1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል ጦርነት ቀጠና የረሐብ አደጋ ተጋርጧል ተባለ

ሐሙስ፣ ጳጉሜን 4 2013

በአማራ ክልል በጦርነት ቀጠና አካባቢ ለሚገኙና ለርሐብ አደጋ ለተጋለጡ ሰዎች ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአፋጣኝ ርዳታ ካላደረሰ የከፋ ችግር ሊከሰት እንደሚችል ተገለጠ። በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ነዋሪዎች ስጋታቸውን እየገለፁ ነው።

https://p.dw.com/p/407vY
Äthiopien Bewohner des Kriegsgebiets in der Nord Wollo Zone haben Angst vor einer Hungersnot
ምስል Alemenew Mekonnen/DW

700 ሺህ ተረጂዎችን ለማገዝ አስቸጋሪና ፈታኝ ነው ተብሏል

በአማራ ክልል በጦርነት ቀጠና አካባቢ ለሚገኙና ለርሐብ አደጋ ለተጋለጡ ሰዎች ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአፋጣኝ ርዳታ ካላደረሰ የከፋ ችግር ሊከሰት እንደሚችል ተገለጠ። በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ነዋሪዎች ስጋታቸውን እየገለፁ ነው። የክልሉ መንግስት በበኩሉ የዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ለችግሩ አፋጣኝ ምላሽ እየሰጡ አይደለም ሲል ወቅሷል። የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ለሰሜን ጎንደር ዞን ተፈናቃዮች ርዳታ ማድረስ ጀምሯል፣ የሚሰጠው ድጋፍ በቂ ባይሆንም በመንግስትና በግለሰቦች እየተረዱ እንደሆነ ደግሞ ደሴ የሚገኙ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች ተናግረዋል።

ሰኔ 2013 ቀን ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ሕወሓት በአማራ ክልል ሰሜናዊና ምስራቅ  አካባቢዎች ያደረገውን ወረራ ተከትሎ በርካቶች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል አሊያም መረዳት የነበረባቸው ችግረኞች በተፈጠረው ጦርነትና ወረራ ባሉበት ርዳታ ማግኘት አልቻሉም። በዚህም በርካቶች ለከፋ ርሐብ እተጋለጡ መሆናቸውን ነው በጦርነት ቀጠና ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች የሚናገሩት። በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ ወርቄ በተባለ አካባቢ ያሉ ነዋሪ አካባቢው በምግብ ለሥራ የሚተዳደር መሆኑን አስታውሰው መንግስት ርዳታ የሚደርስበትን ሁኔታ ያመቻች ብለዋል።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽነር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ መስፍን በጦርነት ቀጠና ውስጥ ያሉ 700 ሺህ ተረጂዎችን ለማገዝ አስቸጋሪና ፈታኝ መሆኑን አመልክተዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለሰሜን ጎንደር ዞን ለ377 ሺህ ተፈናቃዮች እርዳታ መስጠት መጀመሩን የተናገሩት አቶ እያሱ፣ በርካታ ዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች ግን በግልፅ የሚታይ አድልዎ እየፈፀሙ ነው። በቀጣይ ተቋማቱ ከችግራቸው ወጥተው ለአማራ ክልል ተረጂዎችም በቂ ርዳታ ያደርሳሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል። 

በሰሜን ጎንደር ዞን ሽመላኮ መጠለያ ከሚገኙት ተፈናቃዮች መካከል አቶ ደስታው መለሰ በቂ ርዳታ እንደማያገኙ ተናግረዋል። በደሴ ከተማ ተፈናቅለው ለሚገኙ ከ195 ሺህ በላይ ወገኖች ርዳታ እየቀረበላቸው እንደሆነ ግን አቶ እያሱ ገልጠዋል። ከሰሜን ወሎ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ከሚገኙት መካከል በቂ ባይሆንም ከግለሰቦችና ከመንግስት ርዳታ እያገኙ እንደሆነ ተናግረዋል። በአጠቃላይ በአማራ ክልል ከ1 ሚሊዮን 800 ሺህ በላይ በምግብ ለስራ የሚደገፍና 1 ሚሊዮን 300 ሺህ ተፈናቃይ ይገኛል።

ዓለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ 
ነጋሽ መሐመድ