1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

በአፍሪቃ የህዋ ሳይንስ ተቋም ሰለመገንባት የመከረው አውደ ጥናት

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 8 2014

የጠፈር ምርምር ለአዳጊ ሀገራት የጤና፣ የግብርና ስራ፣የኢንዱስሪ፣ የማዕድን ምርት እንዲሁም የበይነመረብ አና የግንኙነት መስኮችን ለማሳደግ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው።ከዚህ አንጻር የህዋ ሳይንስ ከሀገራት ኢኮኖሚ እድገት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው።ይሁን እንጅ በአፍሪቃ ይህ ቴክኖሎጅ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው ያለው።

https://p.dw.com/p/44J4v
5th African Space Generation Workshop Logo
ምስል privat

በአውድ ጥናቱ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችም ተሳትፈዋል

በየዓመቱ በአፍሪቃ ደረጃ የሚዘጋጀው የአፍሪካ የጠፈር ትውልድ አውደ ጥናት  ሰሞኑን በደቡብ አፍሪካ ለአምስተኛ ጊዜ ተካሂዷል።ከመላው አፍሪቃ በርካታ የዘርፉ ባለሙያዎች በተሳተፉበት በዚህ አውደ ጥናት ጠንካራ የአፍሪካ የህዋ ሳይንስ ዘርፍን በመገንባት ላይ ያተኮረ ነበር ተብሏል። የአፍሪቃውያን የጠፈር ትውልድ በእንግሊዝኛው አጠራር «አፍሪካን ስፔስ ጀነሬሽን» አውደ ጥናት  በዚህ ወር መጀመሪያ በደቡብ አፍሪካ ስቴለንቦሽ የላቀ የጥናትና ምርምር ተቋም ተካሂዷል።  በጠፈር ትውልድ አማካሪ ምክር ቤት /SGAC/ እና በተባበሩት መንግስታት የጠፈር ትግበራ መርሃግብር  ድጋፍ  የተዘጋጀው ይህ አውደ ጥናት «ራስ አገዝ  የአፍሪካ የጠፈር ዘርፍን መገንባት» በሚል መሪ ቃል የተካሄደ ነው። ከ18 እስከ 35 ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ  ወጣት አፍሪቃውያን ባለሙያዎች በተሳተፉበት በዚህ አውደ ጥናት በአፍሪቃ የህዋ ሳይንስ ዘርፍ የወደፊት እጣ ፈንታ ውይይት ተካሄዷል።የጠፈር አማካሪ ምክር ቤት በአፍሪቃ ደረጃ አስተባባሪ ሆኖ በመስራት ላይ የሚገኘው ወጣት ትንሳኤ ዓለማየሁ የዓውደ ጥናቱ ተሳታፊ ነው።ትንሳኤ በዚህ አውደ ጥናት ሲሳተፍ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜው ሲሆን፤ይህ መሰሉ ውይይት በዘርፉ ዝቅተኛ ደረጃ ለሚገኙ ለሌሎች የአፍሪቃ ሀገራትም ሆነ ለኢትዮጵያ በትብብር ለመስራት ዕድል ይሰጣል ባይ ነው።
 

Äthiopien Tinsae Alemayehu
ምስል privat

በአፍሪቃና በዓለም አቀፍ ደረጃ 60 የሚሆኑ ተወካዮች በተሳተፉበት በዚህ መድረክ  ትንሳኤ  እንደሚለው  በጠፈር ህግ እና ፖሊሲዎች ፣በዓቅም ግንባታ ፤በጠፈር  የንግድ ስራና አጋርነት እንዲሁም የስራ ፈጠራ አቅሞችን በተመለከተ ውይይቶች ተካሂደዋል።በእነዚህ ውይይቶችም  የአፍሪቃን የጠፈር ምርምር ስለመደገፍ እና ወደፊት ለሚቋቋመው የአፍሪቃ የህዋ ሳይንስ ምርምር ጣቢያ አጋዥ ምክረ ሀሳቦች ቀርበዋል። ይህም እንደ ትንሳኤ ገለፃ ካለፉት ዓመታት ውይይቶች የዘንድሮውን የተለዬ ያደርገዋል።
በጎርጎሪያኑ 2019 ዓ/ም በአዲስ አበባ ከተማ በተዘጋጀው  የአፍሪቃውያን የጠፈር ትውልድ አውደ ጥናት አዘጋጅ ኮሚቴ አባል የነበረው እና የ2021  የአፍሪካ የጠፈር አመራር ሽልማት አሸናፊ  ወጣት ኪሩቤል መንበሩ ሌላው ተሳታፊ ነው።

5th African Space Generation Workshop Kirubel Menberu
ምስል privat

ኪሩቤል እንደሚለው ሽልማቱ በሀገሩ በህዋ ሳይንስ  ምርምር ዘርፍ ባደረገው አስተዋፅኦ እና በጠፈር አማካሪ ምክር ቤት ላደረገው ተሳትፎ የተሰጠ እውቅና ሲሆን፤ አውደ ጥናቱም የሽልማቱ አንድ አካል መሆኑን ይናገራል።የሰሙኑ አውደ ጥናት ከሀገር ውጭ ሲሳተፍ ለመጀመሪያ ጊዜው ሲሆን፤ ተሳታፊ በመሆኑም በግሉ በዘርፉ ካሉ ሰዎች ለወደፊቱ ሙያዊ አጋርነትን ለመመስረት፤እንዲሁም በህዋ ሳይንስ ዘርፍ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ሊጠቅሙ የሚችሉ  በርካታ ልምዶች አግኝቷል።
ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩንቨርሲቲ በኤለክትሮ ሜካኒካል ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪውን በዚህ ዓመት የያዘው ኪሩቤል፤ በዘርፉ የራሱን አስተዋፅኦ ለማድረግ እና በአውደ ጥናቱ ያገኘውን ተሞክሮ ወደ ተግባር የመለወጥ ዕቅድም አለው።
ከዚህ ዓመት ሶስት ተሸላሚ አፍሪቃውያን ወጣቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ኪሩቤል፤በሽልማቱ  እንዲሁም  በውይይቱ ተሳትፎ የተለያዩ ተሞክሮችን በማግኘቱ ደስተኛ  ቢሆንም፤ በሌላ በኩል በዘርፉ የበለጠ ለመስራት ትልቅ ሀላፊነት እንዳለበትም ይገልፃል።

Äthiopien Tinsae Alemayehu
ምስል privat

አውደ ጥናቱ ከጠፈር ምርምር ጋር በተያያዙ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊዎች አመለካከታቸውን፣ ሃሳባቸውን ፣ ዕውቀታቸውን  እንዲሁም ተሞክሮዎቻቸውን እንዲያካፍሉ ዕድል የሚሰጥ መድረክ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ተሳታፊዎቹ ከየመጡባቸው ሀገራት ልምድ የሚገኝበት ጭምር በመሆኑ በአውደ ጥናቱ በተለያዩ የአፍሪቃ ሀገራት በዘርፉ ያለውን ጅምር እና ተሞክሮ ለመረዳት ለኢትዮጵያውያኑ ተሳታፊዎች ዕድል ፈጥሯል።ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይም በአዘጋጇ ሀገር ደቡብ አፍሪቃ በህዋ ሳይንስ መስክ የግሉ ዘርፍ የሚያደርገው የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ትንሳኤ እንደሚለው ኢትዮጵያ ልትተገብረው የሚገባ ልምድ ነው።

Äthiopien Tinsae Alemayehu
ምስል privat

የጠፈር ምርምር ለአዳጊ ሀገራት የጤና፣ የግብርና ስራ፣የኢንዱስሪ፣ የማዕድን ምርት እንዲሁም የበይነመረብና የግንኙነት መስኮችን ለማሳደግ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው።ከዚህ አንጻር የህዋ ሳይንስ ከሀገራት ኢኮኖሚ እድገት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ይሁን እንጅ ከዓለም የእርሻ መሬት 60 በመቶ የሚሆነውን የያዘችው እና ኢኮኖሚዋም በአብዛኛው በዚሁ ዘርፍ ላይ የተመሰረተው  አፍሪቃ፤ ይህ ቴክኖሎጅ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው ያለው።በአህጉሪቱ  የህዋ ሳይንስ መርሀ ግብር ያላቸው  ሀገራትም  20 ብቻ ናቸው።በእነዚህ ሀገራትም ቢሆን፤አህጉሪቱ የሳተላይት ቴክኖሎጅ  ምርቶች ተጠቃሚ እንጅ አቅራቢ አይደለችም።ስለሆነም ችግሩን ለመፍታት በአፍሪቃም ሆነ በኢትዮጵያ ይህንን ቴክኖሎጅ ታሳቢ ያደረገ የአቅም ግንባታ ስራ ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ  ወሳኝ ነው ይላል። ወጣት ትንሳኤ።

ፀሐይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ