1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

በአሶሳ ከ130 በላይ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን ባለሥልጣናት ተናገሩ

ዓርብ፣ ነሐሴ 21 2013

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ዋና ከተማ አሶሳ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ እና ምርት በመሸሸግ የተከሰሱ ከ130 በላይ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን ባለሥልጣናት ተናገሩ። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ጤፍ እና ሽንኩርትን የመሳሰሉ መሠረታዊ የፍጆታ ግብዓቶች በከፍተኛ መጠን ዋጋ እንደጨመሩ ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/3zYvu
Asosa, West-Äthiopien und Hauptstadt der Region Benishangul-Gumuz
ምስል privat

የኑሮ ውድነት በአሶሳ

ምርት ደብቀዋል፣ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ የጭማሪ አድርገዋል በተባሉ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ። በቢሮ የንግድና የንግድ ምዝገባ ፈቃድ ኃላፊ አቶ ሰይድ አሊ እንደተናሩት ከ136 በላይ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወስዷል። በክልሉ ከፍጆታ ዕቃዎች እስከ ግንባታ ምርቶች የዋጋ ጭማሪ እየተስተዋለ እንደሆነ ነዋሪዎች ገልጸዋል። የዋጋ ጭማሪውን ለማረጋጋት የክልሉ መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሆነው የክልሉ ንግድ ቢሮ አመልክቷል። 

በአሶሳ ከተማ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ በፍጆታ ዕቃዎች ላይ  የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ መደረጉን የከተማው ነዋሪዎች  ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 
በአሶሳ ከተማ 30 ብር የነበረው አንድ ኪሎ ሽኩርት 60 ብር፣ 44 ብር የነበረው ጤፍ በ56 ብር እየተሸጠ እንደነበርም ነዋሪዎች እና የክልሉ መንግስት ባለሥልጣናት ተናግረዋል። በጸጥታ መጓደል ምክንያት ተዘግቶ የነበረ መንገድ ከተከፈተ ወዲህም የገበያ መረጋጋት እንዳለም አቶ ሰይድ ተናግረዋል። 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ተቋማትን ለመከታተል ስራ የጀመረው እና በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻሊ ሀሰን የሚመራው ግብረ ሀይል ባለፈው ሳምንት አርብ ነሐሴ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የስራ አፈጻጸሙን በገለጸበት ወቅት በጸጥታ ችግርና በተለይም አሶሳን ከሌሎች ክልሎች ጋር የሚገናኙ መንገዶች መዘጋት ምክንያት በቤኒሻጉል የተለያዩ ስፍራዎች በምርቶች ላይ የተጋነነ ዋጋ ጭማሪ ተስተውሏል ብሏል። 

ከሳምንት በፊት የመንገድ መዘጋትን እንደ ሰበብ በመጠቀም ምርት የደበቁ ግለሰቦች እና ባጠቃላይ በምርት እጥረት ምክንያት በአሶሳ ከተማ በተለያዩ  ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መደረጉን በቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ የንግድ ፈቃድ ምዝገባ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሰይድ አሊ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በክልሉ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉና ምርት ያለአግባብ ያከማቹ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም አብራርተዋል። በአሶሳ ከተማ ብቻ ከ130 በላይ የንግድ ተቋማት ላይ  እርምጃዎች የተወሰደ ሲሆን ገንዘብም ተቀጥቷል፡፡ የገበያ ዋጋ ለማረጋጋት ምርቶች እንዲገቡ  መደረጋቸውንና መንገዶችም እንዲከፈቱ ተደርገዋል ብለዋል። 

ከነሐሴ ወር መጀመሪያ አንስቶ በክልሉ የተለያዩ ስፍራዎች ወቅታዊ የጸጥታ ጉዳይንና መንገድ መዘጋትን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ህብረተሰቡን የሚያማርሩ የንግድ ተቋማት ላይ የተቀናጀ ክትትል ለማድረግ  በክልሉ ርዕሰ መስዳድር የሚመራው ግብረ ሀይል ተቋቋሞ በስራ ላይ እንደሚገኝም ከቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል ኮሙኒኬሽ ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ነጋሳ ደሳለኝ

እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ