1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ የስደተኞች ቁጥር ማሻቀብና የስደተኞች ቅሬታ 

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 14 2010

በኢትዮጵያ ካለፉት አመታት ጋር ሲነጻጸር የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተገልጿል።  አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅትና የተባበሩት መንግስታት  የስደተኞች ከፍተኛ  ኮሚሽን  እንዳመለከቱት በአሁኑ ወቅት  የስደተኞች ቁጥር ከ883 ሺህ በላይ ደርሷል።ይህም ካለፈዉ አመት የስደተኞች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ከ100 ሺህ በላይ ብልጫ አለዉ ተብሏል።

https://p.dw.com/p/2mQnD
Äthiopien Gambella Flüchtlingscamp
ምስል Reuters/D. Lewis

በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች ቅሬታ 

 ይሁን እንጅ በስደተኞቹ  በኩል በየመጠለያ ጣቢያወቻቸዉ ለህይወት የሚያስፈልጉ  አቅርቦቶች ላይ  ቅሬታወች ይሰማሉ።ድርጅቶቹ በበኩላቸዉ እየጨመረ የመጣዉን የስደተኞች ቁጥር የሚያስተናግድ  የገንዘብ ድጋፍ እጥረት  ለችግሩ መንስኤ ነዉ ብለዋል።ፀሐይ ጫኔ የሚመለከታቸዉን አካላት አነጋግራ  ተከታዩን ዘገባ አጠናቅራለች።

ኢትዮጵያ  በርካታ ስደተኞችን በመቀበል ከዩጋንዳ ቀጥላ በአፍሪካ  ሁለተኛ ስትሆን  ከነዚህ በርካታ ስደተኞች መካከል የደቡብ ሱዳንና ፣የሶማሌና የኤርትራ ስደተኞች በርካታ መሆናቸዉን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን፣ ዩኤንሲኤችአር ገልጿል።ከነዚህም ዉስጥ  በተለይ ከጎረቤት  ኤርትራና ከደቡብ ሱዳን የሚመጡ ስደተኞች  ቁጥር የመጨመር አዝማሚያ እያሳየ  ነዉ ተብሏል።  የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ክሱት ገብረእግዚአብሄር ለዶይቸ ቬለ እንደገለጹት በሀገሪቱ በአራቱም አቅጣጫ  በሚገኙ 26 የመጠለያ ጣቢያወች የስደተኞች ቁጥር በማሻቀብ ላይ ይገኛል።
«ትክክል ነዉ ቁጥሩ እየጨመረ ነዉ ያለዉ እንደሚታወቀዉ አቀማመጣችን በተለያዩ ሀገራት የተከበብን ነን።ስለሆነም በተለይ ከደቡብ ሱዳንና ከኤርትራ የሚመጡ ስደተኞች መምጣት ቀጥለዋል።በዚህም የተነሳ ከ883 ሺህ በላይ ስደተኞች ኢትዮጵያ ዉስጥ ተመዝግበዉ በየካምፖቹና በተለያዩ ቦታወች ይኖራሉ።»
የዘንድሮዉ አጠቃላይ የስደተኞች ቁጥር  ካለፈዉ  የጎርጎሮሳዊዉ 2016 አመት ጋር ሲነጻጸር በ100 ሺህ ብልጫ  ያለዉ ሲሆን በተለይ የደቡብ ሱዳን የእርስበእርስ ግጭት እንዲሁም ድርቅ ከሀገሪቱ የሚሰደዱ ሰወችን ቁጥር ከፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል ሲሉ አቶ ክሱት  ተናግረዋል።
በሌላ በኩል  አለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት፣ አይ ኦ ኤም  በአማካኝ   100 ኤርትራዉያን  ስደተኞችን ከጊዜያዊ  የማቆያ ስፍራ ወደተለያዩ መጠለያ ጣቢያወች  በየቀኑ እያጓጓዘ እንደሚገኝ ገልጿል።በዚህ ሁኔታ ካለፈዉ ሚያዚያ ወር ጀምሮ ከ 15 ሺህ በላይ ኤርትራዉያን ስደተኞች ማጓጓዙን የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ አለማየሁ ሰይፈስላሴ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።ይህም ካለፈዉ አመት ጋር ሲነጻጸር ቁጥሩ የመጨመር አዝማሚያ እያሳየ መምጣቱ ተገልጿል።                                                                                     «ከአምናዉ ጋር ሲነጻጸር ፤አምና አመቱን በሙሉ ወደኢትዮፕያ የገቡት ከ21 ሺህ በላይ ናቸዉ ።አሁን ገና አመቱ ሳያልቅ 20 ሺህ አልፏል።»
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በርካታ ስደተኞችን በማስተናገድ የምትወደሰዉን ያህልም  በርካታ ቅሬታወች በስደተኞች እንደሚቀርቡ ይነገራል።  ለህይወት የሚያስፈልጉ አቅርቦቶች መጓደል፣ የስደተኞች አመዘጋገብና ወደ ሶስተኛ ሀገር አላላክ  ከሚነሱት ቅሬታወች መካከል ይገኙበታል። በአቅርቦት በኩል የሚነሱ ቅሬታወች ትክክል መሆናቸዉን አቶ ክሱት ገልጸዉ የለጋሾች  ድጋፍ መቀነስ ለችግሩ  ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል። ለዘንድሮዉ አመት ከታቀደዉ 355 ሚሊዮን ዶላር ዉስጥ 26 ከመቶ ብቻ መገኘቱም ድርጅቱ  በነብስ አድን ስራ ላይ ብቻ እንዲሰማራ ሆኗል ነዉ የተባለዉ።
የስደተኞች ምዝገባን በተመለከተም ኢትዮጵያዉያን  የሌላ ሀገር ዜጋ መስለዉ  ወደ ስደተኛ ካምፖች ይገባሉ  በሚል ቅሬታ  በአንዳንዶች ዘንድ ሲነገር ይሰማል።የስደተኞች ምዝገባ በዋናነት በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የሚከናወን ቢሆንም ዩኤንሲኤችአር እንደቅርብ አጋርነቱ መሰል ችግሮች የመከሰት እድላቸዉ ጠባብ ነዉ ሲሉ አቶ ክሱት አስረድተዋል።                  «ስደተኞች በድንበር በኩል ነዉ የሚመጡት። ሰራዊቱ ተቀብሏቸዉ ከዚያ በኋላ  ለመንግስት የስደተኛ ሀላፊወች ያስረክባል።ከዚያ በኋላ መጥተዉ ምዝገባ የሚደረግባቸዉ ዝርዝር «ፕሮሲጀሮች» አሉ።ስለዚህ ከዚያ አልፎ ኢትዮጵያዊ እዚያ ይገባል የሚለዉ በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም፤አንድ ሰዉ ይገባል አይገባም 100 % ማረጋገጥ ባይቻልምእድሉ ግን በጣም በጣም ጠባብ ነዉ።»
እንደ ተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን  በሀገሪቱ ከሚገኙ አጠቃላይ የስደተኞች ቁጥር  ዉስጥ  416 ሺህ ደቡብ ሱዳናዉያን ፣252 ሽህ ሶማሌያዉያን እና  163 ሺህ የሚሆኑት ኤርትራዉያን ስደተኞች  ናቸዉ። ይህም በመቶኛ ሲሰላ የደቡብ ሱዳን ስደተኖች 47 በመቶ፣የሶማሊያ ስደተኞች ከ28 በመቶ  በላይና የኤርትራ ስደተኞች  ከ18 ከመቶ በላይ  ናቸዉ።  የመንን ጨምሮ የተለያዩ  ሀገራት ስደተኞች ደግሞ ቀሪዉን አምስት ከመቶ ይይዛሉ ተብሏል።

Eritrea Flüchtlingslager in der Region Tigrai Äthiopien
ምስል Reuters/T. Negeri
Eritrea Kinder im Flüchtlingslager in der Region Tigrai Äthiopien
ምስል Reuters/T. Negeri

ፀሐይ ጫኔ

አርያም ተክሌ