1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአዲስ አበባ ከተማ ፀጥታ ጉዳይ የፖሊስ መግለጫ

ሐሙስ፣ መጋቢት 8 2014

በርካታ ወጣቶች በተለያዩ ጊዜያት በገፍ ለእስር የተዳረጉባት አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን በስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸሙ ስኬትማ ያላቸውን ጉዳዮች  ገለጠ። ኮሚሽኑ ለሽብር እና ለተለያዩ ወንጀሎች ሊውሉ ነበሩ ያላቸውን በርካታ የጦር መሣሪያዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉንም ዐስታውቋል።

https://p.dw.com/p/48drA
Äthiopien Stadtbild Adis Abeba mit Schriftzug
ምስል Seyoum Getu/DW

በርካታ ጦር መሣሪያዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ዐስታውቋል

በርካታ ወጣቶች በተለያዩ ጊዜያት በገፍ ለእስር የተዳረጉባት አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን በስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸሙ ስኬትማ ያላቸውን ጉዳዮች  ገለጠ። ኮሚሽኑ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ እንዳመለከተው፦ ለሽብር እና ለተለያዩ ወንጀሎች ሊውሉ ነበሩ ያላቸውን በርካታ የጦር መሣሪያዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉንም ዐስታውቋል። የፖሊስ ደንብን የጣሱ እና ጥፋተኛ ያላቸውን 146 የፖሊስ አባላት ማሰናበቱንም ገልጧል። ሰሞኑን የአዲስ አበባ ወጣቶች በገፍ ይታሰራሉ ስለመባሉ ከጋዘጠኞች ጥያቄ የተነሳላቸው ኮማንደር ፋሲካ፦ «የሚታፈስ ወጣት የለም» ሲሉ መልስ ሰጥተዋል። ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከ30 በላይ አባላቱ እና ሌሎች ወጣቶች መታሰራቸውን ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።  

የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳሬክተር ኮማንደር ፋሲካው ፋንታ ለመገናኛ ብዙኃን ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት በከታማ አስተዳደሩ ፖሊስ ሥራ በበዛበት ባለፉት ስድስት ወራት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ለጸጥታ ስጋት የነበሩ የጦር መሣሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመልክተዋል። 

Äthiopien | Stadtansicht Addis Abeba
ምስል Seyoum Getu/DW

ሕገወጥ የጦር መሣሪያን በመዲናዋ ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረትም 2 ሺህ 300 ክላሽንኮቭ ከ76 ሺህ በላይ መሰል ጥይቶች፣ 23 ሺህ ልዩ ልዩ ሽጎጦች ከ193 ሺህ ጥይቶቹ እንዲሁም ከ600 በላይ ሌሎች የጦር መሳሪያዎች ፈቃድ እያላቸው ድጋሜ ምዝገባ ሲደረግ፡ 12 ሺህ የሚጠጉ ክላሽንኮቭ፣  17 ሺህ ሽጉጦች እንዲሁም 43 ልዩ ልዩ የጦር መሣሪያዎች ከመሰል ጥይቶቻቸው ጋር በአዲስ እንዲመዘገቡ ሆኗልም ተብሏል። በዚህም የላቀ ለውጥ መገኘቱን ያመለከቱት ኮማንደሩ በመዲናዋ የተደረጉ ሁነቶችን በስኬት መጠናቀቅ በማሳያነት አንስተዋል፡፡ የፖሊስ ደንብ የጣሱ አባላት ላይም በዚሁ ጊዜ ርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል፡፡ ወንጀልን ከመቀነስ ጋር በተያየዘም ለኅብረተሰቡ ስጋት ናቸው የተባሉ ወንጀሎችን ለመቆጣጠር ጥረት መደረጉ ተመላክቷል።
 
በመዲናዋ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ የትምህርት ዘርፉ ደህንነት እንዲረጋገጥም ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸው የተነገረ ሲሆን በሕግ የተፈቱ ተጠርጣሪዎችን ፖሊስ የሚያስርበት እና ሰሞኑን የአዲስ አበባ ወጣቶች በገፍ ይታሰራሉ መባል ላይ ከጋዘጠኞች ጥያቄ የተነሳላቸው ኮማንደር ፋሲካ፦ «የሚታፈስ ወጣት የለም» ብለዋል። ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከ30 በላይ ወጣቶች መታሰራቸውን መዘገቡ የሚታወስ ነው።  

ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ