1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

በትግራይ አፋር ክልል አዋሳኝ አካባቢ ጥቃት

ረቡዕ፣ ግንቦት 14 2016

ከአፋር ክልል ዘልቀው ገቡ የተባሉ ታጣቂዎች በትግራይ ክልል ራያ ዓዘቦ ወረዳ በፈፀሙት ጥቃት ሰባት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የአስተዳደር አካል ገለፁ። ከሟቾች አብዛኞቹ ሕጻናት ናቸው ነው የተባለው። በአዋሳኙ አካባቢ ዛሬ እስከ እኩለ ቀን ድረስ ግጭት እንደነበርም ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/4g9kP
የትግራይ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት
የትግራይ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ምስል Million Hailessilasie/DW

በትግራይ አፋር ክልል አዋሳኝ አካባቢ ጥቃት

 

ዶቼቬሌ ያነጋገራቸው በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን የራያ ዓዘቦ ወረዳ፥ ጋራርሳ ተብሎ የሚታወቅ አካባቢ ነዋሪዎች እንደሚሉት፥ ለማክሰኞ አጥቢያ ከአዋሳኝ የአፋር ክልል አካባቢዎች የተነሱ ታጣቂዎች ሌሊት ወደ ወረዳዋ ዘልቀው በመግባት ሕጻናት የሚበዙባቸው ሰባት ንጹሐንን መግደላቸውን ተናግረዋል። ጥቃቱ ከተፈፀመባት ጋራርሳ የገጠር ቀበሌ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች እና የአስተዳደር አካላት እንደሚሉት ከግድያው ባለፈ ዛሬ እስከ እኩለ ቀን ድረስ ከአፋር ክልል ጋር በሚዋሰነው አካባቢ በሚሊሺያዎች መካከል ተኩስ ቀጥሎ መዋሉን አረጋግጠውልናል።

በተፈፀመው ጥቃት ቤተሰባቸውን ያጡት እና ከአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች መካከል የሆኑት አቶ ፅጋቡ ካሣ «ለትላንት አጥቢያ፥ እረኞች በከብቶች ግጦሽ ስፍራ ተኝተው እንዳለ ነው ደርሰው ጥቃት የፈፀሙት። ሰባት ናቸው የሞቱት። ወሬ ነጋሪም ስላልተረፈ የሞታቸው ዜና የደረሰን ጠዋት ሁለት ሰዓት ነው። ከገዳዮቹ ወገን ያልሆኑ አፋሮች ነግረውን ነው እዛ ሄደን የደረስነው። ህዝቡ ሐዘን ላይ ነው። አሁንም ቢሆን እኛ ተዉ ብንልም እየተኮሱ ነው ያሉት። እኛ በአፋር በኩል ወዳሉ የሀገር ሽማግሌዎች እየደወልን እንዲቆም ብንጠይቅም ተኩሱ እየቀጠለ ነው» ሲሉ ተናግረዋል።

በአዋሳኝ አካባቢው የነበረው ተኩስ ዛሬ ከሰዓት በኋላ መቆሙ ሰምተናል። ሌላው ያነጋገርናቸው ጥቃቱ የተከሰተባት ቀበሌ ፀጥታ ሐላፊ አቶ ዓፈራ አብርሃ ለማክሰኞ አጥቢያ ሌሊት ከተገደሉት ሰባት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ከ14 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ልጆች መሆናቸውን የገለፁ ሲሆን ሁሉም በከብት ጥበቃ ላይ የነበሩ እረኞች መሆናቸው አንስተዋል።

አቶ ዓፈራ «ከሰባቱ የሞቱት መካከል የ14 ዓመት፣ 12 ዓመት፣ የዘጠኝ እና አምስት ዓመት ሕጻናት ሲሆኑ ሌሎች የ40 ዓመት አካባቢ ዕድሜ ያላቸውም አሉ። በቅርቡ የተከሰተ የተለየ ጠብ አልነበረም። ድንገት ነው ይህ የሆነው። እንደውም በሀገር ሽማግሌዎች በኩል ግንኙነት ነው የነበረን። ይህ ሆኖ ሳለ ነው ሾልከው ገብተው በተኙበት ጨርሰዋቸው የሄዱት» ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ክስተቱን በማውገዝ ትናንት ማምሻው ባወጣው መግለጫ መነሻቸው ከአፋር ክልል ያደረጉ ሐይሎች ጥቃት መፈፀማቸውን፥ የእነዚህ ጥቃት አድራሾች ማንነትን ለመለየት ደግሞ ጥረት ላይ መሆኑን አስታውቋል። ወንጀለኞችን ለሕግ ለማቅረብ የአፋር ክልላዊ መንግሥት እና የፌደራል ፖሊስ ሐላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቋል።

ያነጋገርናቸው ጥቃት የደረሰበት አካባቢ ነዋሪዎች ሁኔታው ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳያመራ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ሊያረጋጋ ይገባል ብለዋል። በጉዳዩ ላይ የአፋር ክልል መንግሥት ኮምኒኬሽ ሐላፊን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ስልክ ባለማንሳታቸው፣ እንዲሁም ጥቃቱ የተፈፀመባት ራያ ዓዘቦ ወረዳን የምትዋሰነው የአፋር ክልልዋ መጋለ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዓሊ ያሲንን ለማነጋገር የተደረገ ጥረት ደግሞ ስብሰባ ላይ ናቸው በሚል ምክንያት ሊሳካ አልቻለም።

 

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ