌ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው እንዲፈናቀሉ ዋናው ምክንያቱ በአገሪቱ የተገኘው ለውጥ ባለቤት እኔ ነኝ የሚሉ ድርጅቶች ሽኩቻ እና ለውጡ እንዲደናቀፍ የሚፈልጉ ስልጣን ያጡ ኃይላት ናቸው ብለዋል። 

በኢትዮጵያ መሉ ለሙሉ የሕዝቦች ሰላም ዲሞክራሲ እና ሰብአዊ መብት እንደተረጋገጠ ተደርጎ በመገናኛ ብዙሃን ዕለት በዕለት ከፍተኛ የዜና ሽፋን መሰጠቱ መንግሥትም ሆነ ዓለም በመላ አገሪቱ ዜጎች በዘረኞች የሚደርስባቸውን ግድያ ኢሰባዊ ጥቃት እና መፈናቀል ችላ እንዲሉ አድርጓቸዋል ሲሉ አቶ ዓለማየሁ የተባሉ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የታደሙ የፍራንክፈርት ነዋሪ ስጋታቸውን ገልጸውልናል።  በቡራዩ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየታዩ ያሉ መሰል ብሄር ተኮር ጥቃቶች እና ግጭትን የሚቀሰቅሱ ጥላቻዎች ህጋዊ እልባት ካልተሰጣቸው እና መንግሥት ሕብረተሰቡ ማህበራዊ ተቋማት እና የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ አፋጣኝ መፍትሄ ካላገኙለት ለዜጎች ቀጣይ የመኖር ዋስትናም ሆነ ለአገሪቱ ሕልውና አደጋ ማምጣቱ አይቀርም ሲሉ የፕሮግራሙ አስተባባሪ አቶ አፈወርቅ ተፈራም መክረዋል። 

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ እንደታየው ከመንግሥት እውቅና ውጭ ራሳቸውን የክልል እና የመንደር ሹም አድርገው ነዋሪውን ቁምስቅል በሚያሳዩ ግለሰቦች ተደራጅተው በጦር መሳሪያ በሚዘርፉ በብሄር ማንነት ጥቃት በሚፈጽሙ በሚገድሉ ሴቶችን በሚደፍሩ እና ዜጎችን በሚያፈናቅሉ ሕገወጥ ወንጀለኞች ላይ እንዲሁም ሃላፊነታችውን በአግባቡ በማይወጡ እና ከወንጀለኞች ጋር ተባባሪ በሚሆኑ አመራሮች ላይ መንግሥት የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡም ነበሩ። 

በፍራንክፈርት ከተማ የቡራዩ እና አካባቢዋ የዘር ጥቃት ሰለባዎችን ለመዘከር አደባባይ የወጡ ኢትዮጵያውያን አሁን በአገሪቱ ለተገኘው ለውጥ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱት እና በየአካባቢው ለሚከሰቱ ብሄር ተኮር እና የደቦ ጥቃትም እንዲሁ ምክንያት ተደርገው የሚጠቀሱት በተለያየ ስያሜ የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች ከዚህ በኋላ በሚፈጽሙት የሕግ ጥሰት እንዲጠየቁ ሕጋዊ አደረጃጀት እንዲኖራቸው ጠይቀዋል።  በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ጥላቻን እና ግጭትን የሚቀሰቅሱ መልዕክቶችንም በህግ መዋጋት ይገባል ብለዋል። 

በአዲስ አበባ ዙሪያ የጥቃት ሰለባ ለሆኑ ወገኖች የሚካሄድ የመታሰቢያ ሥነ-ሥርዓት በሽቱትጋርት እና በመላው ጀርመን የተለያዩ ከተሞች መጠራቱን እና ለተፈናቃዮችም ዕርዳታ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር እንደሚኖርም አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል:: በሰሞኑ የአዲስ አበባው ጥቃት 58 ያህል ሰዎች መገደላቸውን አምኒስቲ ኢንተርናሽናል መግለጹ ይታወሳል:: የተባበሩት መንግሥታት ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ሪፖርት ደግሞ ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ብቻ በኢትዮጵያ ከ 1.4 ሚልዮን በላይ ዜጎች በእርስ በርስ ግጭት ሳቢያ ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን ጠቁሞ አገሪቱን ከዓለም በተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር በአንደኛ ደረጃ አስቀምቷታል:: ለችግሩም መንግሥትን ተጠያቂና ተወቃሽ አድርጓል። 

እንዳልካቸው ፈቃደ