1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል ተፈናቃዮችን ለማቋቋም 83 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ተባለ

ማክሰኞ፣ መስከረም 18 2014

በአማራ ክልል ህወሓት በጦርነት ተቆጣጥሮ ያወደማቸውንና የዘረፋቸው የተባሉ ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም ከ83 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ከተለያ ተቋማት የተውጣጣውና ችግሩን የሚያጠና ማዕከል አስታወቀ፡፡

https://p.dw.com/p/40zTa
Äthiopien | Amhara Region Emergency Coordination Center (ARECC)
ምስል Amenew Mekonen/DW

በአማራ ክልል ለተፈናቃዮችን ለማቋቋም 83 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተገለጠ

በአማራ ክልል ህወሓት በጦርነት ተቆጣጥሮ ያወደማቸውንና የዘረፋቸው የተባሉ ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም ከ83 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ከተለያ ተቋማት የተውጣጣውና ችግሩን የሚያጠና ማዕከል አስታወቀ፡፡ ዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማት አሁንም በጦርነት ቀጠና ውስጥ ያሉ ወገኖችን መድረስ እንዳልቻሉ የአማራ ክልል ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡
የአማራ ክልል የአስቸኳይ አደጋ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል የተቋቋመው ከፌደራልና ከክልል የተለያ ተቋማትና ከዓለም አቀፍ ሪጂ ድርጅቶች በተውጣጡ አካላት ነው፡፡ የማዕከሉ ዋና ዓላማም በጦርነት ውስጥ ያሉ፣ ከወረራ ነፃ የሆኑትንና የተፈናቀሉ ወገኖችን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት አስቸኳይ መፍትሔ ለመንግስት ማቅረብ ነው፡፡
ማዕከሉ ዛሬ የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት ባቀረበው ሪፖርት እንዳመለከተው፣ በጦርነቱ ምክንያት በአማራ ክልል በርካታ ውድመቶችና መፈናቀሎች ተከስተዋል፡፡
የአስቸኳይ አደጋ ምላሽ ማዕከሉ አስተባባሪ አቶ ጀምበሩ ደሴ ባቀረቡት ሪፖርት እንደጠቆሙት በጦርነቱ ምክንያት በርካታ የትምህርትና የጤና ተቋማት ተዘርፈዋል ወድመዋልም፡፡ በዚህ ጦርነት ብቻ 700ሺህ በላይ ወገኖች ተፈናቅለዋል፡፡ 10 ከመቶ ተፈናቃዮች ብቻ በ30 የመጠለያ ካምፖች እንደሚገኙ ያመለከቱት አስተባባሪው፣ ሌሎቹ 90 ከመቶዎቹ ከዘመድ ጋር እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
በአጠቃለይ በአማራ ክልል ከ1 ሚሊዮን 700 ሺህ በላይ ተፈናቃይ መኖሩን አመልክተው አጠቃላይ የወደሙ ተቋማትን ለመገንባት፣ የተዘረፉ ንብረቶችን ለመተካትና ተፈናቃዮችን ለማቋቋም 83 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡
የአማራ ክልል የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ በበኩላቸው አሁን ባለው ሁኔታ 5 ሚሊዮን የሚደረሰውን በጦርነት ቀጠና ያለውን ህዝብ መደረስ አልተቻለም፣ ዓለም አቀፍ ሚዲያ እውነቱን ማወቅና ማሳወቅ አልፈለጉም፣ ረጂ ተቋማት ደግሞ ለጥያቄያችን አፋጣኝ ምላሽ አልሰጠም ሲሉ አማርረዋል፡፡
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ በጦርነት ቀጠና ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች እርዳታ የሚያገኙበትን ሁኔታ ከፌደራል ምንግስት ጋር እየተነጋገሩበት ቢሆንም ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ግን አፋጣኝ ምላሽ አለሰጠም ሲሉ ከስሰዋል፡፡
ህዝብ እየሞተ ስለሆን ለነገ የሚባል ነገር ባለመኖሩ እንፍጠን ሲሉም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተማፅነዋል፡፡
የተፈናቃዮችን የእርዳታ ስርጭት በተመለከተ ለአንዳንዶቹ ተከታታይና ተመሳሳይ እርዳታ የሚደርስበት ሁኔታ እየታየ በመሆኑ እርማት እንዲወሰድ ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የተወከሉት አቶ ሳሙኤል ከተማ አሳስበዋል፡፡
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ ሚሹ አካባቢዎች ኮሚሽነር ዘለዓለም ልጅዓለም ድግግሞሽ እርዳታን ለማስወገድ ግለሰቦችም ሆኑ ተቀዋማት እርዳታውን ቀጥታ ለተረጂዎች ከመስጠት ይልቅ በኮሚሽናቸው በኩል እንዲልፍ መክረዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ታምራት ዲንሳ

አዜብ ታደሰ