1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በተመድ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ውሳኔ ላይ የኢትዮጵያ አቋም

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 9 2014

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የመብት ጥሰቶችን የሚያጣራ ዓለም አቀፍ መርማሪ አካል ለማቋቋም የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ በድምጽ ብልጫ ማጽደቁን የኢትዮጵያ መንግስት ነቅፎ አጣጥሎታል፡፡

https://p.dw.com/p/44Vlx
Äthiopien | Staatsministerin für Kommunikationsdienste | Selamawit Kassa
ምስል S.Getu/DW

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ትናንት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ባደረገው ልዩ ስብሰባ በኢትዮጵያ ዓመትን ባለፈው ጦርነት የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን የሚያጣራ ዓለም አቀፍ መርማሪ አካል ለማቋቋም የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ በድምጽ ብልጫ ማጽደቁን ነቅፈው ነው መግለጫውን የሰጡት፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቱ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ተቋማትን ከማጠናከር ጀምሮ በተግባር በርካታ ውጤቶችን ማምጣቱን በማንሳት በትናንቱ ስብሰባ ለኢትዮጵያ ፍጹም በጎ የማይመኙ የፖለቲካ ፍላጎታቸው ውሳኔ ነው ያሳለፉት ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ 
የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ቆመናል ካሉ አካላት ጋር በትብብር መስራቱንም አክለው የትናንትናው የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ውሳኔ በነዚህ ጥረት ላይ ውሃ እንደመቸለስ ነው ተብሏልም፡፡ ውሳኔው በሉዓላዊነት ጣልቃ መግባት በመሆኑ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ውድቅ መሆኑንም ሰላማዊት ካሳ አክለዋል።
ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ ማየት ለሚፈልግ የትኛውም ገለልተኛ አካል በሩን ክፍት ያደርጋል ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ከሸማቂ ቡድኖች ጋር ግንኙነት በማድረግ ተጠርጥረው በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር ስለዋሉት ጋዜጠኖች በመግለጫቸው ያካተቱት የኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ጋዜጠኞቹ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያ ጉዳያቸው ይጣራል ነው ያሉት፡፡ ፖሊስ ለአሶሽየትድ ፕሬስ የሚሰሩ ሶስት ጋዜጠኞችን ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ነበር በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰውና መንግስት ሸኔ በሚል በሽብረተኝነት የፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ጦርን በዓለማቀፍ በማስተዋወቅ ወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ ሲል በቁጥጥር ስር ያዋላቸው፡፡ 
ስዩም ጌቱ
ልደት አበበ