1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል ከ3 ሚሊዮን በላይ ተረጂዎች ይገኛሉ 

ዓርብ፣ ጥር 7 2013

በአማራ ክልል በየወሩ እርዳታ የሚደረግላቸው ከ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች እንደሚኖሩ የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራምና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/3nyGu
Äthiopien Amhara Katastrophenprävention   Zelalem Lijalem
ምስል Alemnew Mekonnen/DW


በአማራ ክልል በየወሩ እርዳታ የሚደረግላቸው ከ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች እንደሚኖሩ የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራምና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ።ኮሚሽነሩ አቶ ዘለዓለም ልጃለም ለጋዜጠኞች እንዳብራሩት በአማራ ክልል በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች የተፈናቀሉ፣ በሰብላቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸውና በተፈጥሮ የእርሻ ማሳቸው ሰብል የማያበቅል ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በየወሩ የእርዳታ እህል እየተሰፈረላቸው ነዉ።
በ2013 ዓ.ም ብቻ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉና በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎችና ከዘመድ ተጠግተው የሚኖሩ 48ሺህ ተረጅዎች እንዳሉ የተናገሩት አቶ ዘለዓለም፣ በትግራይ በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ደግሞ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ በጎንደርና አካባቢው ተፈናቅለው እንደሚገኙ ገልፀዋል። ከ2013 ዓ.ም በፊትም በተለያዩ ክልሎች በአማራ ተወላጆች ላይ በተፈጠሩ ዘር ተኮር ጥቃቶ ከ159 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በአማራ ክልል እንደሚገኙም አቶ ዘላለም አስረድተዋል። በማይካድራ፣ ዳንሻና ሁመራ አካባቢም ያለው የስራ እንቅስቃሴ በመዳከሙ በእለት ችርቻሮና በቀን ስራ ኑሯቸውን ይደጉሙ የነበሩ 65 ሺህ ሰዎች እርዳታ እየተደረገላቸው ነው ሲሉ አቶ ዘላለም ተናግረዋል።
ከመፈናቀሉ በተጨማሪ በዚህ ዓመት በደረሱ የተፈጥረ አደጋዎች በርካታ አርሶ አደሮች ለእርዳታ መዳረጋቸውን ኮሚሺነሩ ጠቁመው፣ በተለይም ሰብላቸው በአንበጣ መንጋ የተበላባቸው፣ በመሬት መንሸራተት ሰብላቸው የወደመባቸውና በሌሎች ተፈጥሯዊ አደጋዎች 781 ሺህ አርሶ አደሮች እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል ብለዋል፡፡
በመሬት ለምነት መራቆት ምክንያት የእርሻ ማሳቸው ሰብል ለማያበቅልላቸው 1 ሚሊዮን 800 ሺህ አርሶ አደሮችም በየወሩ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል። በአጠቃላይ በክልሉ ከ3 ሚሊዮን ለሚበልጡ እርዳታ ፈላጊዎች ኮሚሽኑ በየወሩ 413 ሺህ ኩንታል የእርዳታ እህል እያቀረበ እንደሆነም አረጋግጠዋል።
“እርዳተው አልደረሰንም፣ የደረሰንም ቢሆን ማብሰያ እቃ የለንም” ለሚለው የተፈናቃዮች ጥያቄ አቶ ዘለዓለም ሲመልሱ የእርዳታው አቅርቦቱን በተመለከተ የተቋቋመ ኮሚቴ በቦታው እየሰራ እንደሆነና የማብሰያ እቃን በተመለከተ ደግሞ ከፌደራል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጋር እየተነጋገሩበት እንደሆነና በቅርብ እንደሚደርሳቸው አመልክተዋል ኮሚሽነሩ። 


ዓለምነዉ መኮንን 
አዜብ ታደሰ 
ኂሩት መለሰ