1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በተቃውሞ የተበተነው የሕዝብ ስብሰባ

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 13 2010

የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለዉን ልዩ ጥቅም በሚመለከት በተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ የሕዝብን አስተያየት ለማሰባሰብ በዛሬዉ ዕለት በተወካዮች ምክር ቤት የተጠራዉ ስብሰባ በተቃውሞ ተበተነ። ከተቃውሞው መነሻዎች አንዱ «በአዋጁ ላይ ከሕዝብ ጋር ዉይይት አልተካሄደም» የሚል ነው።

https://p.dw.com/p/2prPB
Äthiopien Parlament Hailemariam Desalegn
ምስል DW/Y. G. Egziabher

ምክር ቤቱ ለድጋሚ ስብሰባ ቀን አልቆረጠም

በስብሰባው የተሳተፉት የተወካዮች ምክር ቤት አባል የተከበሩ አቶ ቦንያ ኡዴሳ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት በረቂቅ አዋጁ ላይ ህዝቡ «በቂ ዉይይት አላደረገበትም» የሚለው ለዛሬው ስብሰባ መቋረጥ አንዱ ምክንያት ነው። ሌላኛው ምክንያት ደግሞ «በኦሮሚያ ክልል በአሁኑ ወቅት ያልተረጋጋ የፀጥታ ሁኔታ ስላለ ቅድሚያ ትኩረት የሚያሻዉ ይኸዉ ነዉ» የሚል እንደሆነ ከኦሮሚያ ጉጂ ዞን የቡሌ ሆራ ተወካይ የሆኑት የምክር ቤት አባል ተናግረዋል። የዛሬዉ ስብሰባ እንደታሰበዉ ያልተካሄደዉ «የኦህዴድ አባላት በኦሮሚያ ክልል ላለዉ ሁኔታ ምላሽ ካላገኘን በሚል ረግጠዉ በመዉጣታቸዉ ነዉ» በሚል የተሰራጨውን መረጃ ግን አስተባብለዋል። 

ስብሰባውን ከጠሩት የተወካዮች ምክር ቤት አካላት አንዱ የሆነው የህግ እና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት ስብሰባው የተሰረዘበት ዋና ምክንያት «ህዝብ በአዋጁ ላይ እንዲወያይ» የተነሳው ሀሳብ ተቀባይነት በማግኘቱ እንደሆነ ተናግረዋል። ስብሰባው ለሌላ ጊዜ ቢተላለፍም መቼ እንደሚካሄድ ገና አለመወሰኑን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። ከሁለቱ የምክር ቤት አባላት ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ፡፡    

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ