1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአፍሪቃ ያገረሸው የመገንጠል እንቅስቃሴ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 26 2013

አፍሪቃ ውስጥ የመገንጠል እንቅስቃሴዎች ዳግም ማንሰራራት መጀመራቸው መታየት መጀመሩን አንዳንድ ተንታኞች  መናገር ጀምረዋል። እነዚህ ወገኖች እንዲህ ያለው እሳቤ ሥረ መሠረቱ የቅኝ አገዛዝ ዘመን መሆኑን በመጠቆም ለዚህ የሚጋብዙ ግጭቶችም እያቆጠቆጡ መሆናቸውንም በማሳያነት ያነሳሉ።

https://p.dw.com/p/3mFdX
Karte Western Togoland EN

«ትኩረት በአፍሪቃ»


አፍሪቃ ውስጥ የመገንጠል እንቅስቃሴዎች ዳግም ማንሰራራት መጀመራቸው መታየት መጀመሩን አንዳንድ ተንታኞች  መናገር ጀምረዋል። እነዚህ ወገኖች እንዲህ ያለው እሳቤ ሥረ መሠረቱ የቅኝ አገዛዝ ዘመን መሆኑን በመጠቆም ለዚህ የሚጋብዙ ግጭቶችም እያቆጠቆጡ መሆናቸውንም በማሳያነት ያነሳሉ። ቶይን ፋሎላ በዩናይትድ ስቴትስ ቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰር ናቸው። ጉዳዩንን ወደኋላ በመውሰድ አውሮጳውያን ቅኝ ገዢዎች ከጎርጎሪሳዊው 1894 እስከ 95 ድረስ በርሊን ላይ ባካሄዱት አፍሪቃን ለየራሳቸው በሚያሻቸው መንገድ ከፋፍለው ለመቀራመት ያለመ ስብሰባቸው እና በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማለቂያ ከተፈጠረውን አጋጣሚ ጋር ያያይዙታል። በዚህም ከየሀገሩ ለመገንጠል የሚመኙ እንቅስቃሴዎች ስራቸው ቅኝ ግዛት ነው ብለው ያምናሉ። 
«ለሁሉም መነሻ የሆነው እሱ ነው፤ ምክንያቱም በጎርጎሪዮሳዊው 1885 እና በአንደኛው የዓለም ጦነርት ማለቂያ መካከል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩትን ቀደም ብለው የኖሩ መንግሥታትን በአንድ ላይ አሰባሰቡ፤ አሰባሰቡና 50 እና የሆኑ ሃገራት አደረጓቸው።»   
እሳቸው እንደሚሉት ያኔ በቅኝ ገዢዎቹ ሃገራት ሲደራጁ ነባራዊው ይዞታቸው ወይም ሃይማኖት እና የጎሳ ቅርበቶች ከግምት አልገቡም።  በዚህ ረገድ በምሳሌነት የሚያነሱዋቸው ሁለት በሀገርነት እውቅና የተሰጣቸውን ግዛቶች ነው።  አንደኛዋ አምባዞኒያ ፌደራል ሪፐብሊክ ወይም አምባ ላንድ በመባል ትታወቃለች።  በጎርጎሪዮሳዊው 1961 በተመድ ከካሜሩን ራስ ገዝ ፌደራል ግዛት ብሎ እውቅና ሰጥቷት ነበር። ሆኖም በካሜሩን ብዙሃን ፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ የፖለቲካ አመራር በነበረበት ከጎርጎሪዮሳዊው 1972 ግንቦት እስከ 1984 ጥር ወር ይህ ፌዴሬሽን ውድቅ ተደረገ። ከዚያን ጊዜ አንስቶም ካሜሩን ውስጥ በእንግሊዝኛ ተናጋሪዋ አምባዞኒያ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ግዛትን ገንጥሎ የመመስረቱ ፍላጎት እያደር የማንሰራራት ሙከራ ይታያል። በአሁኑ ጊዜም ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች የቋንቋ ተፅዕኖ እያሳደሩ ነው የሚሉ ወደ 20 የሚደርሱ የመገንጠል አጀንዳ ያላቸው ቡድኖች በስፍራው እንቀሳቀሳሉ። በቅርቡም ይህን ሃሳብ ከሚያራምዱ ታጣቂዎች አንዱ ቡድን ወደ ናይጀሪያ በመጠጋት  በሌሎች ሃገራት የሚኖሩ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ካሜሮናውያን የመገንጠል ሃሳባቸውን በዓለም አቀፍ መድረኮች እንዲያስተጋቡ ጥረት ሲያደርግ ታይቷል። ሁለተኛዋ ማሳያ ደግሞ ምዕራባዊ ቶጎላንድ ናት። በቮልታ ሐይቅና በጋና እና ጎጎ ድንበር መካከል የምትገኘው የጋና ቮልታ ግዛት አካል የነበረችው ምዕራባዊ ቶጎላንድ በቅርቡ ነው ራሷን የቻለች ሀገር ተደርጋ ለመገንጠል በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ነፃነቷን ያወጀችው። በስፍራው የመገንጠን አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱት ቡድኖች የጋና መንግሥት የተመድን በአደራዳሪነት ተቀብሎ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያሰጣቸው ጥያቄያቸውን ያቀረቡትም ባለፈው የጥቅምት ወር መጀመሪያ ቀናት ነው። ቶጎላንድ በጎርጎሪዮሳዊው 1884ዓ,ም በጀርመን ግዛት ጥበቃ ሥር የተመሰረች ናት። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ አካባቢውን ወረሩ። ጀርመን ከተሸነፈች በኋላ የቨርሳይ ውል ሲፈረም ምዕራባዊ ቶጎላንድ በብሪታንያ ስር ገባና የብሪታኒያ ቶጎላንድ ተባለ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የብሪታኒያ ቶጎላንድ በተመድ በሚሰይመው የብሪታንያ አስተዳደር ስር ሆነች። ቆየት ብላም በዚሁ የዘመን ቀመር 1957ዓ,ም በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ በአሁኗ ጋና አካልነት ተጠቃለለች። ይህ አብሮነት ግን አልዘለቀም። አሁን የመንገንጠሉ እንቅስቃሴ ጠንክሮ ወጥቷል። 
ምንም እንኳን በአፍሪቃ ውስጥ ለሚታየው የመገንጠል እንቅስቃሴ በምሳሌ ነት የተጠቀሱት የአምባዞኒያ እና ምዕራባዊ ቶጎላንድ ጉዳይ ከቅኝ ግዛት ጋር ቢገናኝም አንዳንዱ ግን መነሻው ከምን የመጣነው ለሚለው ግልፅ ማሳያ የማይገኝበት አጋጣሚ አለ ይላሉ በኔዘርላንድ የዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ሎቼ ደ ፍሪስ።  የታንዛኒያዋን የደሴት ግዛት ዛንዚባርን ወይም የአንጎላዋን ካቢንዳን በምሳሌነት ያቀርባሉ። 
«እዚህ ጋር በአንድ ወገን ከቅኝ ግዛት ውርስ ማግስት የመጣ ነገር አለ፤ በሌላ ወገን ደግሞ ግዛቱ የየትኛው አካል ነበር፤ እንዲሁም መቼ የየትኛው ወይም ሆኖም ከሆነ በሆነ ጊዜ በትክክል ከየት ወገን እንደነበር ለመለየት እንኳን ያደናግራል።»
«መገንጠል በአፍሪቃ ፖለቲካ» የተሰኘው መጽሐፍ  ተባባሪ ጸሐፊ ሎቼ ደ ፍሪስ በአፍሪቃ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የመገንጠል ሃሳብ አራማጆችን በፈርጅ በፈርጃቸው አሰባስበው ለማየት ጠንከር ያለ ተግዳሮት እንዳጋጠማቸው ይናገራሉ። በዚያ ላይ ለአሳታሚው የመገንጠል ሃሳብ የሚያራምዱት እንቅስቃሴዎችን ታሪካዊ አመጣጥ ጉዳዩ አልነበረም። እሱ መጽሐፉ ቢሆን የሚሻው እንቅስቃሴዎቹ እንዴት ተፈጠሩ የሚለውን የሚመረምር እንዲሆን ነው። 
የካሜሩኗ አምባዞኒያ
 ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የጀርመን የቅኝ ግዛት የነበረችው ካሜሩን በብሪታንያ እና በፈረንሳይ ስር ገባች። በጎርጎሪዮሳዊው 1961 የተካሄደው ሕዝበ ውሳኔም የብሪቲሽ ካሜሩንን ዕጣ ፈንታ ወሰነ፤ ሰሜናዊው ክፍሏ ከናይጀሪያ ጋር ተቀላቀለ፤ ደቡቡ ደግሞ ቀድሞ የፈረንሳይ ግዛት የሆነችው የካሜሩን ሪፐብሊክ አካል መሆን ፈለገ። አሁን በካሜሩን እንግሊዝኛ ተናጋሪዎቹ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በብዙሃኑ ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ተፅዕኖ ደርሶብናል በማለት ቅሬታ ያቀርባሉ። ውጥረቱ ተባብሶም ባስከተለው ግጭት ከሦስት ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። የካሜሩን ጦር ኃይልም ሆነ ለመገንጠል የሚንቀሳቀሱት ኃይሎች አንዳቸው ሌላቸውን በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ይከሳሉ። የዛሬ ሦስት ዓመት በምዕራብ በኩል ሁለቱ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ክፍለ ሃገራት ነጻነታቸውን አውጀናል በማለት ራሳቸውን የአምባዞኒያ ሪፐብሊክ ሲሉ ሰይመዋል። ለደ ፍሪስ አምባዞኒያውያን ለነጻነት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሕዝባቸውማንነት አደጋ ላይ ያለ በመሆኑ ከምር የሚወሰድ ጉዳይ ነው። 
ምዕራባዊ ቶጎላንድ እና ጋና
በካሜሩን እና ጋና መካከል የተሰናሰለ ታሪክ አl።። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊት በጀርመን ቅኝ ግዛት ሥር የነበረችው ቶጎ ጦርነቱ ሲያበቃ፤ በምዕራብ ብሪታኒያ በምሥራቅ ደግሞ ፈረንሳይ ተቀራመቷት። የብሪታኒያው ወገን ከዘመናዊቱ ጋና ጋር ተዋሃደ፤ ሆኖም በያዝነው ያመት መስከረም ወር ጀምሮ በምሥራቃዊ ጋና ማለትም በምዕራባዊ ቶጎላንድ ውጥረት ተቀነቀሰና የመገንጠን እንቅስቃሴውን የሚያራምዱት ኃይሎች ራሷን የቻለች ሉአላዊ ግዛትነቷን አወጁ። የመገንጠሉ ሙከራ የተጀመረው ከጎርጎሪዮሳዊው 12017 መባቻ አንስቶ ነበር። በዚህ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በጋና መንግሥት ውስጥ በቂ ውክልና የለንም ነው የሚሉት። ምዕራባዊ ቶጎላንድም እንደአምባዞኒያ በተመድ እውቅና ያልተሰጣቸው ፤ ያልተወከሉ መንግሥታትና ሕዝቦች ድርጅት በእንግሊዝኛ ምህጻሩ UNPO አካል ናቸው። 
ከዚህም ሌላ የቅኝ ግዛት ውርስ የሆነውን በየሀገራቱ የሚቀሰቀስ ግጭት መንግሥታት የሚያስተናግዱት መንገድ የመገንጠል እንቅስቃሴ መፈጠሪያ እንደሆነ ይታመናል። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው የናይጀሪያው የቢያፍራ ጦርነት ነው። ናይጀሪያ ከቅኝ ግዛትነት ነጻ ስትሆን ከጎርጎሪዮሳዊው 1967 እስከ 1970ዓ,ም ድረስ በደቡባዊ ምሥራቅ ናይጀሪያ በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ከግማሽ ሚሊየን የሚበልጥ ሕዝብ ማለቁ ይነገራል።
የታሪክ ፕሮፌሰሩ ቶይን ፋሎላ እንደሚሉት የጦርነቱ መንስኤ ከቅን ግዛት በኋላ የመጣው የአስተዳደር ብልሹነት ያስከተለው ነው። በተለይም በ1960ዎቹ ናይጀሪያ ውስጥ የፌደራል መዋቅርን ተግባራዊ ለማድረግ ከመሞከር ጋር ያያይዙታል።
«በ1960ዎቹ የፌደራል መዋቅርን ተግባራዊ ለመዳድረግ ሲፈለግ ነው ቀውሱ የመጣው። የፌደራል ገቢን እንዴት ማስተዳደር ይቻላል? የፌደራል ሥልጣንን እንዴት ማከፋፈል ይቻላል? አንድን ነገር በጣም ማዕከላዊ ለማድረግ ሲሞከር አዳዲስ ተፅዕኖ ያረፈባቸው ቀውሶች ይፈጠራሉ። ምክንያቱም በጣም ማዕከላዊ እያደረጉ የሚገፋ ወገን እንዳይኖር ማድረግ አይቻልም።» 
በዚህም ምክንያት የመገንጠል ስሜት በደቡብ ምሥራቅ እየደገጋገመ መቀጣጠሉንም ያስረዳሉ። አሁንም የቢያፍራን የእርስ በርስ ጦርነት የለኮሱ ሁኔታዎችም አሁንም እንዳሉም በአጽንኦት ነው ፕሮፌሰሩ የሚናገሩት። ጦስነቱም ከቅኝ ግዛት ውርስ ጋር ይያያዛል። ለተባባሪ ፕሮፌሰር ሎቼ ደ ፍሪስ ደግሞ ይህ የመገንጠል ስጋት የሚመደበው በመንግሥት ውስጥ የመሰማት ፍላቶች እና በፖለቲካው ረገድ ሚዛን ለመድፋት ከመፈለግ የሚመነጭ ነው። 
የታንዛኒያዋ ዛንዚባር
ዛንዚባር በታሪኳ ሁሉ በበርካታ ኃይሎች ስር ስትዳደር የኖረች ግዛት ናት። በመጀመሪያ የፖርቱጋል ቅኝ ገዢዎች ተፅእኗቸውን አሳረፉባት። በመቀጠል የኦማን ሱልጣኖች ከዚያም ብሪታንያ። ለተወሰነ ጊዜም ዛንዚባር በሱልጣን ስር ነጻ ግዛት ሆና ታውቃለች። ከብሪታን ቅኝ ተገዥነት ነጻ ከወጣች በኋላ በጎርጎሪዮሳዊው 1964 አብዮት ተካሄደ። ከጥቂት ወራት በኋላም ዛንዚባር ከታንጋኒካ ጋር ተዋሃደች እና የተባበረው የታንዛኒያ ሪፐብሊክ ተመሰረተ። 
ሆኖም ዛንዚባር የራሷ መንግሥትና ፓርላማ ያላት ከፊል ራስ ገዝ ሆነች። የብሔርተኝነት አስተሳሰብ በማኅበረሰቡም ሆነ በፖለቲካው ውስጥ አሁን ጠንክሮ የተያዘ ጉዳይ ነው። አንዳንድ ፓርቲዎችን ግን ዛሬም መገንጠልን አልመው ይንቀሳቀሳሉ። 
የአንጎላዋ ካቢንዳ 
የኤኮኖሚ ጥቅም ፍላጎትም ከአንድ መንገሥት ራስን ለመገንጠል ምክንያት የሚሆንበት ጊዜ አለ። በአብዛኛው ወደዚህ የሚገፋው ደግሞ ጥሬ ሀብት የማግኘት ዕድል፤ ይህን ዕድል በበላይነት የመቆጣጠር እንዲሁም ከትርፉም የመካፈል ፍላጎት ነው። ለዚህም ጥሩ ማሳያ የምትሆነው በፖርቱጋል የበላይ ጠባቂነት ስር የቆየችውና ወደ አንጎላ ተቆርጣ የተካለለችው ካቢንዳ የተባለችው ግዛት ናት። የዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ አካል ሆና ሳለ ባላት የተፈጥሮ ሀብት ምክንያት በቅኝ ገዢዎች ተቆርሳ የተለየች እና በኋላም ወደ አንጎላ ክፍለ ሀገርነት የተቀየረች ግዛት ናት። አንጎላ ከምታመርተው 60 በመቶው የነዳጅ ዘይት የሚገኘው ከካቢንዳ ነው። ለመገንጠል የሚንቀሳቀሱት ኃይሎች ማዕከላዊው መንግሥት ከፍተና ትርፍ የሚያገኘው ከዚህች ግዛት መሆኑ ያበሽቃቸዋል። ከዛሬ 20 ዓመት አንስቶ በመገንጠሉ እንቅስቃሴ ምክንያት በርካታ ደም አፋሳሽ ግጭቶች እና ጥቃቶች ደርሰዋል። 
ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት ሕግ የማስከበር ርምጃ በሚለው ትግራይ ክልልን ያስተዳድር ከነበረው የህወሀት ቡድን ጋር የጀመረው ውጊያ ተመሳሳይ የመገንጠል አጀንዳ እንዳዘለ እየተገለጸ ነው። ስለውጊያው አነሳስና ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ በሳምንቱ መጀመሪያ ለምክር ቤት አባላት ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጁንታ ያሉት የህወሃት ቡድን የመገንጠል ሃሳብ ካለው አይበጅም ብለው መናገራቸውን ገልጸዋል። 
የዶቼ ቬለዋ ዑተ ሽታንቩር ያነጋገረቻቸው ምሁራን በተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት የመገንጠል ጥያቄ እንዲነሳና እንዲጠናከር የቅኝ ግዛት ውርስ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ባዮች ናቸው።ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛች ሀገር መሆኗ ግልጽ ነው። ከኢትዮጵያ በይፋ 1985 የተገነጠለችው ኤርትራ ለ50 ዓመታት በቅኝ ግዛትነት መያዟ ይታወሳል። ትግራይ ላይ የሚታየው በየቱ ይመዘን ይሆን?

 Zanzibar House of Wonders | Haus der Wunder von Sansibar
ዛንዚባርምስል Anka Petrovic/Anka Agency International/picture alliance
Angola Cabinda & Luanda | Straße in Cabinda
የአንጎላዋ ካቢንዳምስል DW/B. Ndomba
Deutschland Kundgebung zum Unabhänigkeitstag von Ambazonia in Berlin
የአምባዞኒያ መገንጠል እንቅስቃሴምስል Imago-Imago/C. Spicker

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ