1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአፍሪቃ ዴሞክራሲ እየከሰመ ይሆን?

ሐሙስ፣ ኅዳር 20 2011

ፕሬዚደንቶች በስልጣን ለመቆየት እያሉ ሕገ መንግሥቱን  እስከቀየሩ እና የፖለቲካ ተቃዋሚዎቻቸውን ማሰር እስከቀጠሉ ድረስ  በፍሪቃ ዴሞክራሲ እየከሰመ በመሄድ ላይ ነው የሚል ህዝባዊ እምነት አለ። ይሁንና፣ ጠበብት በአህጉሩ ብዙ ጥሩ መልካም ዜና እንዳለ ይሰማቸዋል።

https://p.dw.com/p/39A78
Proteste im Kongo
ምስል Reuters/K. Katombe

ዴሞክራሲ እና አፍሪቃ

 ከውጭ ለሚመለከተው የአፍሪቃ ዴሞክራሲ ያብብ የነበረበት ጊዜ ያከተመለት ይመስላል። መሪዎች በስልጣን ለመቆየት እያሉ በስልጣን ዘመን ላይ ያረፈውን ገደብ መሰረዝ የዩጋንዳ ፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒን ለመሳሰሉ መሪዎች ተወዳጅ ስፖርት ሆኗል። የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላን የመሳሰሉ ሌሎች ደግሞ ተተኪያቸውን ለመምረጥ የምርጫውን ጊዜ በተደጋጋሚ አስተላልፈዋል። ባለፈው ሀምሌ ምርጫ በተደረገባት ዚምባብዌ ደግሞ ምርጫው ተጭበርብሯል የሚል ወቀሳ ተፈራርቂበታል። 
ይህም ቢሆን ግን፣ የቀድሞ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር ጋናዊው ኤማኑዌል ጊማን ቦዋዲን የመሳሰሉ ምሁራን አፍሪቃውያን ዴሞክራሲ እንደሚፈልጉ እና ለዚህም እንደሚሰሩ የሚጠቁም ብሩህ አመለካከት ነው የሰነዘሩት።  የአፍሪቃውያንን አስተያየት የሚከታተለውን የፓን አፍሪካን ምርምር መረብ ከመሰረቱት መካከል አንዱ የሆኑት  ጊማህን ቦዋዲን  በመጨረሻ በተካሄደው ጥናት እንደተመለከቱት፣ በጥናቱ ከተሳተፉ ከየአስሩ ሰባቱ  ዴሞክራሲን ይደግፋሉ።   80% ያህሉ ወታደራዊ አገዛዝን ውድቅ ያደርጋሉ። የፕሬዚደንታዊውን ስልጣን ገደብ ማንሳትም ተቀባይነት የለውም። 75% ሁለት የስልጣን ዘመንን ነው የሚደግፉት። የአፍሪቃ የዴሞክራሲ ፍላጎት ግን በቁጥር ብቻ ሳይሆን በዕለት ከዕለት ኑሮም እንደሚታይ ምሁሩ ገልጸዋል።  
« በመንገዶች፣ በፍርድ ቤቶች፣ በመገናኛ ብዙኃን፣ በኦንላይን፣ የተቃዋሚ ተሟጋቾች በሚያካሂዱት ዘመቻ ታየዋለህ። ዜጎች ለዴሞክራሲ መተከል፣ ለተጨማሪ ሰብዓዊ መብት እና ለተቸማሪ ፍትሕ ራሳቸውን ለትልቅ አደጋ ሲያጋልጡ ታየያለህ። »
በዩጋንዳ የስልጣኑን ገደብ ሲነሳ ግዙፍ ተቃውሞ ፣ በኮንጎ ፕሬዚደንት አንጻርም ህዝቡ በተደጋጋሚ ተቃውሞ ወጥቷል፣ በጋምቢያ ተቃዋሚዎች እና ያካባቢው ድርጅት ኤኮዋስ በምርጫ ቢሸነፉም ስልጣን አላስረክብም ያሉትን  ያህያ ጃሜን ሀገር ለቀው እንዲወጡ አስገድደዋል።
ሌሎች  ዴሞክራሲ እየጠፋ ነው የሚለውን አባባል የማይቀበሉ ምሁራንም አፍሪቃ ውስጥ የዴሞክራሲ  ጥያቄ በዐረብ ሀገራት የሕዝብ ዓመፅ ሳይጀመር በፊት ገና በ1990 ዎቹ ዓመታት በህዝብ እና በለጋሽ ሀገራት ግፊት እንደተጠየቀ እና በዘላቂነት እንደቀጠለ፣ አንዳንድ አፍሪቃውያን አምባገነኖችን ስልጣናቸውን እንዲለቁ ማድረጉን የጀርመን የፖለቲካ ጥናት ተቋም የአፍሪቃ ጉዳይ ክፍል ባልደረባ ማቲያስ ባሴዱ ያስታውሳሉ።   ይህ በዚህ እንዳለ፣ አንዳንድ ሀገራት ወደ ፈላጭ ቆራጩ አገዛዝ ገብተዋል፣ ሆኖም ግን፣ ሌላዋ የጊጋ ባልደረባ ሻሎተ ሄይል   ብዙ መሻሻል ተደረርጓላ ከሚሉት መካከል ናቸው።
« የፖለቲካ ስልጣን ሽግግር ዛሬ አዘውትሮ የሚደረገው በምርጫ አማካኝነት ነው።  ከኃይሉ ተግባር ወይም ከመፈንቅለ መንግሥት ይበልጥ በእጥፍ  ለማለት ይቻላል። ይህም ከነፃነት በኋላ በተከተለው የመጀመሪያው አሰርተ ዓመት የታየ ጉልህ  ልዩነት ነው።»
ጊማን ቦዋዲ እንደሚሉት ግን፣ አፍሪቃውያኑ የዴሞክራሲ ጥያቄ ስላቀረቡ ብቻ አዎንታዊ ምላሽ ያገኛሉ ማለት አይደለም። ከበጥናቱ ከተጠየቁት አፍሪቃውያን መካከል 51 ከመቶው ብቻ ሙሉ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባለባት ሀገር ውስጥ እንደሚኖር፣ 43 ከመቶው  ደግሞ በአገሮቻቸው የተተከለውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አጥጋቢ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል፣ ይህ እርግጥ ከሀገር ሀገር ይለያያል። በምሥራቅ አፍሪቃ 59 ከመቶው ሲሆን፣ በምዕራብ አፍሪቃ  46 ከመቶ ፣ በማዕከላይ አፍሪቃ ደግሞ 18 ከመቶ ብቻ ነው። 
በአፍሪቃ የዴሞክራሲ ጥያቄ ይሳካ ዘንድ ለጋሽ ሀገራት የዴሞክራሲያዊ መዋቅሮች እና መልካም አስተዳደር  በአፍሪቃ እንዲዳብር የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዳያቋርጡ፣ እንዲሁም፣ ፍልሰትን ለመቆጣጠር በጀመሩት ጥረታቸው  ርዋንዳ ወይም ግብፅን ከመሳሰሉ ፈላጭ ቆራጭ መንግሥታት ጋር እንዳይተባበሩ ጊማን ቦዋዲ ጠይቀዋል። ይሁንና፣ የምዕራባውያን ለጋሾች በጎ ፈቃድ ብቻውን ዴሞክራሲ በአፍሪቃ እንዲሳካ ማረጋገጫ ዋስትና አለመሆኑን የጊጋው ማቲያስ ባሴዱ አስረድተዋል።
«  በአፍሪቃ ዴሞክራሲ  በዋነኝነት  ከጀርመን ወይም ከሌሎች አውሮጳውያት ሀገራት በሚገኝ ድጋፍ ላይ ብቻ ጥገኛ ነው ብለን ማሰብ የለብንም።  ዴሞክራሲ  በራሳቸው በአፍሪቃውያን ጥረት ብቻ መሳካት ያለበት ነገር ነው። »

Uganda Proteste und Ausschreitungen in Kampala
ምስል Getty Images/AFP/I. Kasamani
Deutsches Institut für Entwicklungspolitik Emmanuel Gyimah-Boadi
ምስል DW/W. Mwaura

አርያም ተክሌ/ዳንየል ፔልስ

ሂሩት መለሰ