1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"ለኮቪድ ጽኑ ሕክምና የሚሆኑ አልጋዎችና ማሽኖች በአዲስ አበባ በሙሉ ተይዘዋል"-ዶክተር ያዕቆብ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 6 2013

በአዲስ አበባ የኮቪድ ሕሙማን ቁጥር በመብዛቱ አልጋ እና ለአተነፋፈስ እገዛ የሚያደርግ ማሽን ለማግኘት ወረፋ መያዝ ጀምረዋል። በኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር የሕክምና አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ያዕቆብ ሰማን "የኮቪድ ሕሙማን ተቀብሎ ለማስተናገድ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ገደማ በጣም እየታገልን ነበር። አሁን ከአቅማችን በላይ እየሆነ ነው" ብለዋል

https://p.dw.com/p/3mlDi
Äthiopien | Coronavirus | Friedhof in Wingate nördlich von Addis Abeba
ምስል Reuters/T. Negeri

በአዲስ አበባ የኮቪድ ጽኑ ሕሙማን ቁጥር እየጨመረ ነው

በኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር የሕክምና አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ያዕቆብ ሰማን መረጃ መሠረት በአዲስ አበባ ብቻ በትናንትናው ዕለት "ለኮቪድ የተዘጋጁ መተንፈሻ ማሽኖች በታካሚ ተይዘው 13 ሕሙማን ማሽን ለማግኘት ወረፋ" ይጠብቁ ነበር። ዶክተር ያዕቆብ እንደሚሉት "ለኮቪድ ጽኑ ሕክምና የሚሆኑ አልጋዎች እና ማሽኖች አዲስ አበባ ዉስጥ ሙሉ በሙሉ ተይዘዋል።"

"በአሁን ሰዓት በተለይ አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ ሰዎች ወደ ጽኑ መታመም እየገቡ ነው። በጽኑ ሲታመሙ መጀመሪያ የጽኑ ሕሙማን ሕክምና ክፍል ውጥ ነው የሚገቡት። አለፍ ካለ ደግሞ በማሽን ታግዘው ወደ መተንፈስ ይገባሉ። ሕሙማን ተቀብሎ ለማስተናገድ፤ በተቻለ አቅም በማሽን መረዳት ያለባቸው ሰዎች እንዲረዱ ለማድረግ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ገደማ በጣም እየታገልን ነበር። ነገር ግን አሁን ከአቅማችን በላይ እየሆነ ነው ማለት እችላለሁ" የሚሉት ዶክተር ያዕቆብ "ነጻ የሚሆን ማሽን እስከሚገኝ ድረስ ማሽን የሚጠብቁ ብዙ ሰዎች እየተፈጠሩ ነው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

በዶክተር ያዕቆብ ማብራሪያ መሠረት ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል ከሚገቡ የኮቪድ ታማሚዎች 59 በመቶው ይሞታሉ።  በኮቪድ ሕመም ምክንያት በሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ ላይ የሚቆዩ "ሰዎች የመትረፍ ዕድላቸው ከ10 በመቶ አይበልጥም።"

የጤና ምኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ባለፈው ሐሙስ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በኢትዮጵያ "በየቀኑ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ወደ ሕክምና ማዕከል ከሚገቡት ታማሚዎች ውስጥ በአማካይ 305 የሚሆኑት ጽኑ ሕክምና ክፍል ይገኛሉ።" ከ40 እስከ 45 የሚሆኑት ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ የሚጠቀሙ ናቸው።

ወረርሽኙ በኢትዮጵያ በበረታባቸው ወራት በየቀኑ በሚደረጉ ምርመራዎች በተሕዋሲው መያዛቸው የሚረጋገጥ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም አብዛኞቹ ወጣት ከሚባለው የማሕበረሰብ ክፍል የሚመደቡ እንደነበሩ ዶክተር ያዕቆብ ሰማን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ዶክተር ያዕቆብ እንደሚሉት በመጀመሪያዎቹ አምስት ወራት በኮሮና ከተያዙ ሰዎች መካከል እስከ 75 በመቶው ምልክት የማያሳዩ ነበሩ።  በወቅቱ ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር "ጥቂት ነበሩ" የሚሉት ዶክተር ያዕቆብ "አሁን አሁን ጽኑ ሕሙማን ክፍል ከሚገቡ ሰዎች ውስጥ ከ70 በመቶ ገደማ በላይ የሚሆኑት ከ55 አመት በላይ ያሉ ሰዎች ናቸው" ብለዋል።

 "በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ዕድሜያቸው ትልልቅ፤ እናት አባት የሆኑ ሰዎች ሲሆኑ ቀድሞም በሌሎች ሕመሞች የተያዙ የመሆን ዕድል አላቸው። እኛ አገር ብዙ ሰው የጤና ምርመራ አያደርግም። ስኳር ይኑርበት፣ ደም ግፊት ይኑርበት የሚያውቅ ሰው ጥቂት ነው። ሁሉም ሰው አያውቅም። ስለዚህ ጤነኛ ነኝ ብሎ ነው የሚገምተው። በበሽታው ሲያዝ ቶሎ  በጽኑ የመታመም ዕድሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ እየሆነ መጣ። ስለዚህ አሁን የሚያዙ ሰዎች ጥቂት ቢሆኑም፤ ዕድሜያቸው ከፍ ያሉ፤ በጽኑ ለመታመማቸው ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ የጤና ችግር ያላቸው ሰዎች እየሆኑ መጡ ማለት ነው።" ሲሉ አብራርተዋል።

"አሁን ባለው ኹኔታ በመካከለኛ ደረጃ የታመሙ ሰዎችን ለማከም ለኮቪድ ሕሙማን የተዘጋጁ ኦክስጅን መስጠት የሚችሉ አልጋዎች" እጥረት አለመኖሩን የሚናገሩት ዶክተር ያዕቆብ የጽኑ ሕሙማን ጉዳይ ግን በዚሁ ከቀጠለ ሊከፋ እንደሚችል ለዶይቼ ቬለ ሥጋታቸውን አጋርተዋል። ይኸ ለመደበኛ ሕክምና የተደለደሉ የአተነፋፈስ እገዛ ማድረጊያ ማሽኖችን ለኮቪድ ሕሙማን እስከ መመደብ ሊደርስ ይችላል።

ዶክተር ያዕቆብ ሰማን "ምን አልባት በዚህ ሁኔታ የምንቀጥል ከሆነ የተለያዩ ውይይቶች እያደረግን ነው። የተወሰኑ ማሽኖች ከመደበኛው አገልግሎት ቀንሰን ወደዚህ ማምጣታችን አይቀርም።" ሲሉ  በመደበኛ የጤና ግልጋሎቶች ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ጫና ጠቁመዋል።

"ማሕበረሰቡ ኮቪድ የለም ወደሚል ድምዳሜ እየመጣ ነው።  በጤና ሚኒስቴር ያለ አፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ አገልግሎት ሊሰጥ እንደማይገባ የሚያዝ መመሪያ ወጥቷል። ማስክ ያላደረጉ ሰዎች በጣም በብዙ ስብሰባዎች [ሲሳተፉ] ሚዲያዎቻችን ቀርጸው ያስተላልፋሉ። በባንክ፣ ሆቴል፣ ምግብ ቤት ያለ ማስክ አገልግሎት ይሰጣል።" የሚሉት ዶክተር ያዕቆብ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ የመጠቀም ባህል የመቀነስ አዝማሚያ እንዳሳየ ገልጸዋል። 

"እንዲያውም አዲስ አበባ ውስጥ ማስክ የመጠቀም ባህል ከአንድ ወር በፊት ወደ 78 በመቶ ገደማ ነበረ። አሁን ከ55 በመቶ በታች እየወረደ ነው። ክልሎች አካባቢ እስከ 30 አንዳንዴም 20 በመቶ የሚሆንባቸውም ከተሞች አሉ። በተለያዩ ቦታዎች ሰላማዊ ሰልፎች አሉ። አሁን ያለው ወቅታዊ የአገራችን ሁኔታም ወደ ሌላ ነገር እንድናተኩር ሊያደርገን ይችላል። አሁን ያለው ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነው ብዬ ነው የማስበው። በዚህ የሚቀጥል ከሆነ በጣም ከባድ ነገር ሊጠብቀን ይችላል። የሁለተኛ ዙር ወረርሽኝ ምልክትም ሊሆን ይችላል ብለን እየተጠና ነው።" ብለዋል። 

መፍትሔው ምንድነው?

ዶክተር ያዕቆብ በእርግጥም የኮሮና ወረርሽኝ "አስጊ ሁኔታ ላይ" እንደሚገኝ አምኖ በመቀበል የመከላከያ ዘዴዎችን በትክክል መተግበር አንዱ መፍትሔ እንደሆነ አስረድተዋል። ይኸም ማለት የመንግሥትም ሆኑ የግል ተቋማት የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ለማይጠቀሙ ደንበኞቻቸው አገልግሎት ሊሰጡ አይገባም። ለዚህም የሕግ አስፈፃሚ አካላት የጤና ሚኒስቴር ያወጣው መመሪያ ተግባራዊ እንዲሆን ማስገደድ ይጠበቅባቸዋል። ሰዎች በሚሰበሰቡባቸው መርሐ ግብሮች ወረርሽኙን ለመግታት የሚያግዙ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛዎች ያላደረጉ ሰዎች ሊታደሙ አይገባም ያሉት ዶክተር ያዕቆብ መሪዎች የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ እየተጠቀሙ አርዓያ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።

ሌላው ተስፋ የበረታ ምጣኔ ሐብታዊ አቅም ያላቸው የሚሻሙበትን የኮሮና ክትባት ለኢትዮጵያ ለማድረስ መሞከር ነው። "ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የክትባት ጥምረት ወይም ጋቪ አባል አገር ናት። በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ውድድር ያለበት ጉዳይ ይሆናል። ግን የኮቪድ ክትባት ሥርጭት ሲጀመር ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ከሚያገኙ አገሮች ውስጥ ሆና ክትባቱን እንድታገኝ እንደ መንግሥት እንደ ጤና ሴክተር እየሰራን ነው። እሱን መግፋት እና ክትባት የማግኘት ሒደቱን ማፍጠን ሌላኛው አማራጭ ነው የሚሆነው።" የሚሉት ዶክተር ያዕቆብ ምን አልባት ወረርሽኙ የሚበረታባቸውን አካባቢዎች ለይቶ የእንቅስቃሴ ገደብ ማድረግ ሊያስፈልግ እንደሚችል እምነታቸው ነው።

"እንደ ሀገር ይኸን ማድረግ አንችልም። አሁንም እንደዚያ የሚጠቁም ነገር የለንም።" ያሉት ዶክተር ያቆብ "የመጨረሻው አማራጭ ወረርሽኝ የሚኖርባቸው አካባቢዎች ለይቶ መዝጋት ወይም እንቅስቃሴን መገደብ ሊያስፈልግ ይችላል።" ብለዋል።

የጤና ሚኒስቴር እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ይፋ ባደረጉት መግለጫ መሠረት በትናንትናው ዕለት በተደረጉ ምርመራዎች 473 ሰዎች በኮሮና መያዛቸው ተረጋግጧል። በዕለቱ 3 ሰዎች ከኮሮና በተያያዘ ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን 297 ሰዎች በጽኑ የታመሙ ናቸው።

እሸቴ በቀለ