1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል ተፈናቃዮች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን የክልሉ ባለሥልጣን ተናገሩ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 18 2014

በአማራ ክልል በሚካሔደው ውጊያ የተፈናቀሉ ከ4 ሺሕ 900 በላይ ነፍሰ ጡር እና ከ10 ሺሕ 300 በላይ የሚያጠቡ እናቶች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ክልሉ አስታወቀ። 2.1 ሚሊዮን ከደረሰው የተፈናቃዮች ቁጥር ውስጥ ከ54 ሺሕ በላይ ለከፋ ችግር የተዳረጉ ሕጻናት እንደሚገኙበት ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/43ZWf
Äthiopien Eyasu Mesfin
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ከተፈናቃዮች መካከል ከ54 ሺሕ በላይ ለከፋ ችግር የተዳረጉ ሕጻናት እንደሚገኙ ተገልጿል

በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ከ54 ሺህ በላይ የተፈናቀሉ ህፃናትና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸውን የአማራ ክልል መንግስት አስታወቀ። ዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች በህወሃት ቁጥጥር ስር በሚገኙ የአማራ ክልል አካባቢዎች ለሚገኙ ነዋሪዎች ከቃል ባለፈ ያደረጉት እርዳታ ባለመኖሩ ርሀብ እየተከሰተ እንደሆነም ክልላዊ መንግስቱ አስታውቋል።  

የሕወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል የሚገኙ ቦታዎችን በኃይል ከተቆጣጠሩበት ካለፈው ከነሐሴ 2013 ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ በርካታዎች ተፈናቅለዋል። ሌሎች ደግሞ በህወሓት ቁጥጥር ስር ባሉ የአማራ ክልል አካባቢዎች ረሀብና በሽታ ተጋልጠው እንደሚገኙ የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚያሻቸው አካባቢዎች ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ 

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ መስፍን በተለይ ተፈናቃይ ህፃናት እና እናቶች በከፋ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ 2 ሚሊዮን 1 መቶ ሺህ ተፈናቃይ በአማራ ክልል እንደሚኖር ያመለከቱት አቶ እያሱ አብዛኛው ከዘመድ ጋር እንደሚኖርና በንፅፅር ተገቢው ድጋፍ የማያገኘውም ይኸው ወገን ስለሆነ ረጂ ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ 
ህወሓት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ወገኖችን መድረስ ባለመቻሉ ርሀብ መከሰቱንና ሞትም እየተመዘገበ እንደሆነ ነው ኃላፊው የተናገሩት። 

ዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማትና በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ በህወሓት ቁጥጥር ስር በበሽታና በርሀብ ለተጋለጡ ሰዎች እርዳታ ለማቅረብ ቃል ቢገቡም እስካሁን በተግባር የታየ ነገር የለምም ብለዋል፡፡ 

በአማራ ክልል በወረራ በተያዙ አካባቢዎች ከ7 ሚሊዮን የሚበልጥ ህዝብ ለከፍተኛ ሰቆቃ መዳረጉንም አቶ እያሱ በመግለጫቸው አመልክተዋል። አሁንም ቢሆን ዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማት ፈጥነው እርዳታ የማያቀርቡ ከሆነ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ሰብአዊ ቀውስ እንደሚፈጠር አስጠንቅቀዋል፡፡ 

ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ