1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

የአየር ንብረት ለውጥ በግብርናው ዘርፍ ተጽእኖና መፍትሄው

ሐሙስ፣ ጥር 9 2011

በአንዳንድ አካባቢዎች መደበኛ ያልሆነ የዝናብ መጠን እንዲጨምር ምክንያት ሲሆንም ይስተዋላል፡፡ ይህም የግብርና ዘርፉን የሚያናጋ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/3Bglk
Landwirtschaft Äthiopien Dreschen von Hirse
ምስል Getty Images/AFP/S. Gemechu

የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ

የአየር ንብረት ለውጥ የዝናብ መጠንን በማዛባት የውኃ እጥረት እንዲከሰት ያደርጋል። በተቃራኒው በአንዳንድ አካባቢዎች መደበኛ ያልሆነ የዝናብ መጠን እንዲጨምር ምክንያት ሲሆንም ይስተዋላል፡፡ ይህም የግብርና ዘርፉን የሚያናጋ ነው፡፡ በዚህም መሰል የግብርና ምርምሮች አጋዥ ሊሆን እንደሚችል እሙን ነው።  ችግሩን ለመቅረፍ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በግብርናው ዘርፍ በዋና 17 የምርምር ማእከል ይሠራል። ኢንስቲትዩቱ የሙከራ ማእከላትም አሉት። የአየር ንብረት ለውጡ የምርት መቀነስ ማስከተሉ አንዱና ዋነኛው ውጤት እንደሆነ አቶ ደግፌ ጥበበ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት የአየር ንብረት እና ጂዎፓርሻል ዲያሜትሪክ ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪ ይገልጻሉ። በምርምር ማእከላቸው የአየር ጸባይ ለውጥና መዛባትን አስመልክቶ መረጃ ማውጣት የአየር ንብረት ለውጥ በግብርናው ላይ ያመጣውን ተጽእኖ መለካት እና በቴክኖሎጂ ተጽእኖውን መቀነስ የሚቻልበትን በምርምር ማእከላቸው እንደሚሰራ ጠቅሰዋል። «በተለያየ ደረጃ ከግብርና ጋር በተገናኘ ተጽእኖዎች ይኖሩታል። የዝናብ እጥረት፣ የዝናብ ቶሎ ቶሎ በተለያየ ደረጃ መለዋወጥ፣ ደረቃማ ቀናት መጨመር፣ የእነዚህ የሰብል ምርትን ይቀንሳል» አቶ ደግፌ በአብዛኛው ተጎጂ የሚሆኑት በኢትዮጵያ ደረቃማና ዝቅተኛ አካባቢዎች ያሉ ናቸው ይላሉ። ይህን ለመከላከል ደግሞ አየር ትንቢያ አሰራሮችን መሰረት ባደረገ መልክ መተግበር ያስፈልጋል ሲሉም ያክላሉ። «በአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ የሚሆኑት በአብዛኛው ደረቃማ አካባቢ የበለጠ የመጠቃት ችግር ይኖራል» በሰብል ምርምር የአየር ንብረት ለውጡን መቋቋም የሚችሉ የዘር አይነቶች ተገኝተዋል። በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሰብል ምርምር ዳይሬክተር ዶ/ር ታዬ ታደሰ ለረጅም ጊዜ ድርቅን ሊቋቋሙ የሚችሉ እና በአጭር ጊዜ ደርሰው ምርት የሚሰጡ የሰብል ዝርያዎች በምርምር ማእከላቸው እንደሚወጡ ይገልጻሉ። በተለይ ድርቅን መቋቋም የሚያስችሉ ባህሪያትን ከማጥናት ጋር በተገናኘ በመለየት እና በማሻሻል ቶሎ መድረስ የሚችሉ ዝርያዎችን አግኝተው አርሶ አደሩ ተጠቃሚ የሚሆንበት ስራ እየተሰራ እንዳለም ያስረዳሉ። «ድርቅን መቋቋም የሚችሉ የተለያዩ ዝርያዎች አውጥተናል። በተለይ ድርቅን መቋቋም የሚያስችሉ ባህሪያትን ከማጥናት ጋር በተያያዘ አንዳንድ ባህሪያት የመለየትና የዝርያ ማሻሻያ በመፍጠር የምንሰራቸው ሥራዎች አሉ።» በአየር ንብረት ለውጡ ተጠቂ የማይሆን ሰብል እንደሌለ ሆኖም ችግሩ ጎልቶ የሚታይባቸው ቆላማው አካባቢ እንደሆነ ዶ/ር ታዬ ይገልጻሉ። ለአካባቢው ተስማሚ የሆኑ የሰብል ዝርያዎችን  በምርምር ማእከሉ ግኝት እየወጣ ለአርሶ አደሩ እንደሚከፋፈልም ይናገራሉ። «በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ተጠቂ የማይሆን ሰብል አለ ብሎ ማለት አይቻልም። ችግሩ ግን ጎልቶ የሚታየው ዝናብ አጠር በሆኑ ቆላማ ቦታዎች ላይ ሰፊ የሆነ ጫና ነው የሚያሳድረው። ትኩረት አድርገን የምንሰራው በምግብ ሰብል አርሶ አደሩ ተጠቂ እንዳይሆን ማድረግ ነው።» ዶ/ር ታዬ አርሶ አደሩ የጣለውን ዝናብ የሚጠቀምበትን የውኃ ማቀብ ስራ በስፋት እንደሚሰሩም በተጨማሪ ገልጸውልናል። 

ነጃት ኢብራሂም   
ተስፋአለም ወልደየስ