1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአዲስ አበባ አማራጭ የመኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት

ማክሰኞ፣ መጋቢት 14 2013

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለ2005 ዓ.ም. የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎች አማራጭ ያለውን የመኖሪያ ቤት የግንባታ ሃሳብ ማቅረቡን ገለፀ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ተመዝጋቢዎቹን በጋራ ሕንፃ መኖሪያ ቤት የህብረት ስራ ማኅበር ላደራጅ ነው ብሏል።

https://p.dw.com/p/3r0p5
Addis Abeba Dr. Meskerem Zewde
ምስል Seyoum Getu/DW

ከ4 እስከ 21 ፎቅ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ይገነባሉ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለ2005 ዓ.ም. የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎች አማራጭ ያለውን የመኖሪያ ቤት የግንባታ ሃሳብ ማቅረቡን ገለፀ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃኑ ይፋ ባደረገው እቅዱ የመንግስት ቤቶቹን ገንብቶ የማስተላለፍ አቅም ካለው ፍላጎት ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ተመዝጋቢዎቹን በጋራ ሕንፃ መኖሪያ ቤት የህብረት ስራ ማኅበር ላደራጅ ነው ብሏል። አዲስ ምዝገባ እንደማይፈጽም፤ የመረጃ ቋት ውስጥ ያሉት ብቻ መደራጀት እንደሚችሉም ገልጧል። በጋራ መኖሪያ ቤቶቹ በማኅበር የሚደራጁ ሰዎች መገንባት የሚችሉት ከአራት ፎቅ እስከ 21 ፎቅ ያላቸውን የጋራ መኖሪያ ቤቶች መሆኑም ተጠቅሷል። 

በመጀመሪያ ዙር ምዝገባው 10(አስር) ሺህ ተጠቃሚዎችን በመርሃግብሩ ለማቀፍ ማቀዱን የገለፀው አስተዳደሩ፤ በመንግስት ተዘጋጅቶ በሚቀርብ መሬት የቁጠባ ሂሳባቸውን ያልዘጉ ተመዝጋቢዎች 70 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ በመክፈል በማህበር ተደራጅተው የመኖሪያ ህንጻዎችን መገንባት ይችላሉ ነው ያለው። የህንጻው ዲዛይን በከተማ አስተዳደሩ አሊያም በሚደራጀው ማህበር ሊቀርብ የሚችል ነው ተብሏል፡፡ የተቀመጠውን መስፈርት የሚያሟሉ የማህበሩ አባላት ብዛትም እንደ የህንጻው አይነት ከ40 እስከ 140 አባላት ይኖሩታል ተብሏል፡፡ 

መንግስት አስፈላጊ ክትትሎችን የማድረግ እና የፋይናንስ ምንጭ የማፈላለግ ሚናውን ይወጣል በተባለለት በዚህ አማራጭ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት 60፣ 75 እና 105 ካሬ ስፋት ባላቸው አማራጮች ላይ እንደፍላጎት መመዝገብ እንደሚቻልም ነው የተገለፀው፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ