1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል የተገደሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት መታሰብያ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 16 2012

የዛሬ ዓመት በባሕር ዳር ከታማ ለተገደሉ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና የፀጥታ አባላት የመታሰቢያ ፕሮግራሞች እተካሄዱ ነው፣ በወቅቱ ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው ቤተሰቦች ደግሞ መንግስት ድጋፍ አላደረገልንም ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል፣ መንግስት በቅርቡ ድጋፍ እንደሚያደርግ ደግሞ ክልሉ አመልክቷል፡፡

https://p.dw.com/p/3e9tY
Äthiopien Beerdigung eines Offizziers in Bahirdar
ምስል DW/A. Mekonnen

የሟች ቤተሰቦች በችግር ላይ ነን ሲሉ የርዳታ ጥሪ አቅርበዋል

ልክ የዛሬ ዓመት አመሻሽ ላይ በባሕር ዳር ከተማ አሰደንጋጭ ሁኔታዎች ተፈጥረው ያመሹበት እለት ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ባይስማሙበትም የክልሉም ሆነ የፌደራሉ መንግስት ድርጊቱን መፈንቅለ መንግስት በማለት ሰይሞታል፡፡ በእለቱ በተፈጠረው አስደንጋጭ ክስተት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አምባቸው መኮንንና ሌላው የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣን አቶ እዘዝ ዋሴ ከሌሎች አመራሮች ጋር በርዕሰ መስተዳደር ጽ/ቤት ስብሰባ ላይ በነበሩበት ወቅት በተተኮሰባቸው ጥይት ወዲያዉኑ ሲገደሉ ሰንበት ብለው በተኩሱ ቆስለው የነበሩት አቃቤ ህግ አቶ ምግባሩ ከበደ በህክምና ሲረዱ ቢቆዩም ህይወታቸው አልፏል፡፡ የድርጊቱ አቀነባባሪና መሪ የተባሉት የአማራ ክልል የሠላምና ደህንነት ኃላፊ የነበሩት ብርጋዴየር ጀነራል አሳምነው ፅጌም ከሁለት ቀናት በኋላ ባሕር ዳር ወጣ ብሎ በሚገኝ አካባቢ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ መገደላቸውን በወቅቱ የክልሉ መንግስት አስታውቋል፡፡ 
ታዲያ ሰሞኑን በወቅቱ በስብሰባ ላይ እንዳሉ የተገደሉትንና ህይወታቸው ያለፈ የፀጥታ አባላትን ለመዘከር የተለያዩ ፕሮግራሞች እየተካሄዱ መሆኑን የአማራ ክልል መንግስት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡ የጽ/ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ እንዳሉት አመራሮቹ በተገደሉበት የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ግቢ ቤት መታሰቢያ ሀውልት ይቆማል 
የመታሰቢያ ስነስርዓቱ ሁለት ዓላማዎች እንደሚኖሩት ያመለከቱት አቶ ግዛቸው የደም ልገሳና የፓናል ውይቶችም ተካሂደዋል ብለዋል፡፡ 
ይህ በእንዲህ እንዳለ በእለቱ ባለቤታቸውን በሞት ያጡት ወ/ሮ ፍሬህይዎት ተወልደ መንግስት የቀበሌ ቤት ከመስጠት ውጭ ያደረገልኝ ድጋፍ ባለመኖሩ ሶስት ህፀንት ይዠ ባግባቡ ማሳደግ አልቻልሁም ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ ሌላዋ ባለቤታቸውን በሞት ያጡት ወ/ሮ ፍሬህየወት ጠና በበኩላቸው የት ወደቅሽ ያለኝ አካል የለም ሲሉ በሀዘን ገልፀዋል 
በወቅቱ እርጉዝ የነበሩት ወ/ሮ ፍሬህወት አሁን ከሚያፅናናቸው ከ10 ወር ልጃቸው ጋር በችግር ከእናታቸው ጋር በደቡብ ጎንደር ነፋስ መውጫ ከተማ እንደሚኖሩ አስረድተዋል 
 የአማራ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ የተጎጂ ቤተሰቦች ጥያቄ በቅርቡ ምላሽ ያገኛል ብለዋል፡፡  ከፖሊስ አባላት ተሰብስቧል ስለተባለው ገንዘብ መረጃ ለማግኘት በአካልና በስልክ ያደረግሁት ሙከራ የሚመለከታቸውን ባለማግኘትና መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለሁም በሚል አልተሳካልኝም። 


 ዓለምነው መኮንን  

አዜብ ታደሰ 

ኂሩት መለሰ