1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከአዲስ አበባ ረጃጅም ፎቆች ጀርባ ያለው ቴክኖሎጅ

ረቡዕ፣ ኅዳር 21 2015

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ ረጃጅም ህንፃዎች እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች በአጭር ጊዜ ተገንብተው ለአገልግሎት ሲውሉ ይታያል።እነዚህ ህንጻዎች አሉሙኒየም ፎርም በተባለ ቴክኖሎጅ የተሰሩ መሆናቸውም ይነገራል።ለመሆኑ አሉሚኔም ፎርም ቴክኖሎጅ ምንድነው?ጠቀሜታውስ?

https://p.dw.com/p/4KHon
Äthiopien Addis Abeba Stadtansicht
ምስል Solomon Muchie/DW



የአሉሚኔም ፎርም ቴክኖሎጅ በዓለም ላይ ከጎርጎሪያኑ 1970ዎቹ  መገባደጃ ጀምሮ ሲሰራበት መቆየቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።ይህ የግንባታ ቴክኖሎጅ  በነዚህ ዓመታት ውሊያም ጄ ማሎን በተባለ ካናዳዊ መሐንዲስ  የተዘጋጀ ሲሆን በታዳጊ ሀገሮች አነስተኛ ዋጋ ያለው መኖሪያ ቤት ለመገንባት የሚያስችል ነው።ከ15 ዓመት በላይ በዘርፉ  ልምድ ያካበቱት እና በምስራቅ አፍሪቃዊቷ ሀገር ታንዛኒያ ተሻግረው በዚህ ቴክኖሎጅ የሰሩት  ኢንጅነር ፈቃዱ ቶልቻ እንደሚሉት ይህ ቴክኖሎጅ በኢትዮጵያ  ከአምስት አመት ያልበለጠ ታሪክ ያለው ሲሆን፤ ወደ  መገናኛ ብዙሃን የቀረበውም የኢትዮጵያ የፌድራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አዲስ በአበባ ከተማ ገርጂ አካባቢ የአሉሚንየም ፎርሞርክ የተጠቀመ አንድ ተቋራጭ በአጭር ጊዜ ገንብቶ ለአገልግሎት ባዋላቸው መንደሮች ነው።ለመሆኑ ይህ የአሉሚኔም ፎርም  ቴክኖሎጂ ማለት ምን ማለት ነው?ኢንጅነር ፈቃዱ ቶልቻ።-
«ፎርሞርክ ማለት ቅርጽ ማስያዣ ማለት ሲሆን። አሉሚንየም ፎርሞርክ ማለት ደግሞ ከ አሉሚንየም የተሰራ ቅርጽ ማስያዣ ማለት ነው።»ብለዋል። 
በግንባታው ዘርፍ የህንጻ መዋቅርን በኮንክሪት ወይም አርማታ መስራት የተለመደ ነው የሚሉት ባለሙያው፤ ይህንን ለግንባታ የሚውልን የሲሚንቶ፤ጠጠር፤ አሸዋ እና ውሃ ውህድ ወይም የተቦካ አርማታ የምንፈልገውን አይነት ቅርጽ ማስያዝ የሚቻለው በሶስት መንገድ ነው።በእንጨት በብረት እና በአሉሙኒየም ።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ  አዳጊ ሀገራት ለቅርፅ ስራ  የግንባታ ኢንዱስትሪው  በብዛት የሚጠቀመው  እንጨት እና የእንጨት ውጤቶችን ሲሆን በተለይ በኢትዮጵያ ባህርዛፍን ከሌሎች ነገሮች ጋር በመደባለቅ መጠቀም  የተለመደ ነው። የተሻለ አቅም ባላቸው የግንባታ ተቋራጮች ደግሞ አልፎ አልፎ ብረታብረትን ከእንጨት ውጤቶች ጋር  ይጠቀማሉ። የአሉሚኒየም ፎርሞርክ ወይም ቅርፅ ማስያዣ ግን  እንደ ባለሙያው በባህሪው ከነዚህ ሁሉ የተለዬ ነው። «አሉሚኔምን በባህሪው የሚለየው ላይት ሜታል ወይም ቀላላለ ነው።ቀላል ሆኖ ግን ጠንካራ ነው። »በማለት ገልፀዋል።
ከዚህ ባህሪው የተነሳ ቴክኖሎጅው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ይገልፃሉ። ከነዚህም ውስጥ ጊዜ ቆጣቢነቱ አንዱ ነው።እንደ ባለሙያው ገለፃ በአሉምኔየም የቅርፅ ስራ  ከህንጻው መዋቅር በተጨማሪ የውጭ እና የውስጥ ለውስጥ መከፋፈያ ግርግዳዎችን  ከህንጻው መዋቅር ጋር በአንድ ላይ መገንባት የሚያስችል ነው ።ያ በመሆኑ ተለምዷዊውን የግንባታ ስራ ቅደም ተከተል በማስቀረት የህንጻውን  መዋቅር፣ ግርግዳ እና የልስን ስራ  በተመሳሳይ ጊዜ በማከናወን በአጭር ጊዜ የተሻለ ጥራት ያለው ህንጻ መገንባት ያስችላል።
በሌላ በኩል በእንጨት እና  በብረት በሚሰሩ የቅርፅ ማስያዣ ስራዎች አርማታው የሚፈለገውን ቅርጽ ከያዘ  በኋላ ለማፍረስ  እና ለመነቃቀል ከአሉሚኔሙ ጋር ሲነፃፀር የሚወስደው  ጊዜ ብዙ ነው።በዚህ ሁኔታ በተለመደው የግንባታ አካሄድ ሁለት ወር የሚወስደውን አንድ የወለል ግንባታ ስራ በዚህ ቴክኖሎጅ /በአሉሚንየም ፎርም ወርክ/ግን በአስር ቀናት ውስጥ  ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ማድረስ እንደሚቻል ገለፀዋል።
በተለመደው የቅርፅ ማስያዝ /Formwork/ አሰራር በአንድ ህንጻ ላይ ተመሳሳይ ንድፍ እና መጠን (ስፋት) ባላቸው ቤቶች ኢንጅነሩ እንደሚሉት   ተመሳሳይ ስፋት እና ቁመት ያላቸው በሮች እና መስኮቶች ማግኘት አስቸጋሪ  ነው።ይህ ቴክኖሎጅ ግን ይህንን መሰሉን ችግር በማስቀረት ምንም አይነት የመጠን ልዩነት እንዳይኖር ያደርጋል። ይህም  በብዛት ለተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች  ተመሳሳይ በርና መስኮቶችን አምርቶ በመግጠም የግንባታ ስራን ያቀላል።
ከጥንካሬ  አንፃርም  እንደ ባለሙያው ገለፃ አሉሚኒየም ጠንካራ እና ቀላል ክብደት ያለው ቁስ በመሆኑ፤ ቅለቱ   በሰዎች ሸክም በቀላሉ ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ ሲረዳ ጥንካሬው ደግሞ በከፍተኛ ጫና (pressure ) የሚሞላውን አርማታ ሳይጣመም ወይም ቅርጹንና ቦታውን ሳይለቅ ይዞ እንዲቆይ ይረዳል። 
በዚህ ቴክኖሎጅ የህንጻው መዋቅር እና ግድግዳው አብሮ የሚሰራ በመሆኑ ከተለመደው የግንባታ ዘዴ የተሻለ ጥንካሬ እንዳለውም ተናግረዋል። የቤቶቹን ትክክለኛ ስፋት ፣ ውበት እና ጥራትም  ያስጠብቃል። 
ከወጭ አኳያም ከጥንካሬው የተነሳ አንድን የአሉሚኔየም ቅርፅ ማስያዣ ከ150 ጊዜ በላይ ደጋግሞ መጠቀም ይቻላል። አገልግሎቱን ከጨረሰ በኋላም ለሌላ አገልግሎት መልሶ መሸጥ ወይም መጠቀም ስለሚቻል ምንም እንኳ የመግዣ ዋጋው ከፍተኛ ቢሆንም ብክነትን ያስቀራል።  
ከአካባቢ ጥበቃ አንፃርም እንጨት እና የእንጨት ውጤቶችን መጠቀምን በማስቀረት  ደን እንዳይጨፈጨፍ ይረዳል። አገልግሎቱንም ከጨረሰ በኋላም መልሶ ለሌላ አገልግሎት ስለሚውል ቆሻሻ ሆኖ አካባቢን አይበክልም።
ከላይ ከተዘረዘሩት ጥቅሞቹ ባሻገር  በቂ እና አስተማማኝ ክህሎት ያለው የሰው ሀይል በማይገኝባቸው ታዳጊ ሀገራት በአጭር ጊዜ ስልጠና ማንኛውም ሰው በቀላሉ ሊሰራው የሚችል በመሆኑም እንደ ባለሙያው ቴክኖሎጅው ተመራጭ ነው። 
ከዚህ አኳያ በታዳጊ ሃገራት ለሚከናወኑ አዳዲስ ግንባታዎች የአሉሚንየም ፎርምወርክ ስራ በጣም አስፈላጊ ነው። በኢትዮጵያም በተለይም በአዲስ አበባ  የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ መንግስት ለዘረጋቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ይህ ስራ አዋጭ መሆኑንም አመልክተዋል። 
ከቅለቱ እና ከጥንካሬው የተነሳ ለአውሮፕላን ውጫዊ አካል  ግንባታ አሉሙኒየም ዋነኛ ግባት መሆኑን የገለፁት ባለሙያው፤ ለህንፃ ግንባታ አገልግሎት የሚውለውም ተመሳሳይ የአሉሚኒየም አይነት በመሆኑ በዋጋ ደረጃ ውድ ነው።ከዚህ የተነሳ ለከፍተኛ ሪልስቴት አልሚዎች እና ለመንግስታት ካልሆነ በቀር በግለሰቦች  ደረጃ ለመግዛት አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን ከሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንጻር ለማህበረሰቡ በሰፊው ተደራሽ ለማድረግ በመንግስት እና በባለሃብቶች በኩል በኪራይ መልክ ቢቀርብ መፍትሄ መሆኑን ኢንጅነር ፈቃዱ ቶልቻ ጠቁመዋል። 

Äthiopien | Straßenszene in Addis Abeba
ምስል Eshete Bekele Tekle/DW
Äthiopien, Bahir Dar | Unfertiges Gebäude
ምስል Alemnew Mekonnen/DW
Äthiopien | Ingenieur Fekadu Tolcha
ኢንጅነር ፈቃዱ ቶልቻ ጋሪምስል Fekadu Tolcha

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ፀሀይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ