1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቆጂ ብርቱ አትሌቶችን ማፍራት ምነው ተሳናት?

ሰኞ፣ ሰኔ 27 2014

የአርሲ ዞን አንዷ ከተማ በቆጂ ከአትሌት ደራርቱ ቱሉ እስከ ቀኒሳ በቀለ፤ የዲባባ ስኬታማ ቤተሰብ እና ሌሎችም በቁጥር የላቁ ስኬታማ አትሌቶች ከዚህች ስፍራ ወጥተዋል። በአንድ ወቅት ዓለምን ያስደመሙ አትሌቶች ይፈልቁባት የነበረችው በቆጂ አሁን አሁን ስመ ጥር አትሌቶችን እንደ ቀድሞ ማፍለቅ የተሳናት ለምን ይሆን?

https://p.dw.com/p/4De5n
ምስል Seyoum Getu/DW

የሥመጥር አትሌቶች መፍለቂያ ነበረች

በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ታሪክ የአርሲ ዞን አንድዋ ከተማ በቆጂ ያበረከተችው አስተዋጽኦ ምንጊዜም ጉልህ ሥፍራ ይዞ ይቆያል። ከአትሌት ደራርቱ ቱሉ እስከ ቀኒሳ በቀለ፤ የዲባባ ስኬታማ ቤተሰብ እና ሌሎችም በቁጥር የላቁ ስኬታማ አትሌቶች ከዚህች ስፍራ ወጥተዋል። አሁን አሁን ግን ከዚህች የአትሌቶች ከተማ በቆጂ የሚወጡ የጎላ ስም ያላቸው አትሌቶችን መስማት እጅጉን አዳጋች ሆኗል። በአንድ ወቅት ዓለምን ያስደመሙ አትሌቶች ይፈልቁባት የነበረችው በቆጂ አሁን አሁን ስመ ጥር አትሌቶችን እንደ ቀድሞ ማፍለቅ የተሳናት ለምን ይሆን?

የአዲስ አበባ ወኪላችን ሥዩም ጌቱ ወደ በቆጂ ተጉዞ አትሌትክሱን ሰንገው ስለያዙ ተግዳሮቶች ዳሰሳ ለማድረግ ሞክሯል። ስለ ችግሮቹ እና መፍትኄዎቻቸውም የቀድሞ አትሌቶች እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም አነጋግሯል።

የከዋክብት አትሌቶች ምንጭ፤ በአትሌትክሱ ዓለም የኢትዮጵያ ስም በተደጋጋሚ ለማስጠራት ምክኒያት የነበሩ ቁጥራቸው የበዛ አያለ አትሌቶች ከአከባቢው ወጥተው፤ የትንሽየዋን ከተማ ስም በጉልህ በማጻፍ አስተዋውቀዋታል፡፡ ከባህር ጠለል 2800 ሜትር ከፍ ባለ ደጋማ ስፍራ የምትገኘው የአትሌቶቹ መናኻሪያ በቆጂ ከኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ በስተ ደቡብ ምስራቅ 220 ኪ.ሜ. ርቃም ትገኛለች፡፡ በኦሮሚያ ክልል የአርሲ ዞን አንዱ ከተማ በቆጂ ክረምት የሌው በጋ በውርጫማው የአየር ጠባይዋም ትታወቃለች፡፡

Äthiopien - Leichtathletik in Beqoji Assela
ምስል Seyoum Getu/DW

እያደገች ባለችው በዚህች አነስተኛ ከተማ የአትሌቲክስ ልምምዶች የባህል ያህል በየቦታው ሲደረግ ማስተዋልም እንግዳ ነገር አይነደለም፡፡ ስኬትን ያለሙ አድካሚውን፤ ረጂሙን የአሸናፊነት መንገድ ለመያዝ የቋመጡ፤ ከ10 ዓመት ታዳጊ እስከ የ20ዎቹ እድሜ ወጣቶችም የእየለት አድካሚውን ሥራ ተያይዘውታል፡፡

በልምምድ ስፍራው ትኩረቴን ከሚስቡ የ10 ዓመት ታዳጊ ዮብሳን ዓለማየሁ ወደ ቋሚ የአትሌቲክሱ ስልጠና የመጣችበትን መንገድ በጣፋጭ የልጅነት አንደበቷ ስትገልጽ “ወደ ስታዲየም አከባቢ የስፖርተኞች መለያ ልብስ ሲሸጥ ተመልክቼ ስቦኝ ነበር፡፡ አባቴ ገዝቶልኝ ስመጣ ለምን እንደገዛ ጠየቅኩት፡፡ እሱም ከአሁን ወዲያ አትሌቲክስ ልምምድ እንድትጀምሪ ተፈቅዶልሻል አለኝ፡፡ እኔም መጀመሪያ ይከለክሉኝ ስለነነበር ይሄው ዘንድሮ ስልጠና ጀምሬያለሁ” በማለት ጉጉቷን አብራርታለች፡፡

ዕውቁ የአትሌቶች አሰልጣን ስንታየሁ እሸቱ በዚህች ከተማ ለ38 ዓመታት ያህል ከስፖርት መምህርነት ተነስተው በስኬት ጎዳና ያለፉ ከአትሌት ደራርቱ ቱሉ እስከ የአቴንስ እና ቤጂነግ ኦሎምፒኮቹ ፈርጦች ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩኔሽ ዲባባን፤ እንዲሁም ሌሎች ለቁጥር የሚታክት ብዛት ያላቸው ብርቱ አትሌቶች በስራቸው ሰልጥነው አልፈዋል፡፡ ከከተማዋ የአትሌቲክስ ቡድን አሰልጣኝነት ከራቁ ዋል አደር እንዳሉ የሚናገሩት አሰልጣኝ ስንታየሁ አሁን ላይ ደግሞ የበቆጂ የአትሌቲክስ አካዳሚ ማዕከል ውስጥ በሙያቸው ያገለግላሉ፡፡ ከአሰልጣኝ ስንታየሁ እሸቱ ጋር ለቃለመጠይቃችን አንጸባራቂ ድል በዓለም መድረክ ያስመዘገቡ አትሌቶች ወጥተው በወረዱበት ከበቆጂ ከተማ ወጣ ወዳለው፤ ነገር ግን እምብዛም ወደማርቀው የዳሞታ ደናማና ተራራማ ስፍራ አቀናን፡፡ በዚህ ስፍራ እንኳንም መሮጥ ወትቶ መመለስም የሸክም ያህል ከባድ ነው፡፡ አሰልጣኝ ስንታየሁ እንደሚሉት ግን በእድሜያቸው ልክ ለአትሌቶቹ በአሰልጣኛቸው በሚሰጠው መጠን በዚህ ስፍራ የሚደረገው ልምምድ ለአትሌቶቹ ጥንካሬ፤ በደን መሃል የሚደረግ ልምምድ ደግሞ ለቅልጥፍናቸው ኤነተኛ ሚና አለው፡፡ አትሌቶቹ  6 ኪ.ሜ. የሚገመተውን ይህን የዳሞታን ደን ይዞራሉ፡፡ 200 ሜትር ያህል ሽቅብ የቆመውንም ተራራ ይወጣሉ ይወርዳሉ፡፡

Äthiopien Bekoji | Bekoji Town, Sportzentrum & Laufzentrum
ምስል Seyoum Getu/DW

ከዋክብቶቹን ያፈራች በቆጂ ከምንም ተነስታ እንደ አገርም እንደኣለምም የልጆቿ ስኬት ምስጥሩ ምን ይሆን በሚል ትኩረት በመሳቧ፤ በተለይም በዓለማቀፉ ወረርሽኝ ኮቪድ-19 እና በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁናቴ የተቀዛቀዘ ቢመስልም የበርካታ ቱሪስቶችና ተመራማሪዎች መዳረሻም ለመሆን በቅታ ነበር፡፡ ይሁንና ዛሬ ዛሬ በቆጂ የትናንትናውን ስኬታማ ስሟን ለጊዜውም ቢሆን ማስቀጠል የተሳናት ትመስላለች፡፡ አሁን ላይ በዓለም አትሌትክስ ተስፋን እያሳየ ከሚገኘው ለሜቻ ግርማ ሌላ ላቅ ባለ የስኬት ደረጃ የሚጠቀስ ሌላ ስም ከዚህች የአትሌቲክስ ማፍለቂያ ስፍራ መጥራት አዳጋች መሆኑ በርግጥም ግራ አጋቢ ነገር ነው፡፡

የባርሴሎና ባለድል የአፍሪካ እንስት ሯጮች ተምሳሌት ደራርቱ ቱሉ፣ በሚለየው የአሯሯጥ ዘዬና አይበገሬነታቸው ከማንም አዕምሮ የማይፋቁ ቀኔኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ፤ እስከ የቅርብ ጊዜው ስኬታማዋ ገንዘቤ ከዚያው ከአጠገባቸው ሲወጡ፣ ስማቸውንም በደማቅ የስኬትና ውጤታማ ታሪክ ሲያሰንዱ የተመለከቱ በርካቶች፤ ቢያንስ በእነሱ ስኬት በመነሳሳት ከተቻለም ለመላቅም እያለሙ ሲደክሙ፤ ሳይታክቱ ሲሰሩም ይታያሉ፡፡ በቆጂ ትናንት ያልነበራት ተጨማሪ አሰልጣኞችን ቢታፈራ፤ የዛሬ 10 ዓመት ገደማ የገነባችው የታዳጊዎች ማፍለቂያ አካዳሚ ብትገነባም ውጤት የለም፡፡ የትናንት ስሟም በነበር እንጂ የቀጠለ ሊሆን ከቶውኑም አልቻለም፡፡ ችግሩ የቱ ጋ ይሆን? ለ4 አስርት ዐመታት ያህል በቆጂን የሚያውቋት አሰልጣኝ ስንታየሁ እሸቱ፡ ተፈጥሮ እንኳ ለዘርፉ ስኬታማነት ሁሉ ነገር በሰጠችው በዚህ ስፍራ አብዝቶ የሰራ ለሽንፈት እጅ አይሰጥም ይላሉ፡፡ ምክኒያት ደግሞ ከፍተኛ የአልቲትዩድ አቀማመጥና ከባዱ የአየር ሁኔታ ነው፡፡ ይሁንና የስፖርቱን ዘርፍ ይነስም ይብዛ ሞያተኛ ባልሆኑ ግለሰቦች መምራት መጀመር የቁልቁለት ጅማሮ ትልቁ ምክኒያት ነው ይላሉም፡፡

Äthiopien Bekoji | Bekoji Town, Sportzentrum & Laufzentrum
ምስል Seyoum Getu/DW

በ2004 ዓ.ም. ተስፈኛ ታዳጊ ወጣቶችን በማሰባሰብ የበቆጂ የአትሌቲክስ ስኬታማ ሰንሰለቱን ለማስቀጠል አልሞ የቅበላ አቅሙን በ52 ታዳጊዎች የጀመረውና፤ ባለፉት 10 ዓመታት 193 ተስፈኛ አትሌቶችን ተቀብሎ 133 ያህሉን ክለቦችን ለመቀላቀል አብቅቷል፡፡ የበቆጂ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል፡፡ ከዚህ ቀደም በየዓመቱ ተዳጊዎችን ተቀብሎ የስልጠና እና ሌላም አስፈላጊውን አገልግሎት ሁሉ የሚሰጠው ማዕከሉ ዘንድሮ የተቀበላቸውን እድሜያቸው 18 ያልደረሱ 40 ገደማ ታዳጊዎችን ደግሞ እስከ 4 ዓመት አቆይቶ ስለማብቃት ያልማል፡፡ አቶ ኃይሉ ለማ ማዕከሉን በዳይሬክተርነት ይመራሉ፡፡

እሳቸውም ቢሆኑ የስፖርቱ አልፎ አልፎ ከሞያተኞች ውጭ መመራት ትልቁ ማነቆ እንደሆነ አልሸሸጉም፡፡ ለበቆጂ አትሌቲክስ ከስኬታማነት መንሸራተት የሞያተኛ እጥረት መንስኤ ምክንያት ሆኖ ሊቀርብ እንደማይችል ግን ያስገነዝባሉ፡፡ “በቆጂ እንዳውም አሁን በላቀ ደረጃ በሙያተኞች ተንበሽብሻለች፡፡ ትናንት በስፖርት መመህራን ሲሰለጥኑ የነበሩ አትሌቶች ዛሬ ላይ በተሻለ ብቃት ላይ ባሉ ባለሙያዎች ይሰለጥናሉ፡፡ ችግሩ ያለው የባለሙው ሙያተኝነት ላ ነው፡፡ እራስን ለስራው ከመስጠት ይልቅ የግል ጥቅም ማሳደድ ጎልቶ ይስተዋላል” ሲሉም ማብራሪያቸውን አክለዋል፡፡

Äthiopien Bekoji | Bekoji Town, Sportzentrum & Laufzentrum | Stadion in schlechtem Zustand
ምስል Seyoum Getu/DW

ብቁ አትሌቶችን ለአገር ማበርከትን ቀዳሚ ዓላማው አድርጎ የሚሰራው ይህ የበቆጂ አትሌቲክስ ማእከሉ ለቀጣይ አራት ዓመታት በስልጠና ላይ ቆይተው ይመረቃሉ ተብለው የሚገመቱ 36 ሰልጣኖች አሁን ላይ ከስሩ አሉት፡፡ ማዕከሉ ውስጥ በ400 ሜትር ርቀት የሩጫ ውድድር ላይ እየሰለጠነ ያለው ሰኚ ደመቅሳ የስኬት የተስፋ ጭላንጭል ካሳዩ ይባልለታል፡፡ በሂደት ግን ኢትዮጵያውያን ጥንትም በሚታወቁበት የእረጅም ርቀት ሩጫን ስለመቀላቀል የሚያልመው ሰኚ በጽናታቸው የሚለዩ ያሏቸውን ኢትዮጵያዊውን አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና ኬኒያዊው ኢሊውድ ኪፕቾጌን አርዓያዎቹ አድርጎ ያነሳቸዋል፡፡

በአትሌቶች ከተማዋ በቆጂ ከስልጠና ማእከሉም ውጪ በርካታ የሯጮች ቡድን መኖሩን አስተውያለሁ፡፡ አንደኛው ቡድን ደግሞ ሲንቄ የሴቶች ልማት ማህበር በተባለ ግብረሰናይ ድርጅት የሚደገፍና በተለይም አቅም በሚያንሳቸው ወላጆች ልጆች ላይ አተኩሮ የሚሰራ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ በርካታ ሴት ልጃገረዶች፤ በተለይም ገና በታዳጊ እድሜ ላይ የሚገኙ ይሰለጥኑበታል፡፡ የቀድሞዋ አትሌት ፈቲያ አብዲ የዚህ ቡድን አሰልጣኝ ናት፡፡ እንደ አሰልጣኝ ፈቲያ ገለጻ “አትሌቶቹ ትጋትና ፍላጎት ያላቸው ቢሆኑም ዋና ፈተና እየሆነ የመጣው እየናሬ ባለው የኑሮ ሁኔታ ምክኒያት የአትሌቶች መፍረክረክ ነው፡፡ ስፖርተኛ ሳይበላ አይሰራም፡፡ ቢቻል ስለምግብም ማሰብ አኖርበትም” ስትል አንዱ የስፖርቱ ተግዳሮች ነው ያለችውን ጉዳይ አንስታለች፡፡

የበቆጂ ከተማ አትሌትክስ ፕሮጀክት ሌላው የአትሌቶች ማመንጫ መስመር ነው፡፡ የዚ አትሌቲክስ ቡድን አባል የሆነችው መስከረም ወርቁ በኢትዮጵያ ለማንም ተሳክቶ ያልተመለከትነው የ100 ሜትር ርቀት ውድድር ላይ ስኬትን ስለማምጣት የምታልም ወጣት ናት፡፡ የትምህርት ቤት ውድድሮች ለተስፋዋ ምክኒያት መሆኑን የምትገልጸው መስከረም ስበዛ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባን ታደንቃለች፡፡

Äthiopien Bekoji | Bekoji Town, Sportzentrum & Laufzentrum | Biniam, Trainer
ምስል Seyoum Getu/DW

ወጣት ቢኒያም ደግሞ የበቆጂ ከተማ ፕሮጀክት እና የከተማዋ አትሌቲክስ ቡድን አሰልጣኝ ነው፡፡ አሰልጣኙ ለበቆጂ አትሌትክሲ ውድቀት ዋነኛ ተጠያቂ የሚያደርጉት ስፖርቱን የሚመሩትን ባለስልጣናትን ነው፡፡ “ስለ ስፖርቱ ምንነት ምንም የማያዉቁና መሬት ላይ ምን እየተከናወነ እንዳለ የማይረዱ ግለሰቦች ዘርፉን ይመራሉ፡፡ አንድ ቀን እንኳ እዚህ ሜዳ ላይ ደርሰው የከተማዋ አትሌቶች ምን ችግር እንዳለባቸውም የማይጠይቁ ናቸው” ሲል፤ ሰንሰለታማ ያለውን የአመራር ችግሩን ከላይ ከፌዴሬሽን ጀምሮ መፈታት የሚገባው ሲል ትችቱን ሰንዝሯል፡፡

የበርካታ ከዋክብት አትሌቶች ምንጭ በቆጂ፤ አትሌቶችን የማፍራት እምቅ አቅሟን ትጠቀም ዘንድ የተፈጥሮ ችሮታ ላይ የተሻለ የአትሌትክስ መሰረተ ልማትን ከመገንባት ግን ጀርባዋን የሰጠች ትመስላለች፡፡ በዚያች ታሪካዊና ብዙ የተባለላት ከተማ አንድም ለዘርፉ ስልጠና የሚመች ስፖርተኞች ሊሰሩበት የሚችል ስታዲየም አንኳ የለም፡፡ በከተማዋ ያለው ስታዲየምም ከብቶች ተሰማርተውበት ሞተር ሳይክሎች መለማመጃ ብቻ ሆኖ ነው የተመለከትኩት፡፡ በአትሌቶቿ መንደር በቆጂ በዚህ ደረጃ ለመወዳደሪያ የሚውል የሜዳነት መልክ ያለው ሜዳ መታጣትም ከማነጋገርም አልፎ ግራ ያጋባል፡፡ በከተማዋ ውስጥ እና ቅርብ ቦታዎች ላይ የነበሩ የአትሌቶች ማሰልጠኛ ምቹ ቦታዎች ላይ የነበረው ደን ተጨፍጭፎ ቤቶች በመደደው የተሰራባቸው ስፍራዎችም አሉ፡፡ ይህ ደግሞ አትሌቲክሱን የሚለማመዱ ምቹ ሁኔታን ፍለጋ ከከተማዋ ርቀው እንዲሄዱ ነው የሚያስገድዳቸው፡፡

በበቆጂ ማዘጋጃ ቤት ቅጥር ጊቢ ውስጥ በመጠን እጅግ ያነሰች ለብቻዋ ተለይታ የቆመች አነስተኛ ጎጆ የበቆጂ ከተማ ስፖርትና ወጣቶች ጽህፈት ቤት ስለመሆኗ በግርግዳዋ ላይ በተለጠፈ ጽሁፍ ይለያል፡፡ ያቺ አነስተኛ ጎጆ በውስጧ አራት የጽ/ቤቱ ባልደረቦችን አጣባ ስትይዝ ውስጧ ግን ከበቆጂ እና ሌሎችም አከባቢ በወጡ ከዋክብት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ስዕል ተሽቆጥቅጧል፡፡ አቶ ህርጳ ሱፋ በጽ/ቤቱ የወጣቶች ዘርፍ የስራ ሂደት መሪ ናቸው፡፡ እሳቸውም ቢሆኑ የባለሙያዎች በተገቢ ቦታ አለመመደብ፣ የስልጠና ቦታ ደኖች መጨፍጨፍ እና ቆሞ የቀረው ከምንም ላይ ያልደረሰው የበቆጂ ስታዲየም ነገር እንደ ዘርፉ ማነቆዎች ጠቃቅሰው “ይሰራበታል” ብለው ተስፋ እንዳላቸው አመልክተዋል፡፡

አንጋፋው የአትሌቲክስ አሰልጣኝ ስንታየሁ እሸቱ የቀድሞው ስኬታማ ጉዞው ደብዛው በጠፋው የበቆጂ አትሌቲክስ ላይ አሁንም ተስፋ ከማይቆርጡ ናቸው፡፡ “ከሰራን ወደ በፊቱ የማንመለስበት ምክኒያት አይታየኝም፡፡ ስፖርቱ ከመኮፈስ ይልቅ ወርደው መሬት ላይ መስራትን ይጠይቃል፡፡ ያንን ካደረግን በእርግጠኝነት ወደ ቦታችን እንመለሳለን” ሲሉ ተስፋቸውን አጠናክረዋል፡፡

Äthiopien Bekoji | Bekoji Town, Sportzentrum & Laufzentrum | Haile Geberesillassie, Laufstar
ምስል Seyoum Getu/DW

ከዚያው ከበቆጂ በቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኘው አሰላ ዙሪያ በመውጣት በዓለም የአትሌቲክስ ታሪክ የራሱን አሻራ አጉልቶ ያለፈው የበርካታ ክብረወሰንና ድሎች ባለቤት እና ባንድ ወቅት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የነበረ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ስለ በቆጂ አትሌቲክስ የስኬት ሂደት መፈተን ቀዳሚው ምክንያት የትኩረት ማነስ ችግር ነው ይላል፡፡ እንደ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ ማብራሪያ በፊት በፊት በተፈጥሮም ከትምህርት ቤት ወደ ቤት በመመላለስ ሂደት የሚገኝ ጥንካሬ አሁን በርካታ ነገሮች በመቀያየራቸው ዘርፉን ወደ ማዘመን መገባት ይገባል ብሏል፡፡ በየትምህርት ቤቶችና ስልጠና ማዕከላት የውድድር ማነስንም ኃይሌ እንደ አብይ ምክኒያት አንስቶታል፡፡ ቶሎ ካልተሰራበት የበቆጂ አትሌቲክስ እምቅ አቅም ከናካቴው ደብዛው እንዳይጠፋ ስጋቱንም ይገልጻል፡፡ የቀድሞ አትሌቶች ዘርፉ ላይ ስኬት እንዲቀጥል ትውልዱ ላይ ምን ሰራችሁ ተብሎ የተጠየቀው ኃይሌ፤ ‘ምንም’ ሲል ይመልሳል፡፡ ሙያተኛን የሚገፋ እንጂ የሚያቅፍ አሰራር አለመኖሩን ደግሞ በምክኒያትነት አንስቶታል፡፡ ቱሪስት እንኳ በከፍተኛ ሁኔታ የመሳብ አቅም ባላት በቆጂ በርካታ ዓለማቀፍ አትሌቶች ወደ ከተማዋ እንዳይጎርፉ የስታዲየሙ ነገር ትልቁ ማነቆ ነው ብሏልም፡፡  

አቶ ሳሙኤል ብርሃኑ ደግሞ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስልጠና ጥናት እና ምርምር ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የረጅም ሩጫ ስኬት ቀንሷል የሚባለውን አስተያየት አይቀበሉም፡፡ “እንደ አሸን የፈሉ” ባሏቸው የረጂም ሩጫ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተለያዩ የዓለም የውድድሮች መድረክን ተቆጣጥረውታል ሲሉም ይሞግታሉ፡፡

Äthiopien Bekoji | Bekoji Town, Sportzentrum & Laufzentrum | Samuel Birhanu, technischer Direktor
ምስል Seyoum Getu/DW

አቶ ሳሙኤል አገርን ወክለው በሚደረጉ ውድድሮች ውጤት መጥፋት ላይ ግን ልዩነት የላቸውም፡፡ አገሪቱ አቅም ያላቸው እና ስኬታማ አትሌቶችን ይዛ በአገር ውድድሮች ላይ የውጤት ማሽቆልቆል ለምን መጣ የሚለውን በጥናት ለመመለስ ፌዴሬሽኑ እያስጠና ያለው ጥናት ምናልባትም ከአንድ ወር በኋላ ይፋ ሊደረግ እንደሚችል አንስተዋል፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ በአልጣኖች እና ፌዴሬሽን እንዲሁም አትሌቶች መካከል ጥብቅ ቁጥጥር አለመኖሩ ግን ለአገር ውጤት ማሽቆልቆል እንደጉልህ ምክኒት ሊጠቀስ እንደሚችል አመልክተዋል፡፡ ይህም የሆነው አትሌቶቹ በግል ውድድራቸው ላይ ዓመቱን በሙሉ አቅማቸውን መጨረሻቸው አገር ወደ ምትወከልበት ውድድር ሲመጡ እንደሚፈትናቸውም ተናግረዋል፡፡

የአትሌቶች ማፍለቂያ ምንጭ በቆጂን መነሻ አድርገን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እንደቀደመው ጊዜ በላቀ ደረጃ የገነኑ አትሌቶች የማፍራት እና የኢትዮጵያ በዓለም መድረኮች የውጤት ማሽቆልቆል የገጠመበትን ምክኒያት እና መፍትሄውን የዳሰስንበት የዛሬ ልዩ የስፓርት መሰናዶአችን ይህን ይመስላል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ