1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአዲስ አበባ የቆሻሻ ክምር ተደርምሶ በርካቶች ሞቱ

እሑድ፣ መጋቢት 3 2009

በአዲስ አበባ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በደረሰው የቆሻሻ ክምር መደርመስ የሟቾቹ ቁጥር ቢያንስ 46 መድረሱን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። የአዲስ አበባ ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ዳግማዊት ሞገስ እንደተናገሩት የሟቾች ቁጥር በመጪዎቹ ሰዓታት ሊጨምር ይችላል። አብዛኞቹ ሟቾች ሴቶች እና ሕፃናት ነበሩ ብለዋል።

https://p.dw.com/p/2Z4DA
Äthiopien Erdrutsch
ምስል picture-alliance/AP Photo/E. Meseret

የአካባቢው ነዋሪዎች በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም መሞት አሊያም መትረፋቸው አለመታወቁን ተናግረዋል፡፡ 
ለአዲስ አበባ ከተማ የቆሻሻ መጣያ በሆነው በዚሁ ስፍራ ይኖሩ በነበሩ ሰዎች ላይ የመደርመስ አደጋው የደረሰው ትናንት ቅዳሜ ምሽት ሁለት ሰዓት አካባቢ ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዳግማዊት ሞገስ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት የቆሻሻ መጣያ ስፍራው ሰፊ ስፍራን የሚሸፍን በመሆኑ የሟቾቹ ቁጥር አሁን ካለውም ሊጨምር ይችላል፡፡  
በአደጋው በርካታ ቤቶች በቆሻሻው ክምር መዋጣቸውን አሶሴትድ ፕሬስ ከስፍራው ዘግቧል፡፡ የዜና አገልግሎቱ ያነጋገራቸው አሰፋ ተክለሃይማኖት የተባሉ ነዋሪ ወደ 150 የሚጠጉ ነዋሪዎች አደጋው በደረሰበት ቦታ ነበሩ ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ 37 ሰዎችን ከአደጋው ማትረፍ መቻሉን እና ተጎጂዎቹ የህክምና እርዳታ እያገኙ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ 
የአሶሴትድ ፕሬስ ዘጋቢ ከቆሻሻው ክምር ስር የወጣ የአራት ሰዎች አካላት በአምቡላንስ ሲወሰድ ተመልክቷል፡፡ ስድስት ኤክስካቫተሮች ከቆሻሻ ክምሩ ውስጥ ተጨማሪ ሰዎች ለማግኘት ሲቆፍሩ ነበር፡፡ ተበጁ አስረስ የተባለች የአካባቢው ነዋሪ ቆፋሮው ወደሚካሄድበት ቦታ እያመላከተች “ቤቴ እዚያ ጋር ነበር፡፡ መደርመሱ ሲከሰት እናቴ እና ሶስት እህቶቼ በውስጡ ነበሩ፡፡ የሁሉንም ዕጣፈንታ አላወቅኩም”ብላለች።
አደጋው በደረሰበት ቦታ አዛውንቶች ሲያለቅሱ የታዩ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በአካባቢው ቆመው የቤተሰቦቻቸውን እና ወዳጆቻቸውን መጨረሻ ለማወቅ በጭንቀት ሲጠብቁ ተስተውለዋል፡፡ በአካባቢው የነበረው የቆሻሻ መጣያ አዲስ አበባ ከተማን ለ50 ዓመታት ያገለገለ ሲሆን ባለፉት ዓመታት ግን አገልግሎቱ ቆሞ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቦታው እንደገና ቆሻሻ መጣል መጀመሩ ለአደጋው መንስኤ ሳይሆን እንዳልቀረ የአካባቢው ነዋሪ ለአሶሴትድ ፕሬስ ተናግረዋል፡፡ 

Äthiopien Erdrutsch
የአካባቢው ነዋሪዎች በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም መሞት አሊያም መትረፋቸው አለመታወቁን ተናግረዋል፡፡ ምስል picture-alliance/AP Photo/E. Meseret

ተስፋለም ወልደየስ

ልደት አበበ