1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአሰሪዎቻቸው የሚጣሉት ኢትዮጵያውያን በሊባኖስ

ሐሙስ፣ ግንቦት 27 2012

አርባ ገደማ ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞች ደሞዝ ሳይከፈላቸው በቀጣሪዎቻቸው ተባረው ላለፈው አንድ ወር ገደማ ከኢትዮጵያ ቆንስላ ደጃፍ ጎዳና ላይ ቆይተዋል። ወደ አገራቸው ለመመለስ በቤይሩት ከሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ እገዛ ቢጠይቁም ገንዘብ መክፈል እንዳለባቸው ተነግሯቸው ነበር። የሊባኖስ መንግሥት ኢትዮጵያውያኑን ወደ ሆቴል አዘዋውሯል

https://p.dw.com/p/3dH3X
Libanon Russlands Einfluß
ምስል DW/B. Gerdziunas

ከጽጌረዳ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ

በሊባኖስ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ደጃፍ ለቀናት መፍትሔ ፍለጋ ሲጠባበቁ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ትናንት ማምሻውን በአገሪቱ መንግሥት ወደ ሆቴል ተወሰዱ። ደሞዝ ሳይከፈላቸው በአሰሪዎቻቸው የተባረሩት የቤት ሰራተኞች ቤይሩት ከተማ በሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ደጃፍ ላለፈው አንድ ወር ገደማ ጎዳና ላይ ቆይተዋል።

የአሶሼትድ ፕሬስ ጋዜጠኛ ዳላል ማዋድ በትዊተር ባጋራችው ቪዲዮ ኢትዮጵያውያኑ በቤይሩት ከኢትዮጵያ ቆንስላ ደጃፍ ጎዳና አንድ ሕንፃ ጥግ የተወሰኑት ተኝተው የተወሰኑ ደግሞ መንገድ ላይ ቆመው ታይተዋል። ዳላል እነዚሁ የቤት ሰራተኞች በቀጣሪዎቻቸው ደሞዝ ሳይከፈላቸው መባረራቸውን ገልጻለች። ዳላል እንዳለችው ወደ አገራቸው ለመመለስ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ገንዘብ ጠይቋቸዋል። ኢትዮጵያውያኑ ግን በእጃቸው ገንዘብ የለም። 

ጎዳና ወድቀው ለቆዩት የቤት ሰራተኞች የዕለት ምግብ በማሰባሰብ ዕገዛ ስታደርግ የነበረችው ጽጌረዳ የተባለች የቤይሩት ነዋሪ «በሊባኖስ መንግሥት ሰራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ አማካኝነት» መነሳታቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግራለች። የሊባኖስ የሰራተኛ ጉዳይ ምኒስትር ላሚያ ያሚን የቤት ሰራተኞቹ ከኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ደጃፍ ወደ ሆቴል መዘዋወራቸውን በትዊተር ባሰፈሩት መልዕክት አረጋግጠዋል።

ጽጌረዳ እንዳለችው ኢትዮጵያዉያኑ በቁጥር ከ35 እስከ 40 ይሆናሉ። «በአገሪቷ ዶላር የለም። እኛ የሚከፈለን በዶላር ነው» የምትለው ጽጌረዳ ሊባኖሳዊ ቀጣሪዎቻቸው ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞችን ማባረራቸውን ለዶይቼ ቬለ አስረድታለች።

የኢትዮጵያ ቆንስላ ከደጃፉ የወደቁ የቤት ሰራተኞችን እንዲያስጠልል ቢጠየቅም ጽጌረዳ እንደምትናገረው «ኮሮና ሊያስገቡ ስለሚችሉ ከውጪ አዲስ ሰው እንዳይገባ በዚህ አገር መንግሥት ተከልክለናል» የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

በቤሩት ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት «የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸውን እና አሰሪዎች ጋ ያሉ የእያንዳንዱን ሰራተኛ በተናጠል በማንኛውም ጊዜ ጤንነታቸውን መጠበቅ፣ ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ፤ ደመወዛቸውን እንዲያገኙ ማድረግ ኃላፊነቱ የአሰሪዎች ነው። ሰራተኞች ወደ አገራቸው መመለስ ሲፈልጉ እንዲመለሱ የማድረጉ ኃላፊነትም የአሰሪዎች ነው» የሚል ፅሁፍ አስፍሯል።

ቀጣሪዎች «የትራንስፖርታቸውን ይሁን ሌሎች ወጭዎችንም መሸፈን ግዴታ አለባቸው» የሚለው የኢትዮጵያ ቆንስላ «የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸውን እና አሰሪዎች ጋ ያሉ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ራሳቸውን ጨምሮ፣ አሰሪዎች፤ ሊባኖሳውያን እንዲሁም ኢትዮጵያውያን የሰው አዘዋዋሪዎችም ያለባቸውን ኃላፊነት በመጣስ ቆንስላ ጽህፈት ቤቱ የትራንስፖርታቸውን እና ሌሎች ወጭዎችን ሸፍኖ እንዲልክ በቆንስላው በመገኘት ትልቅ ችግር እየፈጠሩ ይገኛሉ» ብሏል። በቆንስላ ጽህፈት ቤቱ ደጃፍ ወደ አገራቸው ለመመለስ ምን ያክል ኢትዮጵያውያን ልመና ላይ እንደከረሙ ግን ያለው ነገር የለም።  

ቤይሩት በሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት መረጃ መሰረት 400 መቶ ሺሕ ገደማ ኢትዮጵያውያን በሊባኖስ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል ከ300 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ እንደሌላቸው ጽህፈት ቤቱ ይገምታል።

ጽጌረዳ የሊባኖስ መንግሥት ከኢትዮጵያ ቆንስላ ጋር በመነጋገር የቤት ሰራተኞችን ወደ አገራቸው ቀጣሪዎች መመለስ እንደሚችሉ ገልፆ እንደነበር ለዶይቼ ቬለ አስረድታለች።

«የሊባኖስ ሰዎች የኢትዮጵያ ቆንስላ በነፃ ልጆች የሚያሳፍር የመሰላቸው ይመስለኛል» የምትለው ጽጌረዳ የቤት ሰራተኞቹን ከቆንስላው ደጃፍ እየወሰዱ እንደጣሏቸው ገልጻለች። ትናንት ማምሻውን ከጎዳና የተነሱት ኢትዮጵያውያን መቼ እና እንዴት ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ የሚታወቅ ነገር የለም። ጽጌረዳ ግን የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ሰራተኞች ከሊባኖስ መንግሥት ተነጋግረው መፍትሔ ካላበጁ ተመሳሳይ ችግር ሊከሰት እንደሚችል ሥጋት አላት። ባለፈው ሳምንት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  656 ኢትዮጵያውያን ከሊባኖስ መመለሳቸውን አስታውቋል። 

ከጽጌረዳ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ