በትግራይ ሰብዓዊ እርዳታ እንዴት ማድረስ ይቻላል?
እሑድ፣ ሐምሌ 4 2013የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣናት ላለፉት ስምንት ወራት ጦርነት ባመሳቀለው የትግራይ ክልል 400 ሺሕ ገደማ ሰዎች ጠኔ ተብሎ የሚጠራው የከፋ ረሐብ እንደተጋረጠባቸው ይፋ አድርገዋል። በጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት በተደረገ ውይይት ላይ ንግግር ያደረጉት የድርጅቱ የአስቸኳይ ዕርዳታ አስተባባሪ እንዳሉት ሌሎች 1.8 ሚሊዮን ሰዎች በዚያው በትግራይ በጠኔ አፋፍ ላይ ይገኛሉ።
የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች በትግራይ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚያመቻች ፤ ኤሌክትሪክ እና ኮምዩንኬሽን የመሳሰሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ ሥራ እንደሚጀምሩ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ማረጋገጫ እንደሰጧቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አርብ ሐምሌ 02 ቀን 2013 ዓ.ም. በቃል አቀባያቸው ስቴፈን ዱጃሪች በኩል ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ መውጣቱ ከተገለጸ በኋላ መንግሥት ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በተናጠል "ሰብዓዊ የተኩስ አቁም" አውጇል። መቐለን የተቆጣጠሩት ኃይሎች በአንፃሩ የተኩስ አቁሙን በመርኅ ደረጃ ተቀብለው ሰባት ቅድመ ሁኔታዎች አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እርዳታ በአዉሮፕላን ወደ ትግራይ እንዲጓጓዝ ፈቅዷል። የዓለም የምግብ መርሐ-ግብር 900 ሜትሪክ ቶን ምግብ፣ ነዳጅ፣ የተመጣጠነ ምግብ፣ የንጽህና መጠበቂያዎች እና የመጠለያ ግብዓቶች የጫኑ 50 ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ በመጓዝ ላይ መሆናቸውን እሁድ ሐምሌ 04 ቀን 2013 ዓ.ም. አስታውቋል።
ይኸ ውይይት አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ እንዴት የሰብዓዊ ዕርዳታ ለትግራይ ማቅረብ ይቻላል? የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና ቀውሱን ለመፍታት ምን አይነት ሚና ይኖረዋል? የሚሉ ርዕሰ-ጉዳዮችን ይዳስሳል።
የግጭት ትንተና እና አፈታት ባለሙያው አቶ ዓለማየሁ ፈንታው፣ የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሰላሐዲን እሸቱ እና በቪየና የዲፕሎማሲ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት አቶ ሞገስ ዘውዱ በውይይቱ ተሳትፈዋል። በዚህ ውይይት ላይ የሰላም ሚኒስቴር ተወካዮች እንዲሳተፉ ዶይቼ ቬለ ግብዣ ቢያቀርብም መልስ አላገኘም። ውይይቱ የተካሔደው ሐሙስ ሐምሌ 01 ቀን 2013 ዓ.ም. ነው።
ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ
እሸቴ በቀለ