1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቤኒሻንጉል: ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከ 40 በላይ ሰዎች ተገደሉ 

ሰኞ፣ ጳጉሜን 1 2013

በቤኒሻንጉል፤ ካማሺ ዞን ምዥጋ በተባለ ወረዳ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከ40 በላይ ሴቶች በታጣቂዎች ተገደሉ። በካመሺ ዞን  ድዴሳ በሚባል ስፋራ ያለው የጸጥታ ሁኔታ የከፋ መሆኑንና ከ50 በላይ ሰዎች( በብዛት ሴቶች) በታጣቂዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው እና ሁኔታዉ በማጣራት ላይ እንደሆነም ተመልክቶአል፡፡

https://p.dw.com/p/3zyOi
Karte Äthiopien AM

የዞኑ የጸጥታ ችግር አሳሰቢ በመሆኑ ተጨማሪ የጸጥታ ኃይል እንዲገባ ጥያቄ ቀርቦአል

 

በካማሺ ዞን ምዥጋ በተባለ ወረዳ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከ40 በላይ  ሴቶች በታጣቂዎች መገደላቸውን የቤኒሻንል ጉሙዝ ክልል የሰቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ገለጸ፡፡ የቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ አበራሽ ደጃሽ እስከ ትናንት በስቲያ ቅዳሜ ድረስ ጉሙዝን ነጻ እናወጣለን ብለው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ሰዎች በወረዳው ደዴሳ በተባለ ስፋራ መገደላቸውን ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል፡፡በቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ እና ምክትል ኮሚሽነር የሆኑት  ኢንስፔክተር ምስጋናው ኢንጅፋታ በካመሺ ዞን  ድዴሳ በሚባል ስፋራ ያለው የጸጥታ ሁኔታ የከፋ መሆኑንና ከ50 በላይ ሰዎች( በብዛት ሴቶች) በታጣቂዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው እና በማጣራት ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን ሰዳል፣ አጋሎ ሜጢ፣ እና ሚዥጋ በተባሉ ወረዳዎች ውስጥ በታጣቂዎች ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ጥቃቶች መፈጸማቸውን የክልሉ ሴቶች፣ወጣቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ  አስታውቀዋል፡፡ እንደ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ አለምነሽ ደጃሽ በካማሺ ዞን በአጋሎ መጢ እና ሚዥጋ በተባሉ ስፋራዎች ከግንቦት 9 /2013 ዓ.ም አንስቶ በታጣቂዎች የበርካታ ሰዎች ህይወት አልፈዋል፡፡ የዞኑን ሰላም ለማስፋን የክልሉ አመራሮች በተገኙበት ከዚህ ቀደም የሰላም ጉባኤ መካሄዱን  የገለጹ ሲሆን ባለፉው ቅዳሜም በነዋሪው ላይ ጉዳት መድረሱን አብራርተዋል፡፡

በካማሺ ዞን ሚዥጋ ወረዳ ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 24 /2013 ዓ.ም ደግሞ ከ30 በላይ ሴቶች በእነዚሁ ታጣቂዎች በደረሰባቸው ጥቃት በአንድ ስፍራ ህይወታቸው ማለፉንና የወረዳው ነዋሪ በሰላማዊ ሰልፍ ድርጊቱን ማውገዙን አክለዋል፡፡ በወረዳው በታጣቂዎች የሚደረሰውን ጥቃት የፌደራል እና ክልል ጸጥታ ሀይሎች ትኩረት በመስጠት በአስቸኳይ እርምጃ በመውሰድ ማስቆም እንዳለባቸውንም ተናግረዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊና ምክትል ኮሚሽነር ኢንስፐክቴር ምስጋናው እንጅፋታ በዞኑ ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን አመልክቷል፡፡   በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ጸረ ሰላም ያሉት ሀይል በነዋሪ ውስጥ በመደበቅ እና በቤት ውስጥ በመሆን በጸጥታ ሀይሎች ላይ እንደሚተኩስ ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ሰኞና ማክሰኞ በዞኑ (ሚዠጋ)ቦሎጅጋንፎይ በተባለ ወረዳ ድደሳ ቀበሌ ውስጥ ከ50 በላይ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ሀላፊው አስረድተዋል፡፡ የዞኑ የጸጥታ ችግርም አሳሰቢ በመሆኑ ተጨማሪ የጸጥታ አስከባሪዎች ወደ ስፋራውን እንዲላኩ መጠየቃቸውንም ኢንስፔከተሩ አክለዋል፡፡ 

በካማሺ ዞን እና በሌሎች የቤኒሻጉል ስራዎች በታጣቂዎች ይደረሳሉ በተባሉ ጥቃቶች ከዚህ ቀደምም የበርካታ ዜጎች ህይወት ያለፈ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተፈናቅለዋል፡፡ በዞኑ ሚያዚያ ወር ሰዳል በተባለ ወረዳም በታጣቂዎች ደርሰዋል በተባለው ጥቃት በርካቶች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን ከ4ሺ በላይ ዜጎች ደግሞ መፈናቃላቸውን የክልሉ የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል፡፡

 

ነጋሳ ደሳለኝ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ