1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በካፋ ጥቅጥቅ ደን የሚገኝበት አካባቢው ዝናባማ ነው

ማክሰኞ፣ ጥር 23 2015

በካፋ የአካባቢው ነዋሪ በራሱ ባሕል ስርዓት ተከፋፍሎ የተፈጥሮ ሀብቱን ይጠብቃል በካፋ ማኅበረሰብ ያለፈቃድ ዛፍ መቁረጥ አይችልም።ይህም ደኑ የተፈጥሮ ሀብቱን እንደጠበቀ እንዲቆይ አድርጎታል

https://p.dw.com/p/4Mvfy
Äthiopien I Kafa strict forest
ምስል Mahlet Fasil Desalegn/DW

አንድ ዛፍ ለመቁረጥ ችግኞችን መትከል የግድ ነው

የካፋ ጥቅጥቅ ደን አስደናቂ እና ውብ ምድር ነው። ከጠቅላላው የካፋ 10,602.7 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ውስጥ የተፈጥሮ የደን ሽፋን ከፍተኛውን የመሬት ድርሻ ይይዛል። 
በደቡብ ክልል በካፋ ዞን ከ761 ሺ ሄክታር በላይ የሚሸፍነው የካፋ ጥቅጥቅ ደን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በሰኔ 2010 ዓ.ም በዩኔስኮ በዓለም የብዝኃ ሕይወት ጥብቅ ቦታ ተብሎ ተመዝግቧል፡፡ በዚሁ የብዝኃ ሕይወት ጥብቅ ቦታ ጥቅጥቅ ደኖች፣ የጫካ ቡና፣ ረግረጋማ ቦታ፤ የግጦሽ መሬቶች፤ የቀርከሃ ደን እና ሌሎችም የሚገኙበት ነው፡፡ ካፋ በዓለም በብዝኃ ሕይወት  ከሚታወቁ 34 ቦታዎችም አንዱ ነው፡፡ በካፋ ጥብቅ ደን ከ250 በላይ የእፅዋት ዝርያዎች፣ የጫካ ቡና የአፍሪቃ ቀይ እንጨት፣ ቀርከሃ፣ ስድስት መቶ የሚሆኑ የእንስሳት ዝርያዎች፣ ዝንጀሮ፣ ጉማሬ አንበሳ እና የተለያዩ የወፍ ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡

አቶ ኮቺቶ ደሳለኝ የካፋ ዞን ደን አካባቢ ጥበቃ እና አካባቢ ለውጥ መምሪያ ኃላፊ ጥቅጥቅ ጫካው ከጊዜ ወደጊዜ ባለበት እንደነበር እንዲቆይ ያደረገው የኅብረተሰቡ የጥበቃ ባሕል አለው ይላሉ «ለእዚ ምክንያት የሆነው የማኅበረሰቡ የደኑን ጥበቃ ባሕሉ ነው ማኅበረሰቡ በተለያየ መንገድ  ከቆላ እስከ ደጋ ባለው የአየር ሁኔታ እንደ ደን ማኅበራት ተደራጅተው እየጠበቁ ነው ማኅበረሰቡ የራሱ ባሕላዊ አጠባበቅ ስርዓት አለው»።

«የአካባቢው ነዋሪ በራሱ ባሕል ስርዓት ተከፋፍሎ የተፈጥሮ ሀብቱን ይጠብቃል በካፋ ማኅበረሰብ ያለፈቃድ ዛፍ መቁረጥ አይችልም። አንድ የደረሰ ዛፍ ለመቁረጥ ሌሎች ችግኞችን መትከል የማኅበረሰቡ ባህል ነው። የተከሉትን ችግኝ ለአካባቢው ታላላቅ አባቶች አሳውቀው አሳይተው ፍቃድ ካልተሰጠ  መቁረጥ አይቻልም። ይህም ደኑ የተፈጥሮ ሀብቱን እንደጠበቀ እንዲቆይ አድርጎታል» ይላሉ አቶ ኮቺቶ«ማኅበረሰቡ አንድ ችግኝ ለመቁረጥ የአካባቢውን አባቶች አስፈቅዶ ነው። በየአካባቢው ትልልቅ አባቶች አሉ እነሱን አስፈቅዶ ነው ኅብረተሰቡ ሦስት የመ ህጎች አሉት። እሱም የመጠበቅ የመተካት እና የመንከባከብ ነው። ማኅበረሰቡ በብዛት ደን አደር ነው»ሲሉ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል። 

Äthiopien I Kafa strict forest
የካፋ ጥቅጥቅ ጫካ ምስል Mahlet Fasil Desalegn/DW

በካፋ ጥቅጥቅ ደን የሚገኝበት አካባቢው ዝናባማ ነው። በጫካው ውስጥ 15 ወንዞች እና ሁለት ወራጅ ወንዞች ይገኛሉ። በካፋ ጥቅጥቅ ደን ባርታ ፏፏቴ ይገኛል። ከዓመታት በፊት በበርካታ የውጪ ዜጎች ሲጎበኝ የነበረው ይህ የአገር ሀብት በአሁኑ ወቅት የጎብኚዎች ቁጥሩ ቀንሷል ያሉን በካፋ ዞን ስለ አካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ከማኅበረሰቡ ጋር የሚሠራ እና ለአካባቢው ማኅበረሰብም ግንዛቤ መሥጠት ላይ ያተኮረው (CRLF) ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት አቶ እያሱ ደሳለኝ «ከ2010  ወደዚያ ባለው አመት ብዙ ጎብኚዎች ይመጡ ነበር ነገር ግን በመላው አገሪቷ ባለው ችግር  አለመረጋጋት እንደበፊቱ አለብለን መናገር ባንችልም ቀንሷል ምክንያቱም ሲንቀሳቀሱ እናያቸው ነበር  በ2009 ግን ቁጥራቸው በጣም እየጨመረ ነበር።»

በካፋ ጥቅጥቅ ደን ላይ የተለያዩ እቅዶች ይሠራሉ። የመጀመሪያው ደኑን በመጠበቅ ወደቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ሲሆን፤ ሁለተኛው የማኅበረሰቡን የኑሮ ለማሻሻል በዘጠኝ ወረዳዎች ላይ እየተሠራ ነው። ይህን ለማከናወንም 59 ቀበሌዎች ላይ 60 ማኅበራትን ተመስርተው እየተንቀሳቀሱ ነው አቶ እያሱ መስሪያ ቤታቸው ህብረተሰቡ ላይ ላይ ግንዛቤ  ለመፍጠር  ምን እየሰራ ነው ተብለው ከዶቼ ሼሌ ለቀረበቸው ጥያቄ   «አዋጭነት ያለው ግንዛቤ ማኅበረሰቡ ካገኘ በኋላ ማኅበረሰቡ ደኑን የማይጎዳ የግብርና ሥራ ይመርጣል። የማምረቻ መስፈርት አለው። ያ የተመረጠ ሥራ ከባለሙያ ጋር በመሆን ለእዚህ ፕሮጀክት የተቋቋመ ኮሚቴ ያየዋል ። ይህንን ፕሮጀክት ገምግሞ ያፀድቃል። በዚህ መሰረት ከማኅበረሰቡ ጋር በጋራ እንሠራን ነው።» ብለዋል 

የደኑን ዘለቄታ እና ቀጣይነት በማረጋገጥ የተለያዩ ሥራዎች ይሠራሉ። ከነዚህም ውስጥ ማኅበራትን በአዲስ መልክ እና የነበሩትም በማደራጀት ነው ይላሉ አቶ እያሱ። ደን ውስጥ ያለ የተፈጥሮ ሀብትን ማኅበረሰቡ እንዴት እንደሚጠቀም ሲገልፁ ።  «አዲስ 18 ማኅበራትና አቋቁመን 42 ነባር ማኅበራትን እንደገና አደራጅተናል። በደን ውስጥ ያሉ እንደቡና ኮረሪማ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን በማህበራቸው ስርአት ውስጥ በሕግ ማእቀፍ ተቀምጦ ነው የሚጠቀሙት» ብለዋል።

Äthiopien I Kafa strict forest
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የሚገኘው የካፋ ጥቅጥቅ ደንምስል Mahlet Fasil Desalegn/DW

የካፋ ጥቅጥቅ ጫካ ካለበት ትልቁ ጫና ውስጥ አንድ የማኅበረሰቡ ቁጥር መጨመርን እና ከመሬቱ ለምነት ጋር ተያይዞ ባለሀብቶችም ወደአካባቢው የመግባት ፍላጎትም አንዱ ነው ያሉት አቶ እያሱ «በተለይ አሁን አሁን ላይ ያለው ትልቁ ጫና የመሬት ፍላጎት ነው ይላሉ። ነጻ መሬት የሚገኘው ጫካ ላይ ነው። የአካባቢው ወጣትም ይሁን ባለሀብት አይኑን ጫካው ላይ ይጥላል  ይሄ ጫና አለ።»
«ናቡ» የተሰኘው መንስታዊ ያልሆነው የጀርመን  ድርጅት በካፋ ጫካ ላይ የተለያዩ ሥራዎችን ከሌሎች አካላት ጋር በመቀናጀት በቅርበት ይሠራል።  የካፋ ጥቅጥቅ ደን  በዓለም አቀፉ የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ)  እንዲመዘገብ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። በአካባቢው ላይ ላሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች የሞያ እና የዕውቀት ድጋፍ ያደርጋል። ከእዚህ በተጨማሪም የምክር አገልግሎቶችን በመስጠት የካፋ ጫካ የተፈጥሮውን ይዘት እንዲቆይ ያደርጋል።

ካፋ ከ13ኛው ከፍለ ዘመን ጀምሮ እጅግ ጠንካራ እና የተደራጀ መንግስትና ንጉሣዊ አገዛዝ ስርዓት እንዲሁም እጀግ የሰለጠነ እና የተደራጀ የፖለቲካ መዋቅር እንደነበረዉ አያሌ የታሪክ ማሰረጃዎች ያሳያሉ።

ማኅሌት ፋሲል 

ማንተጋፍቶት ስለሺ