1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአምነስቲና ሂዩማን ራይትስ ዎች የጋራ ዘገባ

ረቡዕ፣ መጋቢት 28 2014

የአማራ ልዩ ሐይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ በአስር ሺዎችን ማፈናቀላቸውን፣ ማስር መግደላችውን፣ ሴቶችን መድፈራቸውን እና ከአካባቢው በግድ እንዲባረሩ ማድረጋቸውን፣ ንብረታቸውም እንዲዘረፍ መደረጉን መግለጫው ዘርዝሯል

https://p.dw.com/p/49YN4
Logo amnesty international

የምእራብ ትግራይ የሰብአዊ መብት ጥሰት

             
የአማራና የትግራይ መስተዳድሮች በባለቤትነት በሚወዛገቡበት ምዕራብ ትግራይ ዉስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከጦር ወንጀልና በሰብአዊነት ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ጋር የሚስተካከል የዘር ማጽዳት  ተፈፅሟል በማለት  አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሁዩማን ራይትስ ዎች ዘገቡ። ሁለቱ ዓለም አቀፍ ድርጅቶቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ እና  አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሰጠዉ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዳሉት በአዲጉሹና ሑመራ 120 የትግራይ ተወላጆች በአማራ ሚሊሻ፣ ፋኖና ልዩ ሐይል በጅምላ ተረሽነዋል።የሁለቱ ድርጅቶች ዘገባ በአወዛጋቢዉ  የምዕራብ ትግራይ ግዛት  የአፍሪቃ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ሐይል እንዲሰፍር  ጠቁመዋልም።

ሁለቱ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ያወጡት የጋራ መግለጫና የአምነስቲ የምሥራቅ አፍሪካ የሰብአዊ መብት ተመራማሪ አቶ ፍስሐ ተክሌ ለዶቼ ቬለ  በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ ዛሬ ይፋ የተደረገውን ዘገባ ለማዘጋጀት ከአንድ አመት በላይ ጥናት ተደርጓል። መረጃውንም ከ400 በላይ የዐይን እማኞች እና የጉዳቱ ሰለቦች፣ እንዲሁም ባለሙያዎችን በማናገር እንዳጠናቀሩት ተገልጿል። ሆኖም ድርጊቱ በተፈጸመበት ስፍራ ተገኝቶ የቀጠለውን የዘር ማጽዳት ዘመቻ በገለልተኝነት ለመመርመር የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በጥብቅ መከልከላቸውንም አመልክተዋል። 
የአማራ ልዩ ሐይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ በአስር ሺዎችን ማፈናቀላቸውን፣ ማስር መግደላችውን፣ ሴቶችን መድፈራቸውን እና ከአካባቢው በግድ እንዲባረሩ ማድረጋቸውን፣ ንብረታቸውም እንዲዘረፍ መደረጉን የዘረዘረው መግለጫው ይሕንም ለማስፈጸም በአማራ ክልል አካባቢውን እንዲያስተዳድሩ የተመደቡ ባለሥልጣናት በአደባባይ በቤተክርስቲያን ጭምር ይቀሰቅሱ እንደነበር ተጠቅሷል።
አቶ ፍስሐ ተክሌ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪካ የብአዊ መብቶች ተመራማሪ እንዳሉትና በመግለጫውም እንደተዘረዘረው በድርጅቶቹ እምነት ዘር የማጽዳት ዘመቻ መካሄዱን፣ የአማራ ክልል ታጣቂዎች በትግራይ ተወላጆች ላይ ከዚህ ምድር እናጠፋችኋለን፤ ሴቶችን ሲደፍሩም ዘርሽን እያጸዳሁልሽ ነው ይሉ እንደነበር ተጠቅሷል። 
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሁማን ራይትስ ዎች መግለጫ ዘርዘር ያሉ በሰብአዊነት ከሚፈጸሙ ወንጀሎች እና ከጦር ወንጀሎች የሚስተካከል ያሉት የዘር ማጽዳት ዘመቻ ተግባራትን አስፍሯል እንዲሁም  ምክረ ሐሳቦችንም ጠቁሟል። በጉዳዩ ላይ የመንግሥትን ምላሽ ለማካተት የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ባለሥልጣናትን እንዲሁም የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባለሥልጣናትን ለማናገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት ለጊዜው አልተሳካም። ይሁንና ይኽን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ ከቃላት ልዩነትና በርቀት ያለን ቦታ ለማጣራት ከሚያጋጥሙ እጥረቶች በስተቀር ድርጊቱ ከጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ ከሚፈጸም ወንጀል የሚስተካከል ነው ብሏል። 

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

 

ሽዋዬ  ለገሰ