1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትአፍሪቃ

በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት እንዲሻሻል ጥሪ ተላለፈ

ማክሰኞ፣ የካቲት 7 2015

በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት እንዲሻሻል ከፍተኛ የፖለቲካ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ። በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ የኢትዮጵያ የውይይትና መፍትሄ መድረክ እንዲሁም እምቢልታ ድርጅት በጋራ ባወጡት መግለጫ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ደረጃ አሣሣቢ በሆነ ሁኔታ መውደቁን አመልክተዋል።

https://p.dw.com/p/4NTvB
Äthiopien | Girma Birhanu
ምስል Privat

በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት እንዲሻሻል ከፍተኛ የፖለቲካ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።  በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ የኢትዮጵያ የውይይትና መፍትሄ መድረክ እንዲሁም እምቢልታ ድርጅት በጋራ ባወጡት መግለጫ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ደረጃ አሣሣቢ በሆነ ሁኔታ መውደቁን አመልክተዋል። ስለጉዳዩ ዶቸ ቨለ ያነጋገርናቸው ስዊድን የሚገኘው የጉተንበርግ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ግርማ ብርሃኑ በበኩላቸው፦ መፍትሔው የሀገሪቱን የፖለቲካ መርኅ ማስተካከል ነው ብለዋል። 

በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ጉዳይ በየጊዜው እያሽቆለቆለ የሄደባቸውን መሠረታዊ ምክንያቶች የዘረዘረው መግለጫው፣ ከፍተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ችግር መኖሩን አውስቷል።
የፖሊሲ ችግርና የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በትምህርት አስተዳደር ውስጥ መኖር፣ በኢትዮጵያ ለሚታየው የትምህርት ደረጃ መዳከም የተጠቀሰ ጉዳይ ሲሆን፣ የትምህርት አስተዳደር ከዚህ ሊጸዳ ይገባዋል ብሏል። 

መምህሩ የሚያገኘው ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ኑሮን ለማሸነፍ ሲል ባተሌ ስለሚሆን፣በትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩ ተጠቅሷል።
የተማሪዎች የኑሮ ደረጃን በተመለከተም፣መንግሥት በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የጀመረው ምገባ፣መልካም ነገር ሆኖ ይህ ፕሮግራም መስፋፋት እንዳለበት መግለጫው ጥሪ አቅርቧል።
የሀገሪቱ የፖለቲካ አለመረጋጋት በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ከፍተኛ ጥቁር ጥላ ጥሎበት እንደሚገኝም ተገልጿል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለትምህርት ትኩረት እንዲሰጥ በተጠየቀበት በዚሁ መግለጫ ላይ፣ በሀገሪቱ ውስጥ ፖለቲካዊ ለውጥ መጥቶ ብቁና ችግር ፈቺ ዜጎች ማፍራት እንደሚገባ አስገንዝቧል።
ስለጉዳዩ ዶቸ ቨለ ያነጋገርናቸው ስዊድን የሚገኘው የጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ፣ፕሮፌሰር ግርማ ብርሃኑ ሀገሪቱ ካለችበት የትምህርት ጥራት ሁኔታ አኳያ፣ በቅርብ ይፋ የተደረገው አስደንጋጭ የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት እንዳላስገረማቸው፣ ይናገራሉ።
«እኔ በበኩሌ በቅርብ ቀን የወጣዉ አስደንጋጭ ውጤት አላስገረመኝም፣ የምጠበቀው ነገር ነው። የተማሪዎች አማካይ ውጤት በየትምህርት ዓይነቱ ተዘርዝሮ ነበር። አጠቃላይ መረጃው እንግዲህ ከተፈተኑት ፣ ሃምሣ በመቶ እና በላይ ያስመዘገቡ ተማሪዎች ብዛት ከተፈተኑት መኻከል፣እንደ ሃገር ያለፉት ወደ ሰላሣ ሺህ የሚጠጉ ናቸው።በመቶኛ ሲኬድ ሦስት በመቶ ነው ማለት ነው። በጣም በጣም ትንሽ ነው።»
ፕሮፌሰር ግርማ ፣የትምህርት መዋቅሩ የብቃት ችግር እንዳለበት ጠቅሰው፣ ትልቁ ችግር ፖለቲካዊ ነው የሚለውን አጽንኦት ሰጥተውታል።
«ብዙዎች ደግሞ በዩኒቨርስቲ ደረጃ የሚቀጠሩትን ያየናቸው እንደሆነ፣ስልጣንም የሚይዙት፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንትነትም ይሁን ሌላ መዋቅር ውስጥ በትክክል በችሎታ አይደለም።አንድ ኅብረተሰብ ሊያድግ የሚችለዉ ቢሮክራሲው በሞያ ሲጠናከር፣ ቴክኒካል ዕውቀቶችን ያዳበሩ የሚያውቁ፣የተካኑ የሰው ኀይል ሲሟሉበት፣ በአንድ ተቋም ውስጥ ሊሆን ይችላል፣ዩኒቨርሲቲ ሊሆን ይችላል፣የትምህርት ማሠልጠኛ ተቋማት ሊሆኑ ይችላሉ፤እና ደግሞ ትልቁ ችግር ምንድን ነው ለፖለቲካ ብለህ በየዞኑ ዩኒቨርሲቲ መክፈት ማለት፣ጥራቱ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ አሁንም ጥፋት ነው እናም ትልቁ ችግር ፖለቲካ ነው።»
መፍትሔውም፣የሃገሪቱን ፖለቲካዊ መርዕና አስተዳደር ማስተካከል ነው ይላሉ መምህርና ተመራማሪው። «የተሳሳተ መርዕና የፖለቲካ አመራር በመሆኑ፣መፍትሔው የሀገሪቱን ፖለቲካ መርዕ ማስተካከል ነው።»
በጉዳዩ ላይ የትምህርት ሚኒስቴርን አስተያየት ለማካተት በተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብላቸውም፣ እስካሁን ምላሽ አላገኘንም።"

 

ታሪኩ ኃይሉ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ