1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰሜን ሸዋ ዞንና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አዋሳኝ አካባቢዎች የፀጥታ ሁኔታ

ሰኞ፣ ጥር 22 2015

የሰሜን ሸዋ ዞንና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አዋሳኝ አካባቢዎች እየተረጋጉ መምጣታቸውን አስተዳደሪዎችና ነዋሪዎች ተናገሩ።አንድ የአጣዬ ነዋሪ ትናንት በከተማዋ ከሁለቱም አካላት የተውጣጡ አመራሮች በአጣየ ከተማ ውይይት ማድረጋቸውን አመልክተው ሆኖም ከዚህ ቀደም የተደረጉ ውይይቶች ለውጥ ባለማምጣታቸው በህብረተሰቡ ዘንድ ስጋት እንዳለ ተናግረዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4MsBV
Infografik Karte Äthiopien Close E,  Shewa Robit, Senbete , Ataye, Kemise

የሰሜን ሸዋ ዞንና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አዋሳኝ አካባቢዎች የፀጥታ ሁኔታ


ባለፈው ሰሞን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞንና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረው የፀጥታ መደፍረስ እየተረጋጋ መምጣቱን የየአካባቢዎቹ አስተዳደሪዎችና ነዋሪዎች ተናገሩ፣  ምንም እንኳን አካባቢዎቹ እየተረጋጉ ነው ቢባልም አንዳንድ ነዋሪዎች ግን አሁንም  ስጋት እንዳላቸው  ለዶቼቬለ ተናግረዋል። በሁለቱ ዞን አስተዳደሮች መካከል በተለያዩ ምክንያቶችና ጊዜዎች በሚፈጠሩ አለመግባባቶች በሚነሱ ግጭቶች ህይወት ይጠፋል፣ ንብረትም ይወድማል፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእነኝሁ አዋሳኝ አካባቢዎች በተደጋጋሚ በተፈጠሩ ግጭቶች የንፁሀን ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረትም በከፍተኛ ሁኔታ ወድሟል፤ ሰሞኑንም በተመሳሳ ሁኔታ አንዱ ሌላውን ተጠያቂ ባደረገው የግጭት መነሻ በህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ 
ህብረተሰቡና የፀጥታ ኃይሉ አደርገውታል በተባለ ጥረት አሁን ችግሩ መቀልበሱን በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ ተናግረዋል፡፡ 
“በጽንፈኞች፣ የተጠነሰሰው አገርን የማፍረስና ስርዓትን በኃይል የመናድ ፍላጎት ለማሳካት ታስቦ የተጠነሰሰው ጥፋት ምንም እንኳ ብዙ ጥፋት በቀጠናው ቢያደርስም በህዝቡና በመንግስት የተቀናጀ የፀጥታና የፖለቲካ ስራ ለመቀልበስ ተችሏል፣ አሁን ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመሆን ህዝቡን የማረጋጋት ስራ እየሰራን ነው፡፡” ብለዋል፡፡ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ስራ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አህመድ አጠቃላይ የደረሰው ጥፋት እየተጣራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ 
“አሁን ዋናው አስቸኳይ ጉዳይ በርካታ ሰዎች ተፈናቅለዋል፣ ለእነዚህ ቶሎ መድረስ ስፈልጋል፣ በእኛ በኩል መረጃዎችን እያሰባሰብን ነው፣ እዚህ አካባቢ የሚፈጠሩ ችግሮች ተደጋጋሚ ናቸው፣ ለምን ተደጋጋመ፣ ችግሩ ሳይፈጠር ከህብረተሰቡ ጋር በመነጋጋር ችግር ፈጣሪዎችን ለምን መለየት አልተቻለም የሚለው ጉዳይ መመለስ አለበት፣ በዚህ ሂደት ውስጥ ወደፊትም በሚሰጠው የፌደራልና የክልል መንግስታት አቅጣጫ አጥፊዎች ተለይተው ለሕግ የሚቀርቡበት ሁኔታ ይኖራል፡፡” ሲሉ አክለዋል፡፡ በሰሜን ሸዋ ዞን የኤፍራታን ግድም ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ችሮታው ባሳዝን በበኩላቸው ችግር አለባቸው በተባሉ አካባቢዎች የመከላከያ ሰራዊት ገብቶ አሁን የተረጋጋ ሁኔታ እንዳለ አመልክተዋል፡፡ “ መከላከያ ወደ አካባቢው ገብቷል፣ ዋና ዋና የግጭት ቦታ በተባሉት ላይ ያሉትን አካላት በማንሳት ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እየተመለሰ ነው፣ አጣዬም ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ አለ፣ መከላከያውና የፀጥታ ኃይሉ በጋራ ሆነው እየሰሩ ነው ጥሩ ነው፡፡” የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ፣ ህብረተሰቡ ከመንግስትና ከፀጥታ አካሉ ጋር የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡ 
“… ማህበረሰቡ ጉዳዩን እንዲረዳው ከፀጥታ መዋቅሩ ጎን እንዲቆም አሁንም ከስሜት ወጥቶ ጉዳዩን ተረድቶ የመፍትሔው አካል እንዲሆን በጋራ መቆም፣ ከችግሩ በላይ ሆኖ ማሰብ፣ አንድነትንና ወንድማማችነትን በማጠንከር የተጋረጠብንን አደጋ በአንድነት ቆመን የጠላቶቻችን ቅስም መስበር ነው፡፡ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርና የሰሜን ሸዋ ዞን በክልሉ መሪነት በፌደራል መንግስት ድጋፍ እየሰራን ነው ያለነው፤ በአጭር ጊዜ ሰርተን አስተማማኝ ሰላም በአካባቢው እንደምናሰፍን ሙሉ ተስፋ አለኝ ህዝባችን ከዚህ አንፃር እደረገ ያለውን ድግፍ እጅግ በጣም ላመሰግን እወዳለሁ፡፡” 
በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የሰነበቴ ከተማ ነዋሪ አሁን ሰላማዊ ሁኔታ በከተማዋ መኑሩንና ከተማዋን ትለው ሄደው የነበሩ ሰዎ እየተመለሱ አንደሆነ ገልጠዋል፡፡ አንድ የአጣዬ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው ትናንት በከተማዋ ከሁለቱም አካላት የተውጣጡ አመራሮች በአጣየ ከተማ ውይይት ማድረጋቸውን አመልክተው ሆኖም ባለፉት ተከታታይ ኣመታት የተደረጉ ውይይቶች ለውጥ ማምጣት ባለማቻላቸው አሁንም በህብረተሰቡ ዘንድ ስጋት እንዳለ ተናግረዋል፡፡ 
“የክልሉ ብልጽግና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ መጥተው እዚህ (አጣዬ) ውይይት ተካሂዷል፣ ውይይት ብዙ ጊዜ ይካሄዳል፣ እርምጃ እንወስዳለን የሚል ነገር ይነገራል፣ ትንሽ ከተረጋጋ በኋላ ነገሮች ይረሱና ወደ መደበኛ ነገር ይገባል፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ እየሰለጠኑ እየመጡ (ታጣቂዎች) ወረራ ነው የሚፈጽሙት እንጂ እንደንግግራቸው ቢሆን ነገሮች እያገረሹ እንደዚህ አይመለሱም ነበር፣ ሥጋት አለ፣ ለጊዜው ግን አሁን ደህና ነው፡፡” የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ሸይክ አሊይ ሰሞኑን ለዶይቼ ቬሌ እንደገለፁት ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር 98 ሰዎች ተገድለዋል፣ በሰሜን አሜሪካ የዐማራ ማኀበር በበኩሉ ለግጭቱ መነሾ በሆነው ጀወሀ በተባለ ቦታ የተፈጸመ ጥቃት ከ100 በላይ የጸጥታ አስከባሪዎች እንደተገደሉ መግለፁ ይታወሳል፡፡ 
ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ለሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳደሪና አማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ ብድውልም እንደሁልጊዜው ስልካቸው አይነሳም፡፡ 

ዓለምነው መኮንን

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ