1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቅጡ ባላገገመች ቀበሌ ምርጫ እንዴት ይካሔዳል?

ሰኞ፣ ሰኔ 14 2013

ከሦስት ወራት ገደማ በፊት ደም አፋሳሽ ግጭት የገጠማት በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ የምትገኘው ወሰን ቁርቁር ቀበሌ ለምርጫ እየተዘጋጀች ነው። መንግሥት ለመመሥረት ድምጽ ከሚሰጡ የቀበሌዋ ነዋሪዎች አብዛኞቹ ግን ቤቶቻቸው ተቃጥሎ በመጠለያ ውስጥ ናቸው።

https://p.dw.com/p/3vFdW
Äthiopien Kebelle in Jile Timuga woreda | Beschädigte Schule
ምስል Eshete Bekele/DW

በአማራ ክ/መ በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ጅሌ ጥሙጋ ወረዳዉስጥ ትገኛለች

ከሦስት ወራት ገደማ በፊት ደም አፋሳሽ ግጭት የገጠማት በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ የምትገኘው ወሰን ቁርቁር ቀበሌ ለምርጫ እየተዘጋጀች ነው። መንግሥት ለመመሥረት ድምጽ ከሚሰጡ የቀበሌዋ ነዋሪዎች አብዛኞቹ ግን ቤቶቻቸው ተቃጥሎ በመጠለያ ውስጥ ናቸው።

የወሰን ቁርቁር ቀበሌ የከፋ ጉዳት ካደረሰባት ግጭት ገና በቅጡ አለማገገሟን የሚሳብቁ ጠባሳዎች አሏት። የተቃጠሉ መኖሪያ ቤቶች አመድ እና ፍርስራሽ እዚህም እዚያም ይታያል። መንደሯ የነበራት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ብርቱ ጉዳት ደርሶበታል። የመማሪያ ክፍሎቹ እና የተማሪዎቹ መቀመጫዎች ውልቅልቃቸው ወጥቶ ይታያሉ። የቀበሌዋ አነስተኛ የጤና ማከልም አገልግሎት ከማይሰጥበት ደረጃ ላይ ነው።

Äthiopien Kebelle in Jile Timuga woreda | Beschädigte Schule
ምስል Eshete Bekele/DW

በቀበሌው ለደረሰው ጉዳት አቶ መሐመድ ሙሳን የመሳሰሉ ነዋሪዎች ምስክር ናቸው። ገበሬው አቶ መሐመድ በወቅቱ በተፈጠረው ግጭት ወንድማቸውን አጥተዋል፤ የመኖሪያ ቤታቸው ተቃጥሏል።

“ባልጪ የሚባለው ቀበሌ መጠለያ ተሰርቶ እዚያ ስንኖር ነበር። አሁን ወደ ቀያችሁ ተመለሱ ቤት ይሰራላችዃል፣ መንግሥት ድጋፍ ያደርግላችዃል ተብሎ አሁን ቀበሌያችን ላይ ተመልሰናል። የተሰራ ቤት የለም። ካንድ በኩል የተቃጠለ ቤት አለ። ድሮ አንድ አባወራ የሚኖርበት ቤት ላይ አሁን ዘጠኝ አባወራ የሚኖርበት ቤት አለ” ሲሉ አሁን ያሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል።

Äthiopien Kebelle in Jile Timuga woreda | Beschädigte Schule
ምስል Eshete Bekele/DW

የወሰን ቁርቁር ቀበሌ ሊቀመንር አቶ አሊዬ መሐመድ 691 አባወራዎች መፈናቀላቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ወሰን ቁርቁር በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ የምትገኝ ቀበሌ ነች። ጉዳት የደረሰባት ከሶስት ወራት ገደማ በፊት በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙት የሰሜን ሸዋ ዞን እና የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት ነው። በግጭቱ በሁለቱም ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ከተሞች የከፋ ጉዳት ደርሷል። አቶ አሊዬ መሐመድ “ከዚች ቀበሌ ብቻ ወደ አስራ ስድስት ነው አስራ ሰባት ሰዎች ሞተዋል። የቆሰሉ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከዚያ በላይ ነው ከሃያ በላይ ነው” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ጤፍ እና ማሽላ አምራቹ ገበሬ መሐመድ ኑሯቸው ተናግቶ እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል። “ሁለት ኪሎ፣ አምስት ኪሎ ወይም 50 ኪሎ የቻሉትን እየረዱን ነው። አሁን ሶስተኛ ወራችንን ይዘናል። ለአንድ ሰው አስራ አምስት ኪሎ ስንዴ ከመንግሥት ተሰጥቶናል” ብለዋል።

የወሰን ቁርቁር እና አካባቢው ነዋሪዎች ከግጭቱ ዳፋ በቅጡ ባያገግሙም ለምርጫ እየተዘጋጁ ነው። ቀበሌዋ በምትገኝበት የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ-ፍትህ ፓርቲ ፣የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ እጩዎቻቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለአማራ ክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ያወዳድራሉ።

Äthiopien Kebelle in Jile Timuga woreda | Beschädigte Schule
ምስል Eshete Bekele/DW

በወረዳው በምርጫ አስፈጻሚነት የተሰማራው ወጣት ኡመር አብደላ “የጸጥታ ሁኔታው የፈጠረው ተጽዕኖ የለም። ያለው እንቅስቃሴ ሰላማዊ ነው። ዝግጅቱ ግልጽ እና ተዓማኒነት ባለው ሁኔታ እየተካሔደ ነው። ምንም የሚያስፈራ ነገር የለም። ወቅታዊው ሁኔታም ምንም የሚያስቸግር ነገር የለም” ሲል ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ባስተላለፈው ውሳኔ በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አቅራቢያ በሚገኙት ማጀቴ፣ ሸዋሮቢት እና ኤፌሶን አካባቢዎች የሚካሔደውን ምርጫ አራዝሟል። በተጠቀሱት አካባቢዎች ምርጫ ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ይካሔዳል። ምርጫ የተራዘመባቸው አካባቢዎች የገጠማቸውን የጸጥታ ችግር የምትቋደሰው ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ግን ለሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም.  ቆርጣለች። የወሰን ቁርቁር ቀበሌ ሊቀመንር አሊዬ መሐመድ ”ዛሬ ይኸን ምርጫ ካላካሔድንው በምክር ቤት ተወካይ ልናጣ ነው። የእኛን ጉዳይ፣ የእኛን ችግር የማይገልጽበት አካሔድ ይኖራል። ስለዚህ በዚሕ ጉዳት ውስጥም ሆነን ምርጫ እንመርጣለን ብለን ነው የወሰንው” ሲሉ ፋይዳውን ገልጸዋል።

Äthiopien Kebelle in Jile Timuga woreda | Beschädigte Schule
ምስል Eshete Bekele/DW

በአንድ ጎኑ በተቃጠለ ቤት እየኖሩ ለህልውናቸው እርዳታ ጠባቂ የሆኑት ገበሬ ነገ ድምጽ ከሚሰጡ የወረዳው ነዋሪዎች መካከል ናቸው።

”ምርጫ ግዴታችን ነው። ያለመንግሥት የሚኖር አገር የለም። አንመርጥም ብልም ኢትዮጵያ ወደ መፍረስ ልትሔድ ነው” የሚሉት አቶ መሐመድ  ”አማራጫችን ምርጫ መርጠን መንግሥት በሁለት እግር ቆሞ እንዲያስተካክል ብለን ነው ተስፋችን” በማለት አሸናፊው የሚጠብቀውን የቤት ሥራ የሚጠቁም አስተያየት ሰጥተዋል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ