1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፋር ወጣቶች ጥያቄ እና እስር

ሐሙስ፣ ሰኔ 28 2010

«አሁን የሚታሰሩት ወጣቶች ብቻ አይደሉም።የልዩ የፖሊስ ኃይል አባልም ይገኝበታል። ከመካከላቸው ቤተሰብ እንዳይጠይቃቸው የተደረጉም አሉ። አሁን ከተያዙባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች ወደ ወሕኒ ቤት ተዛወረዋል»ይላሉ የዓይን ምስክሩ።ፖሊስ ሰዎችን ከማሰር በተጨማሪ በየቤቱ እየተዘዋወረ ወይ ደግሞ ሰው እየላከ በወጣቶች ላይ ይዝት እና ያስፈራራቸውም ነበር ይላሉ።

https://p.dw.com/p/30uNi
Äthiopien - Heißester Ort der Erde
ምስል DW/J. Martinez

በአፋር እሥር እና ወከባው ቀጥሏል መባሉ

በአፋር ክልል ባለፈው ሳምንት የተጀመረው የወጣቶች እሥር እና ወከባ መቀጠሉን የዓይን ምስክሮች ለዶቼቬለ ተናገሩ። የአፋር ነዋሪዎች ፣ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ከአፋር ህዝብ ጋር ሲወያዩ በነበረበት ወቅት ሰመራ ውስጥ ተጀመረ የሚሉት እሥር እና ወከባ በሌሎች አካባቢዎችም ቀጥሎ ሰንብቷል ይላሉ። በፖሊስ ጣቢያዎች ታስረው የነበሩት ሰዎችም የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው ወደ ወህኒ ቤት ተወስደዋል። ዶቼቬለ በጉዳዩ ላይ የክልሉን ባለሥልጣናት ለማነጋገር ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።  የአፋር ነዋሪዎች እንደሚሉት ፣ካለፈው ሐሙስ ወዲህ በክልሉ ሰዎች የሚታሰሩት ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ነው። የሚታሰሩትም «ክልላችን አሁን በኢትዮጵያ የተጀመረውን የለውጥ ጎዳና ትቀላቀል።»፣«ለዓመታት በሥልጣን ላይ የቆዩ የገዥው ፓርቲ አባላት ሃላፊነታቸውን ለወጣቱ ያስረክቡ» ማለታቸው ነው። ይህን ጥያቄ የሚያነሱ ወጣቶች መታሰር የጀመሩት ደግሞ ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ህብረተሰቡን ባወያዩበት ስብሰባ ላይ ለመካፈል ጠይቀው ከተከለከሉበት ጊዜ አንስቶ ነው። ዶቼቬለ ያነጋገራቸው እኚህ የአፋር ነዋሪ ከዚያን እለት አንስቶ የእሥር እና የማስፈራራቱ  ዘመቻ በሌሎች አካባቢዎችም ተጠናክሮ ቀጥሏል ይላሉ።  
አስተያየት ሰጭው እንደሚሉት አሁን የሚታሰሩት ወጣቶች ብቻ አይደሉም። የልዩ የፖሊስ ኃይል አባልም ይገኝበታል። ከመካከላቸው ቤተሰብ እንዳይጠይቃቸው የተደረጉም አሉ።
በአሁኑ ጊዜም ታሳሪዎቹ ከተያዙባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች ወደ ወሕኒ ቤት ተዛወረዋል ይላሉ የዓይን ምስክሩ ።ፖሊስ ሰዎችን ከማሰር በተጨማሪ በየቤቱ እየተዘዋወረ ወይ ደግሞ ሰው እየላከ በወጣቶች ላይ ይዝት እና ያስፈራራቸውም እንደነበር እኚሁ የአፋር ነዋሪ ተናግረዋል። ዶክተር ኮንቴ ሙሳ በውጭ የሚገኘው «የአፋር ህዝብ ፓርቲ»መሪ ናቸው።በርሳቸው አስተያየት የሰሞኑ የክልሉ መንግሥት እርምጃ ግልጽ መልዕክት ያስተላልፋል።
ዶክተር ኮንቴ ለዚህ ችግር አስቸኳይ መፍትሄ መፈለግ ይኖርበታል።ወጣቶችን እና ምሁራንን በክልሉ ችግሩ ላይ አነጋግሮ እና አወያይቶ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ የክልሉ ገዢ ፓርቲ የአሁኑ አካሄድ ችግሩ እንዲወሳሰብ እና እንዲሰፋ የሚያደርግ ነው ሲሉም የአፋሩ ነዋሪም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ስለ ጉዳዩ የአፋር ክልል ባለሥልጣናትን ለማነጋገር ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪዎች ብናደርግም ልናገኛቸው አልቻልንም።

Äthiopien - Heißester Ort der Erde
ምስል DW/J. Martinez

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ