1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራና ትግራይ ክልሎች ዳግም ደም አፋሳሽ ግጭት እንዳይከሰት ምን ይደረግ?

እሑድ፣ የካቲት 24 2016

የጦርነቱ ጠባሳ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ ግድም በኋላም በጉልኅ ይታያል ። ባለፉት ሳምንታት በትግራይ እና አማራ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ ታጣቂዎች መካከል ለአጭር ጊዜያት የቆዩ ግጭቶች ከአንዴም ሁለት ጊዜ መከሰታቸው ነዋሪዎችን እጅግ አስግቷል ።

https://p.dw.com/p/4d5hd
በሰሜኑ አውዳሚ ጦርነት የጋየ የወታደራዊ ተሽከርካሪ
በሰሜኑ አውዳሚ ጦርነት የጋየ የወታደራዊ ተሽከርካሪ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Million Haileselassie/DW

የሁለቱም ክልል ነዋሪዎች ከጦርነት ሰላምን ይሻሉ

የፕሪቶሪያው ስምምነት ተፈርሞ የጠመንጃ አፈሙዝ ልሣናት ይዘጉ እስከተባለበት ድረስ በተካሄደው የሰሜኑ ጦርነት የበርካታ ኢትዮጵያውያን  ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል ። ብዙዎች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል ፤ ከቤት ንብረት ከቀዬያቸውም ተፈናቅለዋል ። የጦርነቱ ጠባሳ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ ግድም በኋላም በጉልኅ ይታያል ። ባለፉት ሳምንታት በትግራይ እና አማራ ክልሎች  ውስጥ በሚገኙ ታጣቂዎች መካከል ለአጭር ጊዜያት የቆዩ ግጭቶች ከአንዴም ሁለት ጊዜ መከሰታቸው ነዋሪዎችን እጅግ አስግቷል ።

ኹነኛ መፍትኄ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ሳይበጅለት ተድበስብሶ የቆየው የሁለቱ ክልሎች ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የሚጠይቁ ድምፆች እየተስተጋቡ ነው ።  በሁለቱም ክልሎች በጦርነት እና ተደጋጋሚ ግጭቶች እጅግ የተጎዳው ማኅበረሰብ ለረሐብ እና ለእርዛትም ተዳርጓል ። አማራ ክልል የፋኖ እና የከመከላከያ ጦርነት ቀጥሏል ።  በዚህ ሁሉ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በአማራና ትግራይ ክልሎች  በርካታ ሕዝብ የተገደለበት አይነት ዳግም ደም አፋሳሽ ግጭት በሁለቱ ክልሎች መካከል እንዳይከሰት ምን ይደረግ? የዛሬው የእንወያይ መሰናዶዋችን ዋነኛ ትኩረት ነው ።

በውይይቱ 3 እንግዶች ተሳታፊ ናቸው።

  1. ገብረየሱስ ተክሉ ባሕታ (/) በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ሣይንስ እና ቋንቋዎች የኮሌጅ መምህር

  2. አቶ ባይሳ ዋቅወያ፦ የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሞያ፤ ላለፉት 30 ዓመታት የተመድ ባለሥልጣን

  3. ሲሳይ መንግስቴ አዲሱ (/)  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ፤ ፌዴራሊዝም እና ሰብአዊ መብቶች መምህር እና ተመራማሪ  ናቸው ።

በውይይቱ መግቢያ ላይም፦ የአማራና የትግራይ ክልሎች  የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱባቸው አካባቢዎች ከሚኖሩ ሰዎች ያሰባሰብናቸው አስተያየቶችም ተካቷል ። አስተያየት ሰጪዎቹ ውጥረቶች በመላ በሰላማዊ መንገድ በውይይት እንዲፈታ ጠይቀዋል ።

 የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሲፈረም
የጠመንጃ አፈሙዝ ልሣናት ይዘጉየተባለበት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሲፈረምምስል Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

ሙሉ ውይይቱን በድምፅ መከታተል ይቻላል ።

«በአማራና ትግራይ ክልሎች ዳግም ደም አፋሳሽ ግጭት እንዳይከሰት»፦ በሚል ርእስ በቀረበው ውይይት ተሳታፊ እንዲሆኑ ለጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት በኢሜል ብንጠይቅም ለውይይቱ ተሳታፊ የሚሆን ሰው እንደሌለ በዛው በኢሜል ምላሽ ተሰጥቶናል ። ለመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) እንዲሁም ለምክትላቸው ሠላማዊት ካሳ በዶይቸ ቬለ በኩል የላክነው ይፋዊ የኢሜል ግብዣ ውይይቱን እስካደረግንበት ጊዜ ድረስ ምላሽ አላገኘም ።

ሙሉ ውይይቱን በድምፅ መከታተል ይቻላል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ