1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአደጋ የሚሞቱና የሚጎዱ ልጆች በኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 3 2011

በድሃ ሀገራት የሚገኙ ህፃናትና ልጆች በአደጉ ሀገራት ከሚገኙ አቻዎቻቸዉ በበለጠ በአደጋ ሳቢያ ለሚከሰቱ  ሞትና የአካል ጉዳት የተጋለጡ ናቸዉ ሲል አንድ ጥናት አመለከተ። በኢትዮጵያም ከአደጋ ጋር በተያያዘ  በህፃናቱ ላይ የሚደርሰዉ ሞትና የአካል ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ጥናቱ ጠቁሟል።።

https://p.dw.com/p/39sFh
Bildergalerie Somalia Sicherheitslage Jowhar 2012
ምስል STUART PRICE/AFP/Getty Images

«ከ25 ሺህ በላይ ልጆች በአደጋ ምክንያት ሞተዋል»

በሀገሪቱ  በጎርጎሮሳዊዉ 2015 ዓ/ም  ብቻ 25 ሺህ ሕፃናት  ከአደጋ ጋር በተያያዘ መሞታቸዉንም ጥናቱ ጨምሮ አመልክቷል። የኢትዮጵያ የሕፃናትና ወጣቶችና ሴቶች ሚንስቴር በበኩሉ ችግሩን ለመቀነስ እየሰራሁ ነዉ ብሏል።
የጆንሆፕኪንስ  ዩንቨርሲቲ በቅርቡ ባወጣዉ ጥናት እንዳመለከተዉ በድንገተኛ አደጋና ሆን ተብሎ በሚፈፀም ጥቃት  ሳቢያ ለአካል ጉዳትና ለሞት የሚዳረጉ የድሃ ሀገራት ልጆች ከአደጉ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር ጉዳቱ ከፍተኛ ነዉ።
በድሃ ሀገራት የሚገኙ ልጆች ለትራፊክ አደጋ፣ ለእሳት ቃጠሎ፣ ለመመረዝ፣ ለመዉደቅ እንዲሁም ሆን ተብሎ ለሚፈፀም የወሲብ ጥቃትና በወላጆችና በአሳዳጊዎች ለሚፈፀም አካላዊ ቅጣት የተጋለጡ በመሆናቸዉ ጉዳቱ ሊጨምር መቻሉን ጥናቱ አመልክቷል።
ጥናቱ ከድሃ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያን በማሳያነት የወሰደ ሲሆን ፤ በሀገሪቱ በጎርጎሮሳዊዉ 2015 ዓ/ም ብቻ 85 ሺህ በላይ ልጆች ከአደጋ ጋር በተያያዘ ጉዳት እንደደረሰባቸዉ  አመልክቷል። ከነዚህም መካከል 25 ሺ በላይ ህፃናትና ልጆች ለሞት ተዳርገዋል። ከሟቶቹ መካከል 13 ሺህ 550ዎቹ ከ 5 ዓመት ዕድሜ በታች ሲሆኑ 11 ሺህ 684ቱ ደግሞ ከ5 ዓመት እሰከ 14 ዓመት ዕድሜ ክልል የሚገኙ መሆናቸዉ ተገልጿል።
ይህንን መረጃ መሰረት በማድረግም በጎርጎሮሳዉያኑ 2020 እና 2030 የጉዳቱ መጠን የት ሊደርስ ይችላል የሚለዉን ትንተና ሰጥቷል። ከሚመለከታቸዉ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች አገኘሁት ባለዉ መረጃ መሰረትም ተገቢ የመፍትሄ ርምጃ ካልተወሰደ  በልጆች ላይ የሚደርሰዉ ጉዳት በኢትዮጵያ እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችል ትንበያዉን አስቀምጧል።
ለጉዳቱ መጨመር የትራፊክ አደጋ ፣የእሳት ቃጠሎ፣ጎርፍ ወይም በዉሃ መስጠም ዋነኛዎቹ መንስኤዎች ተደርገዉ ተለይተዋል።
ሆን ተብሎ በሚፈፀም አደጋ ደግሞ በህፃናት ላይ የሚፈፀም የወሲብ ጥቃት እንዲሁም ልጆችን ለማረም በሚል በወላጆችና በአሳዳጊዎች የሚደረጉ አካላዊ ቅጣቶች  መሆናቸዉ ተገልጿል።ጉዳዩን በተመለከተ DW ያነጋገራቸዉ በሴቶች የህፃናትና ወጣቶች ሚንስቴር የህዝብ ግንኙነት ረዳት ሃላፊ አቶ አለማየሁ ማሞ እንደሚሉት ችግሩን ለመፍታት መሰል ጥናቶች በግብዓትነት ስለሚያገለግሉ ጠቃሚ ናቸዉ።በጥናቱ የተነሱ ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነዉ በአሁኑ ወቅት የሚታየዉ የመፈናቀል አደጋም ለችግሩ መባባስ ሌላዉ ምክንያት ነዉ ብለዋል።
ስለሆነም በአስቸጋሪ ሁኔታ የሚገኙ ህፃናትን ችግር ለመፍታት ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር መንግስት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በወላጆች ጥበቃ ማነስ የሚከሰቱ ጉዳቶችን ለመቀነስም ለሰራተኛ እናቶች በየ ተቋማቱ የህፃናት ማቆያና ጥበቃ ማዕከሎች ለመመስረት መታቀዱንም ገልዋል። በአስቸጋሪ ሁኔታ ያሉ ህጻናትን መደገፍ ለመንግስት ብቻ የሚተዉ ሥራ አይደለም የሚሉት ኃላፊዉ ኅብረተሰቡን ለማሳተፍም ዕቅድ መያዙን ጠቁመዋል።
እንደ ጥናቱ አደጋዉ በገጠር የሚገኙ ህፃናት ልጆች በከተማ ከሚኖሩት በበለጠ ለችግሩ ተጋላጭ ናቸዉ ።ፆታን በተመለከተ ወንድ ሕፃናት ልጆች ከሴቶች በበለጠ ለሞትና ለአካል ጉዳት ለሚያደርሱ አደጋዎች የተጋለጡ ናቸዉ ብሏል ጥናቱ።ለዚህም ወንድ ህፃናት ልጆች ከሴት እኩዮቻቸዉ በበበለጠ ለአደጋ የሚያጋልጡ አዳዲስ ነገሮችን ለመሞከር ካላቸዉ ፍላጎት ጋር የተያያዘ ነዉ ተብሏል። 
ይህ መሰሉ ጉዳት በሌሎች ድሃ ሀገራትም ተመሳሳይ  ሊሆን  እንደሚችል  በጥናቱ  ተመልክቷል።
በህፃናቱ ላይ ለሚደርሰዉ አደጋ በዋናነት ድህነት  አስተዋፅኦ የሚያደርግ ሲሆን እድሜ ፣ጾታ፣አካባቢ ፣ የወላጆች ወይም የአሳዳጊዎች የጤና ሁኔታና አካባቢ ለጉዳቱ ተጨማሪ አባባሽ ነገሮች መሆናቸዉ ተጠቁሟል።
ችግሩን ለመፍታት የኢትዮጵያ መንግስትም ይሁን ባለ ድርሻ አካላት  በልጆች ላይ የሚደርሰዉን የአካል ጉዳትና  ሞት በተመለከተ የክትትል ስርዓት በመላ  መዘርጋት እንዲሁም ትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ የድርጊት መርሃ ግብር ተግባራዊ ማድረግ ጠቃሚ ነዉ ሲል ጥናቱ ምክረ ሀሳብ አስቀምጧል።

Zwillinge in Äthiopien
ምስል picture-alliance/dpa
Global Media Forum KLICK! 2012 Horst Frommont 2
ምስል Horst Frommont
Ethiopian children play in the water of a well built by Sailors.
ምስል Official U.S. Navy Imagery / CC BY 2.0

ፀሐይ ጫኔ

እሸቴ በቀለ