1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል በጃሪ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች እሮሮ

ረቡዕ፣ ግንቦት 16 2015

አማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ በጃሪ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች የምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው ተናገግሩ። በአፈር ጥበቃ ስራ ተሰማርተው በቀን ይሰጣቸዋል የተባለው ገንዘብም እንዳልተከፈላቸው ተፈናቃዮቹ ገልፀዋል።

https://p.dw.com/p/4Ri69
Äthiopien l IDPS und IDPs, Vertriebene in der Süd-Wollo-Provinz
ምስል Aleminew Mekonnen

በጃሪ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ የተፈናቃዮች የምግብ እጥረት

አማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ በሚገኘው የጃሪ  መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች የምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው አማረሩ፣ በአፈር ጥበቃ ስራ ላይ ተሰማርተው በቀን ይሰጣቸዋል የተባለው ገንዘብም እንዳልተከፈላቸው ገልፀዋል፣ የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ በእርግጥም እርዳታው መዘግየቱን  አመልክቶ የበተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የሰሩበት ግን በወሩ መጨረሻ ይከፈላቸዋል ብሏል.

ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልለና በከሌሎች አካባቢዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል የተለያዩ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል በደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ ጃሪ የተፈናቃዮች ጣቢያ የሚገኙ ወገኖች የምግብ እህል እጥረት አጋጥሞናል ብለዋል፡፡

የተሁለደሬ ወረዳ አስተዳደር በአፈር ጥበቃ ስራ እንዳሰማራቸው የሚናገሩት ተፋናቃዮች፣ ሆኖም በየቀኑ ይሰጣችኋል የተባለው የቀን የስራ አበል አልተሰጠንም ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

ያለምግብ በአፈር ጥበቃ ስራ ላይ መሰማራታቸው ከባድ እንደሆነ የሚገልፁት ተፈናቃዮቹ የሚመለከተው አካል አስፈላጊውን ትኩረት ሰጥቶ ምግብ እንድናገኝ ያድርግ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

Äthiopien | Binnenvertriebene in Amhara Region
ምስል Alemnew Mekonen/DW

የጃሪ ተፈናቃዮች መጠለያ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ አቶ ብርሀኑ በላይ ግን ለተፈናቃዮቹ በአፈር ጥበቃ የሰሩበት ታስቦ በየቀኑ ክፍያ ይፈፀማል ብለዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ ግን ለአፈር ጥበቃ ስራ የሰሩበት ተከፍሏል የተባለው ፍፁም ሀሰት እንደሆነ ነው የሚያስረዱት፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ይመር በአፈር ጥበቃ ስራ የሰሩበት በወሩ ማጠቃለያ ታስቦ ይከፈላቸዋል ነው ያሉት፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር አቶ ብርሀኑ ዘውዱ የእርዳታ እህል ከፌደራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ባለመላኩ የምግብ አርዳታ አቅርቦቱ ዘግይቷል ብለዋል፡፡

ከፌደራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘውዴ የሥራ ግንኙነታቸው ከክልል ጋር በመሆኑ ለዞን፣ ለወረዳና ለቀበሌ የእርዳታ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እንደማይገደዱ በአንድ ወቅት ተናግረው ነበር፡፡

በአማራ ክልል በአጠቃላይ ከ1 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ
ፀሀይ ጫኔ