1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል የ72 ባለሐብቶች የኢንቨስትመንት ውል ተቋረጠ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 17 2013

በአማራ ክልላዊ መንግሥት ለኢንቨስትመንት መሬት ወስደው ሥራ አልጀመሩም የተባሉ 72 ባለሐብቶች ውል ተቋረጠ። ሌሎች 30 ባለሐብቶች ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ሁለት ኢንቨስትሮች የተወሰደውን እርምጃ ተቃውመዋል።

https://p.dw.com/p/3xylV
Äthiopische Industriepark-Entwicklungsgesellschaft, Mitarbeiter der Niederlassung in der Region Amhara
ምስል DW/Alemnew Mekonnen

በአማራ ክልል የ72 ባለሐብቶች የኢንቨስትመንት ውል ተቋረጠ

ቦታ ወስደው ወደ ልማት ባልገቡ ከ100 በላይ ባለሀብቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የባህር ዳር ቅርንጫፍ አስታወቀ። ባለሀብቶቹ ደግሞ የተወሰደው እርምጃ ትክክል አይደለም ይላሉ። 
በአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የባህር የቅርንጫፍ ጽ/ቤት የደንበኞች አገልግሎትና የገበያ ትስስር ቡድን መሪና ባለሙያ አቶ ዘመነ ጫኔ ዛሬ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ቦታ ወስደው ያላለሙና በውላቸው መሰረት ወደ ልማት ያልገቡ 72 ባለሀብቶች 47. 43 ሄክታር መሬታቸው ተነጥቋል፣ በ25 ሄክታር መሬት የወሰዱ 30 ባለሀብቶች ደግሞ ማስጠንቀቂያ ተጽፎባቸዋል። 
ከባለሀብቱ ይጠበቅ የነበረውን የጠቀሱት አቶ ዘመነ ያን ያላደረጉ ናቸው እርምጃ የተወሰደባቸው ባይ ናቸው። የባለሀብቶች እንቅስቃሴ ከተለያዩ አካላት በተውጣጣ ኮሚቴ እንደሚገመገምና በውላቸው መሰረት ወደስራ ያልገቡት በየዓመቱ መሬት እስከመንጠቅ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድባቸውም ገልፀዋል፡፡ 
መሬት ከተነጠቀባቸው ባለሀብቶች መካከል በኤሌክትሮኒክስ፣ መካኒካል ማኑፋክቸሪነግ ተሰማርተው የነበሩት አቶ ሰለሞን ያዛቸው የተወሰደው እርምጃ ትክክል አይደለም መንግስት መጀመሪያ መስራት የነበረበትን ስራ አልሰራም ይላሉ፡፡ 
ሌላው በእንጨት ስራዎች የተሰማሩት አቶ መኳንንት ታደሰም የተወሰደው እርምጃ ትክክል ያልሆነና ዱብዳ እንደሆነባቸው ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል፡፡ 
በአጠቃላይ በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር 650 ባለሀብቶች 633 ሄክታር መሬት ለልማት መውሰዳቸውንና ወደ ስራ የገቡት በቀለም ምርት፣ በብረታብረት ሥራ፣ በእምነ በረድና በሌሎችም መስኮች የተሰማሩ ናቸው ብለዋል፡፡ 

ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ